ትራምፕ ላይ የተከሰተው የደም ሥር ችግር ምንድን ነው? ምን ያህል ለሕይወት አስጊ ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ሐሙስ የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጽህፈት ቤት በአገሪቱ መሪ የደም ሥር ላይ ከባድ ያለ የጤና ችግር እንዳለ አስታውቋል።
በመደበኛ ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት የዋይት ሐውስ ፕሬስ ሴክሬታሪ ካሮሊን ሌቪት የ79 ዓመቱ ትራምፕ እግሮቻቸው ላይ እብጠት እንደተስተዋለ ገልጸው፣ ይህም በሐኪም ምርመራ እንዲያደርጉ እና ያሉበት ሁኔታ እንዲታወቅ ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል።
በቅርቡም ትራምፕ በመዳፋቸው ጀርባ ላይ የተለጠፈ ነገር የሚያሳይ ፎቶግራፍ ተሠራጭቶ ነበር።
ነገር ግን ዋይት ሐውስ ይህ ካለባቸው የደም ሥር ችግር ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው እና በተደጋጋሚ ከሚያደርጉት የእጅ መጨባበጥ ጋር የተያያዘ መሆኑን ገልጿል።
ይህ የአሜሪካው ፕሬዝዳንትን ያጋጠማቸው እና በተለይ ከ70 ዓመት በላይ በሆኑ ሰዎች ላይ የሚከሰተው የደም ሥር መታወክ ችግርን በተመለከተ ለማወቅ የሚያግዙ አንዳንድ ነጥቦች እነሆ. . .
ሥር የሰደደ የደም ሥር እክል ምንድን ነው?
ለጋዜጠኞች የተሠራጨው የዋይት ሐውስ ሐኪም የሆኑት ዶክተር ሾን ባርባቤላ ማስታወሻ እንደሚያመለክተው ትራምፕ የገጠማቸው የጤና እክል "ቀለል ያለ እና የተለመደ" ሲሆን፣ በተለይ ዕድሜያቸው ከ70 በላይ የሆኑ ሰዎችን ያጋጥማል።
ሥር የሰደደ የደም ሥር እክል የሚከሰተው የእግር ደም መላሽ ቧንቧዎች ደም ወደ ልብ ተመልሶ እንዲሄድ ማድረግ በማይችሉበት ጊዜ ሲሆን፣ ይህም በታችኛው የእግር ክፍል ላይ ደም እንዲጠራቀም ምክንያት ይሆናል።
በደም ዝውውር ሂደት ደም በመደበኛ ሁኔታ ከእግር ወደ ልብ የሚመለሰው በስበት ኃይል ሲሆን፣ ይህ ሁኔታ ግን በዕድሜ በገፉ ሰዎች ላይ ከበድ ይላል።
ይህም ሊሆን የሚችለው ከዕድሜ መግፋት ጋር በተያያዘ በደም ሥር ውስጥ ያሉ ቫልቮች በመዳከማቸው ምክንያት ሊሆን ይችላል።
ምልክቶቹ ምንድን ናቸው?
ሥር የሰደደ የደም ሥር እክል በሚያጋጥም ጊዜ ደም በእግር ላይ በመጠራቀም በቅርቡ በወጡ የትራምፕ ፎቶግራፎች ላይ እንደታየው በቁርጭምጭሚት አካባቢ እብጠትን ሊያስከትል ይችላል።
በተጨማሪም ሕመም እና ማሳከክን ሊያካትት ይችላል፣ ወይም በጣም ከባድ ከሆነ ደግሞ በቆዳ ላይ ለውጦችን በማስከተል ቁስለት፣ የደም መፍሰስ ወይም በእግር የደም መላሽ ቧንቧዎች ውስጥ የደም መርጋትን ይፈጥራል።
በዋክ ፎረስት ዩኒቨርሲቲ የደም ሥር ቀዶ ሕክምና ክፍል ኃላፊ የሆኑት ዶ/ር ማቲው ኤድዋርድስ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ይህ ሁኔታ "ከከባድ የጤና ችግሮች ጋር ሊያያዝ ይችላል፣ ነገር ግን በራሱ ከባድ ሕመም አይደለም እና በጣም የተለመደ ነው" ብለዋል።
"በፕሬዝዳንት ትራምፕ የዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ሰዎች መካከል ምናልባት ከ10 እስከ 35 በመቶ የሚሆኑት ይህ የጤና ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል እላለሁ።"
በተጨማሪም ከመጠን በላይ ውፍረት፣ የደም መርጋት ታሪክ መኖር እና ሥራቸውን ለረጅም ጊዜ ቆመው የሚሠሩ ሰዎች ለዚህ የደም ሥር ችግር ሊጋለጡ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የትራምፕ ዶክተር ምን አሉ?
ፕሬዝዳንት ትራምፕ በእግራቸው ላይ እብጠት ካዩ በኋላ "ለጥንቃቄ ሲባል" በዋይት ሐውስ የሕክምና ክፍል ምርመራ ተደርጎላቸዋል ሲሉ የትራምፕ ዶክተር ሾን ባርባቤላ በመግለጫቸው ላይ ጠቅሰዋል።
ዶ/ር ባርባቤላ ፕሬዝዳንት ትራምፕ "አጠቃላይ ምርመራ" ተደርጎላቸው "አስጊ ያልሆነ እና የተለመደ ዓይነት" ሥር የሰደደ የደም ሥር እክል እንደተገኘባቸው ገልጸዋል።
"ዋናው ነገር የጥልቅ ደም ወሳጅ ቧንቧ እብጠት (DVT) ወይም የደም ወሳጅ ቧንቧ በሽታ መኖሩን የሚያሳይ ምንም ምልክት የለም" በማለት ትራምፕ "በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ" አክለዋል።
በተጨማሪም የተደረጓቸው ምርመራዎች "የተለመደ የልብ መዋቅር እና ተግባርን አሳይተዋል" ያሉት ዶክተር ባርባቤላ "የልብ ድካም፣ የኩላሊት እክል ወይም አጠቃላይ የሰውነት ሥርዓታቸው ላይ የሕመም ምልክቶች አልተገኙም" ብለዋል።
ዶ/ር ባርባቤላ በቅርብ ጊዜ ፎቶግራፎች ላይ የታየው እና አንዳንድ ጊዜ በሜካፕ የተሸፈነው በትራምፕ የእጅ መዳፍ ጀርባ ላይ የተስተዋለውን መበለዝም ጠቅሰዋል።
"ይህ በተደጋጋሚ በሚያደርጉት የእጅ መጨባበጥ እና የልብ እና የደም ቧንቧ ችግሮችን ለመከላከል በመደበኛነት በሚወስዱት አስፕሪን የተነሳ በለስላሳ ኅብረ ሕዋሶቻቸው ላይ ከሚያጋጥም መቆጣት የሚመጣ ነው" ሲሉ አብራርተዋል።
የብሪታንያ እና የአየርላንድ የደም ዝውውር ሥርዓት ጤና ማኅበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ፕሮፌሰር ኢያን ቼተር በትራምፕ ዶክተር የተባለው ሊሆን እንደሚችል ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ለሕይወት አስጊ ነው?
በአሜሪካ የሚገኘው የደም ዝውውር ቀዶ ሕክምና ማኅበር በሽታው ምልክቱ በታየበት አካል ክፍል ላይ የመክበድ እንዲሁም እብጠት እና ሕመም ያስከትላል ብሏል።
በአንዳንድ ሁኔታዎች እንዲህ ያለው ሥር የሰደደ የደም ሥር እክል የሚያሠቃይ ቁርጠት፣ መሸምቀቅ እና የእግር ላይ ቁስለትን ያስከትላል።
እንዲሁም ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስን እና የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችን ወደ መገደብም ሊያመራ እንደሚችል ፕሮፌሰር ቼተር አመለክተዋል።
ችግሩ ላለበት ሰው ተብለው የሚሠሩ አጥብቀው የሚይዙ ረጅም ካልሲ ማድረግ የሚረዳ ሲሆን፣ ሕመምተኞች በመኝታ ጊዜ እግሮቻቸውን ከፍ በማድረግ እንዲተኙ እና የሚቀቡ ሎሽኖችን እንዲጠቀሙ ባለሙያዎች ይመክራሉ።
ፕሮፌሰር ቼተር እንደሚሉት ይህ የጤና እክል "ለሕይወት አስጊ የመሆን ዕድሉ በጣም በጣም ዝቅተኛ ነው።"

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ትራምፕ ስለ ጤንነታቸው ምን አሉ?
ባለፈው ሚያዝያ ወር ትራምፕ ለሁለተኛ ጊዜ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ የመጀመሪያውን ዓመታዊ አካላዊ ምርመራ አድርገዋል።
"ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጠንካራ የልብ፣ የሳንባ፣ የነርቭ እና በአጠቃላይ የአካላዊ ጤንነት በጥሩ ጤንነት ላይ ይገኛሉ" ሲሉ ዶ/ር ባርባቤላ በወቅቱ ባሰፈሩት ማስታወሻ ላይ ጠቅሰዋል።
የጤና ግምገማው ፕሬዝዳንቱ ኮሌስትሮልን ለመቆጣጠር የተለያዩ ዓይነት መድኃኒቶችን እንዲሁም ለልባቸው ጤንነት አስፕሪን እንደሚወስዱ እና ለቆዳቸውም ሕመም ክሬም እንደሚጠቀሙ አስታውቋል።
ፕሬዝዳንት ትራምፕ ጤናማ ስለመሆናቸው አዘውትረው የሚናገሩ ሲሆን፣ አንድ ጊዜ እራሳቸውን "እስከ ዛሬ አሜሪካን ከመሩ ፕሬዝዳንቶች ሁሉ እጅግ ጤናማው ነኝ" ሲሉ ገልጸዋል።
ትራምፕ ከመጀመሪያው ዓመታዊ የአጠቃላይ ጤና ምርመራቸው በኋላ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት "በአጠቃላይ በጣም ጥሩ ሁኔታ ላይ እንዳለሁ ይሰማኛል" እና "ጥሩ ልብ፣ ጥሩ ነፍስ፣ በጣም ጥሩ ነፍስ አለኝ" ብለዋል።
ምን ዓይነት ሕክምና አለው?
ለዚህ የጤና እክል ያለው የሕክምና አማራጭ የደም ዝውውርን በማሻሻል እና የሕመሙን ምልክቶች በመቆጣጠር ላይ የሚያተኩር ነው።
እግርን ከፍ አድርጎ መተኛት እና መቀመጥ፣ ጠበቅ አድርጎ የሚይዙ ረጅም ካልሲዎችን ማድረግ፣ እንዲሁም መደበኛ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ እብጠትን ለመቀነስ እና የደም ዝውውርን ለማቀላጠፍ ይረዳሉ።
በጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ የሕክምና ትምህርት ቤት መረጃ መሠረት ይህንን የደም ሥር እክልን ለማከም የሚከተሉት ዘዴዎች ተግባራዊ ሊሆኑ ይችላሉ።
የደም ዝውውርን የሚያሻሽሉ መድኃኒቶች ጥቅም ላይ ማዋል ይቻላል። አስፕሪንም በእግር ላይ የሚውጡ ቁስሎችን ለማዳን ይታዘዛል። ከሰውነት ውስጥ ከመጠን ያለፈ ፈሳሽን በኩላሊት በኩል እንዲወጣ የሚያደርጉ መድኃኒቶችም አልፎ አልፎ ጥቅም ላይ ይውላል።
ከዚህ ባሻገርም የደም ዝውውርን በማሻሻል በእግር ላይ የሚፈጠረውን እብጠት ለማስወገድ የተለያዩ አማራጮች ያሉ ሲሆን፣ የደም ዝውውርን ለማቀላጠፍ የሚሰጥ የመርፌ ሕክምናም ሌላው አማራጭ ነው።
ችግሩ ከበድ ያለ ከሆነ ቀዶ ሕክምና አስፈላጊ ሊሆን ይችላል። ይህም የተጎዳ የደም ሥር እና ቫልቮች ላይ አስፈላጊ የሚሆን ቀዶ ሕክምና በማድረግ የደም ፍሰትን በማሻሻል ሕመምና እብጠትን ያቃልላል።
ለሁሉም የሕክምና አማራጮች ግን በዋናነት የሐኪም ምክር ማግኘት ቀዳሚው እርምጃ መሆን አለበት።















