ኢራን ውስጥ በተቀሰቀሰ ተቃውሞ ቢያንስ 17 ሰዎች ተገድሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኢራን ባለፉት ዓመታት ከታዩት ከፍተኛ ነው በተባለለት የአደባባይ ተቃውሞ ምክንያት ቢያንስ 17 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።
ተቃውሞው የተቀሰቀሰው ሒጃብ አልለበሽም በሚል ፀጥታ ኃይሎች ድብደባ ተፈጽሞባት ለሞት በቅታለች በተባለችው ማህሳ አማኒ ምክንያት ነው።
ይህን ከፍተኛ ተቃውሞ ተከትሎ ፕሬዝዳንት ኢብራሂም ራይሲ በፖሊስ ቁጥጥር ስር እያለች ሕይወቷ ያለፈው ሴት ጉዳይ መመርመር አለበት ብለዋል።
በኒውዮርክ እየተካሄደ ባለው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንቱ በማህሳ አሚኒ ህልፈተ ሕይወት ዙሪያ ምዕራባውያን ግብዝነት አሳይተዋል ብለዋል።
አማኒ የሥነ ምግባር ደንብ አስከባሪ ፖሊሶች ሂጃብ ባለመልበስ ሕግን ጥሳለች በሚል በቁጥጥር ስር ካዋሏት ከሰዓታት በኋላ ሕይወቷ አልፏል።
ይህን ተከትሎ በተከሰተው ተቃውሞ እና አለመረጋጋት ነው የሰዎች ሕይወት የተቀጠፈው።
በሰሜን ምዕራብ በምትገኘው የሳቄዝ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ኩርዳዊቷ አሚኒ ራሷን ስታ ህክምና በምትከታተልበት የቴህራን በሆስፒታል ከሦስት ቀናት በኋላ ሕይወቷ አልፏል።
ወጣቷ እንዳልተደበደበች ራይሲ በድጋሚ አስታውቀዋል። የኢራን ፖሊስ “ድንገተኛ የልብ ድካም” አጋጥሟታል ነው ያለው።
ተቃዋሚዎች ግን ፖሊስ የአሚኒን ጭንቅላት በዱላ ከመደብደቡም ባለፈ ከመኪና ጋር አጋጭተዋታል በሚል ሪፖርቱን ውድቅ ያደርጋሉ።
ፕሬዚዳንቱ ተቃዋሚዎቹን “ግርግር” ተቀባይነት የለውም ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በዩናይትድ ኪንግደም እና በአሜሪካ በፖሊስ የተፈጸሙ ግድያዎችን በመጥቀስም የምዕራባውያን አገራትን እናን ከመክሰሳችሁ በፊት ራሳችሁን ተመልከቱ ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ በምዕራቡ ዓለም ላይ ጣታቸውን የቀሰሩት ዩናይትድ ስቴትስ በኢራን የሥነ ምግባር ፖሊሶች ላይ ማዕቀብ እንደሚጣል ካሳወቀች ከሰዓታት በኋላ ነው።
የዩናይትድ ስቴትስ ግምጃ ቤት ማዕቀቡ የሚጣለው በኢራን ሴቶች ላይ በደረሰው ጥቃት እና የተቃዋሚዎችን መብት በመጣሱ ነው ብሏል።
ከመንፈሳዊው መሪ አያቶላህ አሊ ካሜኒ ጋር የጠበቀ ግንኙነት ያለውና ለአሚኒ ቤተሰቦችም ሐዘኑን የገለጸው የኢራን አብዮታዊ ዘብ የፍትህ አካላት የተቃውሞውን ሂደት ለማስቆም በሚደረገው ጥረት “የውሸት ዜናዎችን እና አሉባልታዎችን የሚያሰራጩ” ለፍርድ እንዲያቀርቡ ጠይቋል።
ተቃውሞው ወደ 80 የሚጠጉ ከተሞችና መንደሮች ደርሷል። አንድ ግለሰብ ለቢቢሲ ፐርሺያን እንደተናገረችው ሰፈሯ የጦር ሜዳ መስሏል።
የአሚኒ አባት የሆኑት አምጃድ ከቢቢሲ ፐርሺያን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፊቷ እና እግሮቿን ከማየት ውጪ ሙሉ አካሏን በመገነዙ ለማየት በባለሥልጣናት እንዳልተፈቀደላቸው ተናግረዋል።
“እግሮቿ ላይ ቁስሎች ነበሩ” ያሉት አባት ዶክተሮች እንዲመረምሯቸው ቢጠይቁም ምላሽ አለማግኘቱን ተናግሯል።
ልጃቸው ቀደም ሲል የነበረ የጤና ችግሮች ነበረባት ሲሉ የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ እና የቴህራን የፎረንሲክ ህክምና ዳይሬክተር ያቀረቡትን ውጤትም ውድቅ አድርገዋል።
“ውሸታሞች ናቸው። ባለፉት 22 ዓታት ውስጥ ከጉንፋን ጋር ከተያያዙ ጥቂት ህመሞች በስተቀር ሆስፒታል ሄዳ አታውቅም” ብለዋል።
የመጀመሪያው ተቃውሞ የተካሄደው ከቀብር ሥነ ሥርዓቷ በኋላ ነው። ሴቶች ሒጃባቸውን በአየር ላይ እያውለበለቡ “ሞት ለአምባገነኑ” ሲሉ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች ወጥተዋል። ይህም ብዙ ጊዜ መንፈሳዊው መሪ አያቶላ አሊ ካሜኒ ላይ የሚያነጣጠር ተቃውሞ ነው።
ተቃውሞው በፍጥነት በመላ አገሪቱ መስፋፋት ከመጀመሩ በፊት በቴህራን በሚገኙ በርካታ ዩኒቨርሲቲዎች ተመሳሳይ ሰልፎች ተካሂደዋል።
የቢቢሲ ፐርሺያ ባልደረባ ሆነችው ራና ራሂምፑር “አሁን ብዙ ወንዶች ተቃውሞውን መቀላቀላቸውን አይተናል። በሒጃብ የተጀመረው ተቃውሞም ወደ ኢስላማዊ ሪፐብሊኩ አነጣጥሯል” ብላለች።
“ይህ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ካየናቸው የኢራን ኢስላማዊ አመራር ፈተናዎች ከባዱ ነው” ስትል ተናግራለች።
ግድያዎች የነበሩት አማኒ በምትኖርበት እና ኩርዶች መኖሪያ በሆነው ሰሜናዊ ምዕራብ ኢራን ነው።












