ቤንጃሚን ሜንዲ ‘ከ10 ሺህ ሴቶች ጋር ወሲብ ፈፅሚያለሁ’ ስለማለቱ ለፍርድ ቤት ተነገረ

ቤንጃሚን ሜንዲ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የማንቸስተር ሲቲው ተጫዋች አንዲት ወጣት ሴት ከደፈረ በኋኃ “አትጨነቂ ከ10 ሺህ ሴቶች ጋር ወሲብ ፈፅሚያለሁ” ስለማለቱ ለፍርድ ቤት ተነገረ።

የ28 ዓመቱ ሜንዲ ጥቅምት 2020 ቼሻየር በሚገኘው 4 ሚሊዮን ፓውንድ በሚያወጣ ልጥጥ መኖሪያ ቤቱ የ24 ዓመቷ ግለሰብ ላይ ጾታዊ ጥቃት ማድረሱ ተሰምቷል።

ተከሳሹ ከዚህም በተጨማሪ በወቅቱ ዕድሜዋ 29 ዓመት የሆነች ሴትን ለመድፈር በመሞከር ተከሷል።

ግለሰቧ አክላ ተከሳሹ ከሁለት ዓመት በፊት እሱ ቤት ሳለች ጥቃት እንዳደረሰባት ትናገራለች።

እግር ኳስ ተጫዋቹ በሁለቱ ግለሰቦች የቀረበቡትን ክሶች አልፈፀምኩም ሲል ያስተባብላል።

አሁን ቼስተር ክራውን ፍርድ ቤት ክሱን እየተከታተለ ይገኛል።

ከሕብረተሰቡ የተውጣጡ ስድስት ሴትና ስድስት ወንዶች የተካተቱበት ሸንጎ [ጁሪ] የቤንጃሚን ሜንዲ ጉዳይ እየተከታተሉ ይገኛሉ።

ዳኛ ስቴፈን ኤቨሬት ለሸንጎው ፈረንሳዊው ተጫዋች በሌሎች ሴቶች በቀረበበት ክስ ጥፋተኛ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

ነገር ግን በወቅቱ የነበረው ሸንጎ በተከሰሰበት የመድፈርና የመድፈር ሙከራ ጉዳይ ከስምምነት ሊደርስ ስላልቻለ ነው አሁን ፍርድ ቤት እንዲገኝ የሆነው።

ዳኛው፤ ሸንጎው ከባለፈው የፍርድ ሂደት ምንም ዓይነት ዝርዝር መረጃ እንዳያዩ አስጠንቅቀው፤ ፍርድ ቤት የሚቀርበው ማስረጃ ብቻ አይተው ውሳኔ እንዲሰጡ መክረዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቤንጃሚን አይና ኬሲ የተባሉት አቃቤ ሕግ ተጫዋቹ ለማንቸስተር ሲቲ እንሚጫወት ገልጠው በርካታ ጊዜ ቤቱ ውስጥ ድግስ እንደሚያዘጋጅ ተናግረዋል።

ሴትና ወንድ ጓደኞቹ እኒህን ፓርቲዎች እንደሚታደሙ አሳውቀው ሁለት ሴቶች ላይ ጥቃት ፈፅሟል ብለዋል።

“በአንድ ወቅት ከአንዲት ሴት ጋር በግዴታ ወሲብ ሊፈፅም ሞክሯል። በሌላ ጊዜ ደግሞ አንዲት ሴትን ከመኝታ ክፍሎቹ በአንዱ ደፍሯል።”

የመድፈር ሙከራ የተደረገባት የዩኬ ሴት ተማሪ ስትሆን ሜንዲ የተዋወቃት 2017 ባርሴሎና ውስጥ መሆኑን ፍርድ ቤቱ ሰምቷል።

በጓደኝነት ለአንድ ዓመት ከዘለቁ በኋላ ሴቷ ወደ ተከሳሽ ቤት በግብዣ መምጧተን፤ ነገር ግን ጠዋት ገላዋን ስትታጠብ ሜንዲ ሳይጋበዝ በግልገል ሱሪ “ስሜት ውስጥ ሆኖ” ወደሷ መምጣቱን ለፍርድ ቤቱ ተገልጿል።

ተጫዋቹ ሴቷን በግድ ይዞ ሊደፍራት ሲሞክር በተደጋጋሚ እንዲያቆም እየነገረችው እንደታገለችው ተነግሯል።

ሌላኛዋ ሴት ወደ እግር ኳስ ተጫዋቹ ቤት ከሌሎች ጓደኞቿ ጋር ተጋብዛ መምጣቷ ተሰምቷል።

ከሷሿ እንደምትለው ሜንዲ ምስጢር ያዘለ የግል ስልኳን ተቀብሎ ወደ መኝታ ቤቱ ያመራል፤ እሷም ስልኳን ፍለጋ ተከትላዋለች።

አቃቤ ሕጉ እንዳሉት ሜንዲ ሴቷን “ላይሽ ፈልጌ ነው” ብሎ ልብሷን እንድታወልቅ ነግሯታል።

ሴቷም እሱ እንዳላታ አድርጋ ነገር ግን በውስጥ ልብስ ብቻ ትቀራለች። ከዚያም ሜንዲ ስልኳን ወደ አልጋ ይወረውረዋል።

ሴቷ ስልኳን ለማንሳት ወደ አልጋው ስትሄድ ሜንዲ ተከትሏት ሄዶ ወሲብ ማድረግ እንደማትፈልግ እየነገረችው ደፍሯታል።

“ሜንዲ ‘አትጨነቂ። ከ10 ሺህ ሴቶች ጋር ወሲብ ፈፅሚያለሁ’ ብሏታል።”

እግር ኳስ ተጫዋቹ በተከሰሰባቸው ሁለቱም አጋጣሚዎች ወሲብ የፈፀመው በግዴታ ሳይሆን በውዴታ መሆኑን ለፖሊስ ተናግሮ ክሱን አስተባብሏል።

የፍርድ ሂደቱ እንደቀጠለ ነው።