'በመርፌ ቀዳዳ ማለፍ የሚችለው የእጅ ቦርሳ' በ3.4 ሚሊዮን ብር ተሸጠ

ትንሹ ቦርሳ

የፎቶው ባለመብት, MSCHF

እጅግ በጣም ደቃቅ፤ ከጤፍ ፍሬ ያነሰ መጠን ያለው ‘የእጅ ቦርሳ’ ለጨረታ ቀርቦ በ63ሺህ 750 ዶላር ተሸጠ።

ይህ ገንዘብ አሁን ባለው የውጭ ምንዛሪ ቢሰላ ከ3.4 ሚሊዮን ብር በላይ ይወጣዋል።

'የእጅ ቦርሳውን' ለማየት ማይክሮስኮፕ የሚያስፈልገው ይህን ቦርሳ መጠኑ 657x222x700 ማይክሮሚትር ነው ተብሏል።

ቦርሳውን ለገበያ ያቀረበው ኩባንያ “በመርፌ ቀዳዳ ማለፍ የሚችለውን ይህን አስተኛ ቦርሳ ለማየት ማይክሮስኮፕ ያስፈልግዎታል” ብሏል።

ኤምኤስሲኤችኤፍ የሚለው ኩባንያ ከዚህ ቀደምም ብዙ አነጋጋሪ የሆኑ ምርቶችን ዲዛይን አድርጎ ለገበያ በማቅረብ ይታወቃል።

የጥበብ ሥራዎችን በመሰብሰብ የሚታወቀው ኤምኤስሲኤችኤፍ ከዚህ ቀደም ካስተዋወቃቸው ምርቶች መካከል የሰው ልጅ ደም ያለበት ጫማ፣ በሶሉ ውስጥ ጸበል ያለበት የስፖርት ጫማ እና እጅግ ትልቅ ከጎማ የተሰራ ቦት ጫማ ይገኙበታል።

አሁን ላይ ደግሞ ይህ ኩባንያ እጅግ በጣም ደቃቅ የሆነውን የእጅ ቦርሳ ሰርቶ ለጨረታ አቅርቧል።

ትንሹ ቦርሳ

የፎቶው ባለመብት, MSCHF

“ትልቅ፣ መካከለኛ እና ትንሽ የእጅ ቦርሳዎች አሉ። ይህ ግን የመጨረሻው ትንሹ ቦርሳ ነው” ብሏል ኩባንያ አዲሱን ምርቱን ሲገልጽ።

ቦርሳውን ለመስራት 3-ዲ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን ቦርሳው እየተሰራ ሳለ ናሙናዎች ለጥራት ቁጥጥር ሲጓጓዙ ከማነሳቸው የተነሳ የጠፉ እንዳሉ ተዘግቧል።

ቦርሳውን በ60ሺህ ዶላር የሚገዙ ደንበኞች የገዙትን ቦርሳ የሚመለከቱበት ማይክሮስኮፕ አብሮ ይመጣላቸዋል።