ባይደን ለሩሲያዊው ተቃዋሚ አሌክሲ ናቫልኒ ሞት ፑቲንን ተጠያቂ አደረጉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ለሩሲያዊው ተቃዋሚ አሌክሲ ናቫልኒ ሞት ፑቲን ተጠያቂ ስለመሆናቸው “ምንም ጥርጥር የለውም” ሲሉ ተናገሩ።
ከዋይት ሃውስ መግለጫ የሰጡት ባይደን አሜሪካ ሩሲያን ለመቅጣት “የተለያዩ አማራጮችን” እየተመለከተች ነው ብለዋል።
የፑቲንን አገዛዝ በሰላ በመተቸት የሚታወቀው የ47 ዓመቱ ናቫልኒ በአርክቲክ ሰርክ እስር ቤት ሕይወቱ ማለፉን የሩሲያ የማረሚያ ቤት አገልግሎት አስታውቋል።
ናቫልኒ በእስር በነበረበትም ወቅት በርካታ የአሜሪካ መንግሥት ባለስልጣናት እና ሕግ አውጪዎች ስጋታቸውን ሲገልጹም ነበር።
ተቃዋሚው እና የፑቲን ቀንደኛ ተቺ የሆነው ናቫልኒ በበርካቶች ፖለቲካዊ ነው ተብሎ በሚታመን ክስ የ19 ዓመት እስር ላይ ነበር።
ላለፉት አስርት ዓመታት ናቫልኒ እና ያቋቋመው የጸረ ሙስና ፋውንዴሽኑ ለሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን አገዛዝ ዋነኛ ተቃዋሚዎች ሆነው ቀጥለዋል።
ናቫልኒ አርብ ዕለት ለእግር እንቅስቃሴ ከወጣ በኋላ “ህመም ተሰምቶት ወዲያው ራሱን እንደሳተም” የሩሲያ ማረሚያ ቤት አገልግሎት ባወጣው መግለጫ አትቷል።
“የአደጋ ጊዜ የህክምና ባለሙያዎች እስረኛው መሞቱን አስታውቀዋል” ያለው መግለጫው “የሞቱ መንስዔም እየተጣራ ነው” ብሏል።
አርብ ከሰዓት በኋላ ከዋይት ሐውስ በቴሌቪዥን በተላለፈ መግለጫቸው ፕሬዚዳንት ባይደን እንደተናገሩት የአሜሪካ ባለስልጣናት ናቫልኒ የሞተበትን መንስዔ ትክክለኛ ሁኔታ እርግጠኛ ባይሆኑም “ፑቲን እና ወሮበሎቻቸው ያደረጉት ነገር” ስለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም ብለዋል።
“አምላክ አሌክሲ ናቫልኒን” ይባርክ ያሉት ባይደን “ድፍረቱ ፍጹም አይረሳም” ሲሉም አክለዋል።
የተቃዋሚው ሞት መንስዔ ከተረጋገጠ በኋላ የአሜሪካ መንግሥት ሩሲያን ለመቅጣት ተጨማሪ ማዕቀቦችን ወይም ሌሎች መንገዶችን እያሰቡ እንደሆነ የተጠየቁት ባይደን ዝርዝር መረጃዎችን ከመስጠት ተቆጥበዋል።
“በርካታ አማራጮችን እየተመለከትን ነው። አሁን የምለው ይህንን ብቻ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት ባይደን ባደረጉት አጭር ንግግር የሪፐብሊካን ሕግ አውጭዎች ዩክሬን ከሩሲያ ጋር በምታደርገው ጦርነት ዩክሬንን እንዲረዱ ጥሪ አቅርበዋል። “ታሪክ ይታዘበናል” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
“በዚህ ፈታኝ ወቅት ዩክሬንን አለመደገፍ የማይረሳ ይሆናል። አሁን መርዳት አለብን” ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሙኒክ የጸጥታ ጉባኤ ላይ ቀደም ብሎ ንግግር ያደረጉት ምክትል ፕሬዚዳንት ካማላ ሐሪስ በበኩላቸው ከተረጋገጠ የናቫልኒ ሞት የፕሬዚዳንት ፑቲን “ጭካኔ” “ተጨማሪ ማሳያ” ይሆናል ብለዋል።












