አሜሪካ ተጨማሪ የአፍሪካ አገራት ቪዛ ጠያቂዎች የገንዘብ ማስያዢያ እንዲያቀርቡ ወሰነች

የምዕራብ አፍሪካ አገራት ማኅበር ፓስፖርት እና የአሜሪካ ሰንደቅ ዓላማ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በርካታ የምዕራብ አፍሪካ አገራት በአሜሪካ የቪዛ ማስያዣ ይጠየቃሉ ወይም የጉዞ እገዳ ተጥሎባቸዋል

አሜሪካ ተጨማሪ የአፍሪካ አገራትን ቪዛ ለማግኘት የዋስትና ማስያዣ ገንዘብ ከሚጠየቁ ውስጥ ማካተቷን ይፋ አደረገች።

ባለፈው ዓመት ሐምሌ በተወሰኑ አገራት ላይ ተግባራዊ የተደረገው የዋስትና ማስያዣ አሠራር ዜጎች የአሜሪካ ቪዛ ለማግኘት ሲያመለክቱ አስከ 15 ሺህ ዶላር ማስያዣ ማቅረብ እንዳለባቸው ያዛል።

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ድረ ገጽ ላይ በወጣው ዝርዝር 38 አገራት የተካተቱ ሲሆን፣ 24ቱ የአፍሪካ አገራት ናቸው።

የአሜሪካ መንግሥት አሁን ዜጎቻቸው በዚህ አሠራር ውስጥ እንዲያልፉ በተጨማሪነት ይፋ ያደረጋቸው አገራት አልጄሪያ፣ አንጎላ፣ ባንግላዲሽ፣ ቤኒን፣ ቡሩንዲ፣ ኬፕ ቬርዲ፣ ኩባ፣ ጂቡቲ፣ ዶሚኒካን፣ ፊጂ፣ ጋቦን፣ አይቮሪ ኮስት፣ ኪርጊስታን፣ ኔፓል፣ ናይጄሪያ፣ ሴኔጋል፣ ታጂኪስታን፣ ቶጎ፣ ኡጋንዳ፣ ቫንዋቱ፣ ቬንዙዌላ እና ዜምባብዌ ናቸው።

በዚህ አሠራር መደበኛዎቹን ቢ1 እና ቢ2 የተባሉትን የሥራ እና የቱሪስት ቪዛዎች ለማግኘት የሚያመለክቱ የአገራቱ ዜጎች ጉዳያቸውን በሚመለከተው የቪዛ ባለሥልጣን ውሳኔ መሠረት አምስት ሺህ፣ አስር ሺህ ወይም 15 ሺህ ዶላር ማስያዣ ማቅረብ አለባቸው።

ይህ ባለፈው ዓመት ሐምሌ መጨረሻ ላይ ይፋ ተደረገው የቪዛ አሠራር በቀዳሚነት ቡታን፣ ቦትስዋና፣ ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ጋምቢያ፣ ጊኒ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ማላዊ፣ ሞሪታኒያ፣ ናሚቢያ፣ ሳኦ ቶሚ፣ ታንዛኒያ፣ ተርክሜኒስታን እና ዛምቢያ ነበሩበት።

በቪዛ ማመልከቻው ወቅት የሚቀርበው የገንዘብ መስያዣ አመልካቾች ቪዛ ለማግኘታቸው ዋስትና እንዳመይሆን እና ቪዛውን ከተከለከሉ ወይም አግኝተው በተፈቀደላቸው ጊዜ ከአሜሪካ ሲወጡ ተመላሽ የሚሆን እንደሆነ ተገልጿል።

ይህ የአሜሪካ መንግሥት በ38 አገራት ዜጎች ላይ የጣለው ቪዛ የማግኛ ቅድመ ሁኔታ ከተፈቀደላቸው ጊዜ በላይ በአሜሪካ የሚቆዩ ሰዎችን ለመቆጣጠር መሆኑን ባለሥልጣናት ይናገራሉ።

ነገር ግን ይህ የገንዘብ ማስያዣ ግዴታ ቤተሰብ ለመጎብኘት፣ ለሥራ እና ለሌሎች ጉዳዮች ወደ አሜሪካ በሚጓዙ ሰዎች ላይ ከባድ ጫና የሚፈጥር እና ጉዟቸውን የሚያደናቅፍ ይሆንል በማለት ቅሬታ እየቀረበበት ነው።

ዶናልድ ትራምፕ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ የአሜሪካ መንግሥት የውጭ አገር ዜጎች ወደ አሜሪካ በሚያደርጉት ጉዞ ላይ በአካል ተገኝቶ ቃለ ምልልስ ማድረግን እና አመልካችን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያጋሯቸውን መልዕክቶች መመርመርን ጨምሮ የተለያዩ ጥብቅ አሠራሮችን ተግባራዊ አድርጓል።

በዚህ ዜጎቻቸው ወደ አሜሪካ ለመጓዝ ሲጠይቁ አስከ 15 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ማስያዣ ከሚጠየቁት ዝርዝር ውስጥ ወደ ሁለት ሦስተኛው የሚጠጉት የአፍሪካ አገራት ናቸው።

አሜሪካ በኅዳር ወር መጨረሻ ላይ ባወጣችው የጉዞ እገዳ ውስጥም በርካታ የአፍሪካ አገራት ይገኙበታል። የአሜሪካ መንግሥት የአገሩን ደኅንነት ለመጠበቅ በሚል በጣለው ዕደገ ውስጥ ቡርኪና ፋሶ፣ ማሊ እና ኒጀር ይገኙበታል።

ነገር ግን ሦስቱ የምዕራብ አፍሪካ አገራት አሜሪካ በዜጎቻቸው ላይ የጣለችውን የጉዞ ዕገዳን ተከትሎ እነሱም በምላሹ የአሜሪካ ዜጎች ወደ አገራቸው እንዳይገቡ የአጸፋ ዕገዳ ጥለዋል።