በሳዑዲ አረቢያ በሞት ይቀጣል ተብሎ የነበረው ትንሹ እስረኛ ከዓመታት እስር በኋላ ተለቀቀ

ሙርታጃ ቁሬይሪስ በተያዘበት ጊዜ እና ከአስር ቤት ሲወጣ

የፎቶው ባለመብት, ESOHR

የምስሉ መግለጫ, ሙርታጃ ቁሬይሪስ በተያዘበት ጊዜ እና ከአስር ቤት ሲወጣ

በፀረ መንግሥት ተቃውሞ ውስጥ ተሳትፏል ተብሎ ተጠርጥሮ ታስሮ የቀየውን የ13 ዓመት ታዳጊ ሳዑዲ አረቢያ መልቀቋን የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ተናገሩ።

ሙርታጃ ቁሬይሪስ የተባለው ይህ ታዳጊ የሞት ቅጣት ይጠብቀዋል ተብሎ ተሰግቶ የነበረ ሲሆን በኋላ ላይ ግን እስር ተፈርዶበታል።

ታዳጊው የታሰረው ከስድስት ዓመት በፊት ሲሆን፣ ምክንያቱም በተለያዩ የአረብ አገራት ተካሂዶ የመንግሥታት ለውጥ ባስከተለው ሕዝባዊ ተቃውሞ ወቅት ሳዑዲ ውስጥ በተካሄደ ሰልፍ ላይ ተሳትፏል በሚል ነው።

በዚህም ሳቢያ ታዳጊው ሙርታጃ ቁሬይሪስ በሳዑዲ አረቢያ ውስጥ በፖለቲካዊ ተቃውሞ የተነሳ ለእስር የተዳረገ ትንሹ አስረኛ ነው ተብሎ ይታመናል።

አነሳ ቁጥር ያላቸው የሺዓ ሙስሊሞች በሚኖሩበት በምሥራቃዊው የሳዑዲ ግዛት ውስጥ የተካሄደን ተቃውሞ በሚያሳይ ቪዲዮ ላይ ታዳጊው ከሌሎች ልጆች ጋር በብስክሌት ላይ ሆኖ ከታየ በኋላ ነው ለእስር የተዳረገው።

የሱኒ ሙስሊሞች ከፍተኛውን ቁጥር በሚይዙባት ሳዑዲ አረቢያ ያሉ የሺዓ ሙስሊሞች በአገሪቱ ውስጥ እንደ ሁለተኛ ዜጋ ነው የምንታየው በሚል ስለሚገጥማቸው መድልዎ ቅሬታቸውን ሲያሰሙ ቆይተዋል።

ከአስር ዓመት በፊት በተለያዩ የአረብ አገራት ውስጥ በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ የተበረታቱት የሳዑዲ የሺዓ ማኅበረሰብ አባላት በወቅቱ ወደ አደባባይ ወጥተው በአገሪቱ ባለሥልጣናት ላይ ተቃውሟቸውን አሰምተው ነበር።

የፀጥታ ኃይሎችም ተቃውሞውን በኃይል የተቆጣጠሩት ሲሆን፣ በተካሄዱት ተቃውሞዎች ተሳትፈዋል የተባሉ በርካታ ሰዎች ተይዘው ሲታሰሩ፣ ጥቂት የማይባሉት ተገድለዋል።

ከዚሁ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ የታሰረው ታዳጊው ሙርታጃ ቁሬይሪስ ለበርካታ ዓመታት ክስ ሳይመሰረትበት በአስር ላይ እንደቆየ የሰብአዊ መብት ቡድኖች ተናግረዋል።

ታዳጊው አስር ቤት ከመግባቱ በፊትና ከዓመታት እስር ከተለቀቀ በኋላ የተነሳቸው ፎቶዎች የዕድሜውን ልዩነት ያመለክታሉ። መጀመሪያ ሲያዝ የህጻንነት ገጽታ ያለው ሙርታጃ ቁሬይሪስ አሁን ሲፈታ ጺም ማብቀል የጀመረ ወጣት ሆኗል።

ታዳጊው ካለክስ ለዓመታት በእስር ቆይቶ በመጨረሻ ላይ ፍርድ ቤት ቀርቦ ክስ ሲመሰረትበት “የአክራሪ ሽብርተኛ ቡድን” አባል ነው ተብሎ ነበር።

በተጨማሪም በፖሊስ ጣቢያ ላይ ቤት ውስጥ የተሰራ ተቀጣጣይ ነገር በአንድ ፖሊስ ጣቢያ ላይ ወርውሯል ከተባለው ታላቅ ወንድሙ ጋር አብሮ ነበርም ተብሏል።

በታዳጊው ላይ ለቀረበው ክስ የእምነት ቃሉን መስጠቱ በዐቃቤ ሕግ እንደማስረጃ የቀረበ ቢሆንም፣ እንዲያምን የተደረገው በማሰቃይ እንደሆነ ልጁ ገልጿል።

ዐቃቤ ሕግም በእነዚህ ክሶች ምክንያት በታዳጊው ላይ የሞት ቅጣት እንዲወሰንበት የጠየቀ ሲሆን፣ የመብት ተሟጋቾችም ሙርታጃ ቁሬይሪስ ሊሰቀል ይችላል ብለው ሰግተው ነበር።

የልጁ እድሜ ለጋ መሆንና የሚጠብቀው ቅጣት ሞት ሊሆን እንደሚችል መነገሩ ዓለም አቀፍ ትኩረትን በመሳቡ ምክንያት፣ በቀረበበት ክስ በሞት ከመቀጣት ይልቅ አስር እንዲፈረድበት ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ይታመናል።

መጀመሪያ ላይ የአሰራ ሁለት ዓመት አስር የተፈረደበት ታዳጊው፣ በኋላ ላይ አስሩ ወደ 8 ዓመት እንዲቀነስ ተደርጎለታል።

በዚህም በታዳጊነቱ ወቅት የተፈረደበትን የአስር ጊዜውን አጠናቆ ወደ ወጣትነት በሚሸጋገርበት ዕድሜው መፈታቱ ተነግሯል።