የቤላሩሱ ሉካሼንኮ በሩሲያ ኒውክሌር መሳሪያ ልዋጋ እችላለሁ አሉ

አሌክሳንደር ሉኬሼንኮ
የምስሉ መግለጫ, አሌክሳንደር ሉካሼንኮ

የቤላሩሱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ የቫግነርን አመጽ አረጋግተው የቡድኑን መሪ የቭጌኒ ፕሪጎዢን በአገራቸው አስጠልለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ከጥቂት ጋዜጠኞች ጋር ቃለ ምልልስ ለማድረግ የቢቢሲን ዘጋቢ ጨምሮ ጋዜጠኞችን ወደ ሚንስክ ጋብዘዋል።

ከሳምናት በፊት የጤናቸው ጉዳይ አነጋጋሪ ሆኖ ነበር።

በቫግነር ቡድን እና ክሬምሊን መካከል የተደረሰው ስምምነት ፕሪጎዢን ከተዋጊዎቹ ጋር ቤላሩስ እንዲቆይ ነው። እስካሁን ግን ይህ አልሆነም።

“ዋናዎቹ የቫግነር ተዋጊዎች ከባኽሙት ከወጡ በኋላ ባሉበት ካምፕ ነው ያሉት። ፕሪጎዢን ደግሞ ወደ ሴንት ፒተርስፐርግ ከዚያም ወደ ሞስኮ አቅንቷል። ቤላሩስ የለም” ብለዋል ሉካሼንኮ።

ፕሪጎዢን ወደ ሞስኮ መጓዙ የቫግነርን እና የሞስኮን ስምምነት ያፈርሰው እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ ተጠይቀዋል።

እሳቸው በዚህ አይስማሙም።

ምናልባትም ለጋዜጠኞች ይፋ የማያደርጉት ውይይት ከመጋረጃ ጀርባ እየተካሄደ ይሆናል።

ከሚንስክ እና ሞስኮ ስለ አመጹ የሚሰሙ ዜናዎች ተመሳሳይ አይደሉም።

የሩሲያ ብሔራዊ ቴሌቭዥን ባለፈው ሳምንት ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ‘ጀግና’ ሆነው እንደወጡ ገልጿል።

ሉካሼንኮ ግን “ከዚህ ሁኔታ ማንም ጀግና ሆኖ የሚወጣ አይመስለኝም። ፕሪጎዢንም ይሁን ፑቲን እኔም ብሆን ጀግና የለም” ይላሉ።

“እንዲህ ያሉ ወታደራዊ ቡድኖች ስንፈጥር በአንክሮ መከታተል እንዳለብን ሁኔታው አስተምሮናል” ሲሉ አክለዋል።

ሌላው የንግግር ነጥብ የኒውክሌር መሣሪያ ጉዳይ ነው። ሩሲያ ወደ ቤላሩስ መሣሪያዎች እንደምታስገባ ገልጻለች።

ፕሬዝዳንቱ “መሣሪያዎቹን እንዳልጠቀም ፈጣሪ ይጠብቀን። ከመጠቀም ወደኋላ ግን አልልም” ሲሉ በቅርቡ አስተያየት ሰጥተዋል።

ፕሬዝዳንቱ አክለውም ተመሳሳይ አስተያየት ከጆ ባይደን ወይም ሪሺ ሱናክ ሊሰማ እንደሚችል ተናግረዋል።

“ጓደኛዬ ዢ ዢፒንግ እና ታላቅ ወንድሜ ፑቲንም ይሄንኑ ነው የሚሉት” ብለዋል።

መሣሪያው የሩሲያ ቢሆንም፣ ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን (ኔቶ) እና ሌሎችም የውጭ መሣሪያዎች መጠቀሟን በመግለጽ “ታዲያ እኔስ በሌላ ሰው መሣሪያ ብዋጋ ምን አለበት?” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።

አሌክሳንደር ሉካሼንኮ እና ቭላድሚር ፑቲን
የምስሉ መግለጫ, አሌክሳንደር ሉካሼንኮ እና ቭላድሚር ፑቲን

አሜሪካ፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና የአውሮፓ ኅብረት ሉካሼንኮ ሕጋዊ የቤላሩስ መሪ ናቸው ብለው አያምኑም።

እአአ በ2020 ቤላሩሳውያን አደባባይ ወጥተው መሪያቸውን የሕዝብ ድምጽ በመበዝበዝ ከሰዋል።

ተቃውሞውን መንግሥት አክስሞታል። ተቃዋሚ የመብት ተሟጋች ማሪያ ኮልሲንኮቫ ከታሰሩት አንዷ ናት።

ለምን ዘመዶቿና ጋዜጠኞች እንዲጎበኟት አልተፈቀደም በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ “ስለዚህ የማውቀው ነገር የለም” ብለው ነው የመለሱት።

በ2021 ከቢቢሲ ዘጋቢ ጋር ቃለ ምልልስ ሲያደርጉ የፖለቲካ እስረኞች 873 እንደነበሩና አሁን 1,500 እንደደረሱ በመጥቀስ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሻቸው “በወንጀለኛ መቅጫ ሕጋችን የፖለቲካ ወንጀሎችን መቅጫ አንቀጽ የለም” ነበር።

አንቀጹ የለም ማለት ሰዎች የፖለቲካ እስረኛ አይሆኑም ማለት እንዳልሆነ የቢቢሲ ዘጋቢ ሲጠቅስ፣ ፕሬዝዳንቱ “አንቀጽ ከሌላ እስረኞች የፖለቲካ እስረኞች ሊሆኑ አይችሉም። እንዴት ይሄ ይሆናል?” ብለዋል።