የትራምፕ ጉዳይ በሚታይበት ፍርድቤት አቅራቢያ ራሱን ያቃጠለው ግለሰብ ሕይወት አለፈ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ የማጭበርበር ክስ በሚታይበት ማንሃታን በሚገኘው ፍርድ ቤት አቅራቢያ ራሱን ያቃጠለው ግለሰብ ሕይወት አለፈ።
የ37 ዓመቱ ማክስዌል አዛሬሎ ተቀጣጣይ ፈሳሽ አርከፍክፎ ራሱን ከማቃጠሉ በፊት 'በሴራ የተሞሉ' በራሪ ወረቀቶችን በትኗል።
ይህ ክስተት ያጋጠመው የዶናልድ ትራምፕን ክስ ለመመልከት የሚሰሙ ዳኞች ምርጫ ከተጠናቀቀ በኋላ ነበር።
ትራምፕ የዳኞችን ምርጫ ለመታደም በሕንጻው ውስጥ የነበሩ ሲሆን ድርጊቱ በተፈፀመበት ወቅት ሕንጻውን ለቀው ወጥተዋል።
ግለሰቡ ለሕይወቱ አስጊ የሆነ ጉዳት ደርሶበት በሆስፒታል ሕክምና ሲደርግለት ቆይቶ በኋላ ላይ ሕይወቱ ማለፉን የአሜሪካው የቢቢሲ አጋር ሲቢኤስ ኒውስ አረጋግጧል።
የኒው ዮርክ ፖሊስም አዛሬሎ መሞቱ በሆስፒታሉ ባልደረቦች ቅዳሜ ጠዋት እንደተገለጸለት ኤንቢሲ ዘግቧል።
አዛሬሎ ራሱ ላይ እንዲህ ዓይነት ጭካኔ ለምን እንደፈፀመ ግልጽ አይደለም።
መርማሪዎች ክስተቱን አስመልክቶ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ በ911 የአደጋ ጊዜ የጥሪ ማዕከል ተደውሎላቸው አንድ ግለሰብ ራሱን ሊያቃጥል እንደሆነ እንደተነገራቸው ገልጸዋል።
አዛሬሎ ይኖርበት ከነበረው ፍሎሪዳ ወደ ኒው ዮርክ ያመራውም ባለፈው ሳምንት ነበር።
ግለሰቡ ከዚህ በፊት በኒው ዮርክ የሰራው ወንጀል እንደሌለ እና በፍሎሪዳ የሚኖሩ ቤተሰቦቹ ወደ ኒው ዮርክ ማቅናቱን እንደማያውቁም ተገልጿል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የኒው ዮርክ ፖሊስ አዛዥ ጀፍሪ ማድሬይ እንዳሉት አዛሬሎ ተቀጣጣይ ፈሳሽ እና በራሪ ወረቀቶችን ይዞ ወደ ሥፍራው ከማቅናቱ በፊት በአካባቢው በሚገኝ መናፈሻ ውስጥ ሲዘዋወር ነበር።
የበተናቸው በራሪ ወረቀቶች ፕሮፖጋንዳ ላይ የተመሰረቱ እንደሆኑ የገለጹት የፖሊስ አዛዡ፣ ‘የሴራ ይዘት' ያላቸው ናቸው ብለዋል።
በትራምፕ ችሎት ምክንያት በፍርድ ቤቱ አካባቢ በርካታ የፀጥታ አካላት የነበሩ ሲሆን የፖሊስ መኮንኖች እሳቱን ለማጥፋት ወደ መናፈሻው በፍጥነት ነበር ያመሩት።
በእሳት ክፉኛ የተቃጠለውን አዛሬሎን በማንሳት ወደ አካባቢው ወደሚገኝ የቃጠሎ ህክምና ማዕከል መወሰዱን ፖሊስ ገልጿል።
ሦስት የኒው ዮርክ ፖሊስ መኮንኖች እና አንድ የፍርድ ቤት ባለሥልጣን እሳቱን ለማጥፋት ሲሞክሩ ቀላል ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ጁሊ በርማን የተባሉ የዓይን ምስክር “ . . . ምንም ትርጉም የሚሰጥ አይደለም፤ ሁሉም ነገር በፍጥነት የሆነ ነበር። ምን እየተካሄደ እንዳለ ለማወቅ 20 ሰከንድ ፈጅቶብኛል” ሲሉ ለጋዜጠኞች ተናግረዋል።
ከአደጋው በኋላ መርማሪዎች በሥፍራው ተገኝተው ግለሰቡ ራሱን ከማቃጠሉ በፊት የበተናቸውን ወረቀቶች ሲሰበስቡ ታይተዋል።
መርማሪዎቹ የዓይን እማኞችን እያነጋገሩ ሲሆን ግለሰቡ ራሱን ከማቃጠሉ በፊት የተናገረው ነገር እንደሌለ ገልጸዋል።
በአሜሪካ ግለሰቦች ራሳቸውን ሲያቃጥሉ ይህ የመጀመሪያው አይደለም።
የካቲት ወር ላይ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ከሚገኘው የአስራኤል ኤምባሲ ፊት ለፊት አንድ የአሜሪካ የአየር ኃይል አባል ራሱን በእሳት ያቃጠለ ሲሆን በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ሕይወቱ ሊያልፍ ችሏል።












