ትዊተር፤ ሜታ የሠራው አዲሱን ተቀናቃኝ መተግበሪያ ትሬድስ እከሳለሁ ሲል አስጠነቀቀ

አዲሱ መተግበሪያ ትሬድስ

የፎቶው ባለመብት, EPA

ትዊተር በፍጥነት በርካታ ተጠቃሚዎች እያፈራ ያለውን ትሬድስ የተሰኘ መተግበሪያ እከሳለሁ ሲል አስጠነቀቀ።

ረቡዕ ሥራ የጀመረው ትሬድስ፤ ፌስቡክ እና ኢንስታግራምን የሚያስተዳድረው ሜታ የፈበረከው ሲሆን ከትዊተር ተመሳሳይነት ያለው ነው።

የትዊተር አለቃ ኢላን መስክ “ውድድር መልካም ነው፤ ሥርቆት ግን ቦታ የለውም” ሲል ወቅሷል።

የፌስቡክና ኢንስታግራም እናት ኩባንያ ሜታ ግን ይህን አስተባብሏል።

ሜታ በይፋ በለቀቀው ደብዳቤ የቀድሞው የትዊተር ሠራተኛ ነው አዲሱን መተግበሪያ የሠራው የሚለውን ሐሜት ውድቅ አድርጓል።

እንደሜታ ከሆነ እስካሁን 30 ሚሊዮን ሰዎች መተግበሪያውን አውርደው መጠቀም ጀምረዋል።

ቢቢሲ እንደታዘበው ትሬድስ ነገረ ሥራው ከትዊተር ጋር እጅግ ተመሳሳይነት ያለው ነው።

አንድ የዜና አውታር እንደገለጠው የትዊተር ጠበቃ አሌክስ ስፒሮ ለሜታ አለቃ ማርክ ዛከርበርግ ደብዳቤ ልከዋል።

ደብዳቤው ሜታ “የትዊተርን ሚስጥሮችና የአእምሮ ንብረቶች ሕጋዊ ባለሆነ መንገድ ቀድቷል” የሚል ወቀሳ ይዟል።

በተለይ ደግሞ የትዊተር ጠበቃ እንደሚሉት ሜታ በርካታ የቀድሞ የትዊተር ሠራተኞችን በመቅጠር “ከባድ ሚስጥር የሆነ መረጃዎችን” ማግኘት ችሏል ይላሉ።

“ትዊተር የአእምሮ ንብረት መብቱን ለማስጠበቅ አስፈላጊውን ያደርጋል፤ ሜታ የትዊተርን ሚስጥራዊ መረጃዎች ከመጠቀም እንደታቀብም ያሳስባል።”

ደብዳቤው በእጁ የገባው ቢቢሲ ሜታና እና ትዊተርን አስተያየት ጠይቆ ምላሽ እየተጠባበቀ ነው።

ኢላን መስክ ደብዳቤውን በተለመከተ ከተለጠፈ አንድ መልዕክት ሥር ገብቶ ““ውድድር መልካም ነው፤ ሥርቆት ግን ቦታ የለውም” የሚል ፅሑፍ አሥፍሯል።

የሜታ ቃል አቀባይ አንዲ ስቶን ደግሞ ወደ ትሬድስ አቅንቶ “እዚህ ትሬድስ የሚሠራ ማንም የቀድሞ የትዊተር ሠራተኛ የለም። ሐሰት ነው” ብሏል።

ማርክ ዛከርበርግ፤ ትሬድስ የትዊተር ተቀናቃኝ ሆኖ መምጣቱንና ከኢንስታግራም ጋር ግንኙነት እንዳለው ቢያምንም ራሱን የቻለ መተግበሪያ ነው ይላል።

ኢላን መስክ ትሬድስ ይፋ ከሆነ በኋላ “በሐሰተኛ ደስታ በኢንታግራም ስቃየን ከምደብቅ፤ ትዊተር ላይ የማላውቀው ሰው ቢዘልፈኝ ይሻለኛል” ሲል አዲሱን መተግበሪያ ሸንቆጥ አድርጓል።

የትዊተር ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊንዳ ያካሪኖ በበኩሏ ትዊተር በወር 260 ሚሊዮን ተጠቃሚዎች እንዳሉት ጠቅሳ “ይህን ማንም አይደግመውም” ብላለች።

ሜታና ትዊተር በያዝነው ዓመት በርካታ ሠራተኞቻቸውን የቀነሱ ሲሆን በለተይ ሜታ ከ10 ሺህ በላይ ሠራተኞቹን አሰናብቷል።

ኢላን መስክ ባለፈው ጥቅምት ትዊተርን የግል ንብረቱ ካደረገው በኋላ 7500 ሠራተኞቹን ቀንሷል።