የሩሲያ ደጋፊው ፖለቲከኛ የዩክሬን ደጋፊ የሆነችው ስሎቫኪያ ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጡ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሩሲያ ደጋፊ የሆኑት ፒተር ፔሌግሪኒ፤ ዙዛና ካፑቶቫን በመተካት አዲሱ የስሎቫኪያ ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጡ።
48 ዓመቱ ፔልግሪኒ የምዕራባዊያን ደጋፊ የሆኑት ኢቫን ኮርኮክን 53 በመቶ በሆነ ድምፅ በመርታት ነው የስሎቫኪያ መሪ የሆኑት።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ለሩሲያ ጠንከር ያለ ድጋፍ እንዳላቸው ይነገራል።
የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሮበርት ፊኮም በተመሳሳይ የሩሲያ ደጋፊ ሲሆኑ የስሎቫኪያ ፓርላማ የሳቸውን ሐሳብ እንደሚያንፀባርቅ ይታመናል።
ፓርላማው፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እና አሁን ደግሞ የፕሬዝደንቱ ፅ/ቤት በሩሲያ ደጋፊ ፖለቲከኞች ተይዟል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ፊኮ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ስሎቫኪያ የዩክሬን ጠንካራ አጋር ነበረች።
ፊኮ ባለፈው ጥቅምት ወደ ሥልጣን ሲመጡ ለዩክሬን ሲደረግ የነበረው ድጋፍ እንዲቋረጥ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ፔግሪኒ አዲሱ የስሎቫኪያ ፕሬዝደንት ሆነው ተመረጡ ማለት ዩክሬን ከስሎቫኪያ የምታገኘው ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ተቋረጠ ማለት ነው።
ፊኮ ምዕራባዊያን ለዩክሬን የሚያደርጉት ወታደራዊ ድጋፍ እንዲቋረጥ፤ የሰላም ስምምነት እንዲደረስና የተኩስ አቁም እንዲደረግ በመጠየቅ ይታወቃሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን “ሰይጣናዊ ተደርገው ተስለዋል”፤ ዩከሬንን የኔቶ አባል ማድረግ ሶስተኛውን የዓለም ጦርነት እንደማወጅ ነው ሲሉ በቅርቡ ተናግረው ነበር።
አዲሱ ፕሬዝደንት ፔሌግሪኒ በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት ለሩሲያ የሚያደሉ ንግግሮች ሲያሰሙ ተደምጠዋል። አልፎም ተቀናቃኛቸው ኮርኮክ የስሎቫኪያ ወታደሮች ወደ ጦርነት ሜዳ እየሰደዱ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
በስሎቫኪያ ሕገ-መንግሥት መሠረት ፕሬዝደንቱ ይህን የማድረግ ሥልጣን የለውም።
ከአንድ ዓመት በፊት ስሎቫኪያ ሚግ-29 የተባለው የጦር አውሮፕላንን ለዩክሬን በድጋፍ መልክ ሰጥታ እንደነበር አይዘነጋም።
ፔሌግሪኒ የገዥው ፓርቲ ሊቀ-መንበር እና የፓርላማው አፈ-ጉባዔ ሆነው ሳለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፀረ-ሙስና ኮሚሽኑን ሲያፈርሱ ዝም ብለው ተመልክተዋል ተብለው ይወቀሳሉ።
አዲሱ የስሎቫኪያ መንግሥት ቀጣዩ እርምጃው የሀገሪቱን መገናኝ ብዙኃን በቁጥጥር ሥር ማድረግ ሊሆን ይችላል የሚል ስጋት ከተቃዋሚዎች ይነሳል።












