ውጤቴ አነስ ብሎ አስተማሪውን የገደለው የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት

የፎቶው ባለመብት, POLICE HANDOUT
አዮዋ ውስጥ ዊላርድ ሚለር የተባለ የ17 ዓመት አሜሪካዊ የስፓኒሽ ቋንቋ መምህሩን ደብድቦ በመግደሉ የዕድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት።
መምህርቷ ‘አነስተኛ ውጤት ሰጥታኛለች’ በሚል በቤዝቦል መጫወቻ ዱላ ደብድቦ እንደገደላት ተገልጿል።
18 ዓመት የሞላውና በድብደባው ተሳታፊ የነበረው ጀርሚ ጎዳሌ በነሐሴ ፍርድ ይበየንበታል።
ድብደባውን ፈጽመው ሲከሰሱ 16 ዓመታቸው ሲሆን በሕጉ እንደ አዋቂ ሰው ተከሰዋል።
ኖሄማ ግራበር የተባለችው ስፓኒሽ መምህርቷ 66 ዓመቷ ነበር።
ዋና ተከሳሹ በአመክሮ ከእስር ሊለቀቅ የሚችለው ቢያንስ ከ35 ዓመት በኋላ ነው።
ለመምህርቷ ቤተሰቦች 150,000 ዶላር ካሳ እንዲከፍል ታዟል።
የዕድሜ ልክ እስራቱን ያስተላለፉት ዳኛ ተከሳሹ በወቅቱ ‘ታዳጊ ስለነበር ድርጊቱን አልተገነዘበም’ ነበር የሚለውን መከራከሪያ ውድቅ አድርገዋል።
ዳኛ ሻውን ሾወርስ “ክፋት ልደት የለውም” ብለዋል።
የመምህርቷ ቤተሰቦች እንዳሉት ተማሪው አንዳችም መጸጸት አላሳየም።
መምህርቷ መገደሏን ተከትሎ ባለቤቷ ፓልም በሐዘን መሞቱን ቤተሰቡ ተናግሯል። የፍርድ ቤት ውሳኔው ከመተላለፉ ከአንድ ቀን በፊት ነው ሥርዓተ ቀብሩ የተፈጸመው።
ፍርዱ ሲተላለፍ ተከሳሹ ማኅበረሰቡን ይቅርታ ጠይቋል። የመምህርቷን ቤተሰብ “ስለፈጠርኩት ሰቆቃና ቤተሰባችሁን በማወኬ ታላቅ ይቅርታ እጠይቃለሁ” ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, POLICE HANDOUT
ረዥም እስር እንዳይፈረድበት ዳኛውን ሲጠይቅ “ብዙ ጊዜ ታስሬ ማንነቴን እና የመጣሁበትን መርሳት አልፈልግም” ብሏል።
ዐቃቤ ሕግ እንዳለው ሁለቱም ተከሳሾች መምህርቷን ደብድበዋል።
ከጥቃቱ በነጋታው የመምህርቷ አስክሬን ከትምህርት ቤት ወጥታ ትጓዝ በነበረበት ፓርክ ውስጥ ድንኳን ሥር ተደብቆ ፖሊሶች አግኝተዋል።
ተከሳሹ መምህርቷ ስፓኒሽ የምታስተምርበትን መንገድ ‘እንዳልወደደው’ ለፖሊስ ቃል ሰጥቷል።
ውጤቱ እያነሰ እንደመጣና ይህም ወደ ኮሌጅ ለመግባት እንደሚያዳግተውም ተናግሯል።
ሜክሲኮ የተወለደችው መምህርት ኖሄማ ግራበር እአአ ከ2012 ጀምሮ በፌርፊልድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አስተምራለች።












