ትራምፕ በማጭበርበር ክስ 354 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍሉ ተወሰነ

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Image
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ በማጭበርበር ክስ ለኒውዮርክ ግዛት 355 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ እንዲከፍሉ ተወሰነባቸው።
ትራምፕ ያላቸውን ንብረት በተመለከተ ለባንኮች ሐሰተኛ መረጃዎችን ሰጥተዋል የሚለውን ጨምሮ ሌሎች ክሶች ቀርበውባቸው ነበር።
ብያኔውን ያስተላለፉት ዳኛ አርተር ኢንጎሮን ከገንዘብ ቅጣቱ በተጨማሪም ትራምፕም ሆነ ድርጅታቸው ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት በኒውዮርክ ከሚገኙ የፋይናንስ ተቋማት ብድር እንዳይጠይቁ እንዲሁም በኒውዮርክ በሚገኙ ኩባንያዎቻቸው ዳይሬክተር ሆነው እንዳያገለግሉም እግድ አስተላልፈውባቸዋል።
ከሳቸው በተጨማሪም ሁለቱ ልጆቻቸው ኤሪክ ትራምፕ እና ዶናልድ ትራምፕ ጁኒየር በኒውዮርክ በሚገኙ በትራምፕ ድርጅቶች ላይ በሥራ ኃላፊነት እንዳይቀመጡም እግድ ተጥሎባቸዋል።
ትራምፕ ከቀረቡባቸው ክሶች መካከል ተደጋጋሚ ማጭበርበሮች፣ ሐሰተኛ የንግድ መዝገቦችን በማቅረብ፣ ሐሰተኛ የፋይናንስ ሪፖርቶችን በማቅረብ እና የኢንሹራንስ ማጭበርበር ክሶች ይገኙባቸዋል።
በተጨማሪም ትራምፕ እና ኩባንያቸው ለባንኮች እና ኢንሹራንስ ላይ ላይ ባቀረቡት ሪፖርት ላይ የትራምፕ ንብረት ላይ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበትን ያካተተ ተመን አቅርበዋል የሚልም ተካቶበታል።
በኒውዮርክ ሪል ስቴት ዘርፍ ከፍተኛ ኃብት ያፈሩት ትራምፕ በበኩላቸው በብያኔው ላይ ይግባኝ እንደሚጠይቁም ተናግረዋል።
“አንድ ጠማማ የኒውዮርክ ግዛት ዳኛ ምርጥ የሆነ ኩባንያ በመመስረቴ 350 ሚሊዮን ዶላር ቅጣት እንድከፍል ወስኗል” ሲሉ የተናገሩት የቀድሞው ፕሬዚዳንት ትራምፕ ውሳኔውን የፖለቲካ ሴራ ብለውታል።
“በእኔ እምነት ለአገሪቱ በጣም አሳዛኝ ቀን ነው” ብለዋል።
አርብ ዕለት ብያኔውን የሰጡት ዳኛ ኢንጎሮን ተከሳሹ ከዚህ ቀደምም የተከሰሱበትን ክስ በመጥቀስ “ከፍተኛ” የገንዘብ ቅጣት እስካልተቀጡ ድረስ “በማጭበርበር መንገዳቸው ሊቀጥሉ ይችላሉ” በማለትም በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች እንዲቀጡ የወሰኑበትን ምክንያት ጠቅሰዋል።
ትራምፕ በንግድ ዓለሙ ላይ የኮርፖሬሽን ሞት ተብሎ ከሚታወቀው የንግድ ፈቃዳቸው ከመሰረዝ ቅጣት ተርፈዋል።
ነገር ግን ኩባንያዎቸቸውን በተመለከተ ለመጪው ሦስት ዓመት ለፍርድ ቤቱ ሪፖርት የሚያደርግ ገለልተኛ ተቆጣጣሪ እንዲሁም ሌላ ዳይሬክተር እንዲቀጥሩም ተወስኖባቸዋል።ዳኛው በተጨማሪም ትራምፕ በማጭበርበር ካገኙት ትርፍ ላይ ወለድ እንዲከፍሉ የተወሰነባቸው ሲሆን ይህም ቅጣታቸውን ወደ 450 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ያደርገዋል።












