“አባቴ ሰው ገድሎ ይሆን?” የጋዜጠኛው ማስታወሻ

ሳውል ወርድስዎርዝ ከአባቱ ክርስቶፈር ጋር

የፎቶው ባለመብት, Saul Wordsworth

የምስሉ መግለጫ, ሳውል ወርድስዎርዝ ከአባቱ ክርስቶፈር ጋር

አያድርገውና የቅርብ የምትሉት ሰው ወይም አባታችሁ ሰው ገድሏል ብላችሁ ብትጠረጥሩ ምን ታደርጋላችሁ?

ለሰዎች ትናገራላችሁ? ወይስ ምሥጢሩን በውስጣችሁ ቀብራችሁ ታስቀሩታላችሁ?

እንግሊዛዊው ሳውል ወርድስዎርዝ ግን በአንድ ወቅት በብሪታንያ ታዋቂ ጋዜጠኛ የነበሩትን አባቱን ሰው ገድለው ይሆን ወይ? የሚለውን ጥርጣሬውን ለዓለም አጋርቷል።

በዚህም ላይ የሬድዮ ፕሮግራሞች (ፖድካስት) አዘጋጅቶበታል። በርካታ መጣጥፎችንም ተጽፈውበታል።

ይህ ሁሉ የሆነው አባቱ ከሞቱ ከ25 ዓመታት በኋላ ነው።

አባቱ ከከፋ ምሥጢራቸው ጋር ወደ መቃብር ወርደዋል ለሚለውም ጥርጣሬ መነሻ የሆነው የራሳቸው የጋዜጠኛው አባቱ ማስታወሻዎች ናቸው።

አባቱ ቁጡ፣ እንደ እሳት የሚንቀለቀል ንዴት ቢኖርባቸውም በግድያ ግን አልጠረጠራቸውም።

በእጃቸው የተጻፉ ማስታወሻዎችን እየገለበጠች የነበረችም ሴት ናት መጀመሪያ ላይ “አባትህ አንድ ሰው የገደለ ይመስለኛል” ያለችው።

እየገለበጠችው ከነበረውም ማስታወሻ ላይ አስከሬን መደበቃቸውን የሚጠቅስ መስመር አለ።

ፍንጭ ይሆን? ሳውል እርግጠኛ አልነበረም። የተፈጠረ፣ ልብወለድ ታሪክም መሰለው።

በልጅነቱም አባትየው ይነግሩት የነበረው ታሪክ የተጋነነ እንደሆነም በማስታወስም እውነት ላይሆን ይችላል አለ።

ክርስተቶፈር ወርድስወርዝ እስከ ዘጠናዎቹ ድረስ ለኦብዘርቨር እና ጋርዲያን መጽሔቶች በየሳምንቱ የሚጽፉ ጋዜጠኛ ነበሩ።

ለሥነ ጽሑፍ ጥልቅ ፍቅር የነበራቸው ክርሰቶፈር ተደናቂነትን ያተረፈ ሃያሲም ነበሩ።

በእነዚህ መጽሔቶች ልብወለዶችን የሚገመግሙበት፣ ወንጀሎችን እንዲሁም የሕንድ እና የብሪታንያ ሕይወት ላይ ያጠነጠኑ ሥራዎቻቸው ተወዳጅነት ነበራቸው። ስፖርትንም አጥብቀው የሚወዱት ክርስቶፈር ክሪኬት እና ራግቢንም በተመለከተ ሪፖርት ሲያደርጉ በነገር ሸንቆጥ ያደረጉ ነበር።

ሆኖም ከእነዚህ ሁሉ ስኬቶታቸው በተቃራኒ ሳውል የአባቱንም ያልተሳካ የሕይወት ዘመን ምኞታቸውንም ያውቃል።

ሙሉ ሕይወታቸውን ሲያሰቃያቸው የነበረ፣ መጨረሻም ላይ ሳይሳካ የቀረ ታላቅ ልብወለድ የመጻፍ ታሪካቸውንም እሱ ብቻ ሳይሆን አጠገባቸው የነበሩ ሁሉ የሚያውቁት ነው።

ሳውል ወርድስዎርዝ

የፎቶው ባለመብት, Saul Wordsworth

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እናም ይህንን ሁሉ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለአስርት ዓመታት የተደበቀው ምሥጢርን ለማወቅ አጥብቆ ባይሞክርም ምን ይሆን የሚለውን ለማወቅ ጉጉት ማሳደሩ አልቀረም።

ሌሎች እንዲሁ ወንጀሉ ተፈጽሟል ሊያስብሉ የሚባሉ ዓረፍተ ነገሮችም እንዲሁ በማስታወሻዎቹ ተካትተዋል። ለምሳሌም ያህል “እኔን የሚያሳፍረኝ ስሌቴ ነው፤ ግድያ የሚያደርገው ይሄው ነው” ይላል።

የ51 ዓመቱ ሳውል አባቱ አንድ ሰው ቢገድሉ ጉዳዩን ለመጻፍ ይደፍሩ ይሆን? ወይስ ሳያስቡት ገድለው ይሆን? የሚሉ ሃሳቦች ይመላለሱበት ነበር።

የአባቱን ማስታወሻዎች እውነታውን ከልብወለድ ለመለየት በመሞከርም ‘ዴቪል ኢን ዘ ዋይልደርነስ’ (ዲያብሎስ በምድረ በዳ) በሚል ስድስት ክፍል ባለው ፖድካስትም አቀረበው። ለፖድካስቱም የማጀቢያ ሙዚቃም አቀናበረ።

የአባቱን በዕድሜ የገፉ ጓደኞች፣ ዘመዶች፣ እንዲሁም የቀድሞ ባልደረቦችን በማናገርም አባቱ ምን ያህል ብሩህ አዕምሮ እንደነበራቸው እንዲሁም የተመሳቀለ እና የሚረብሽ ታሪክ ባለቤትነታቸውንም ማሳየት ቻለ።

“በዚህ ፖድካስት ትክክለኛ ማንነትህን ማሳየት ችያለሁ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፣ ለማንኛውም ግን አባ ይቅር በለኝ” ሲልም በመጀመሪያው ክፍል ሲደመጥ ይሰማል።

በአውሮፓውያኑ 1914 በኮልካታ የተወለዱት ክርስቶፈር ዕድሜያቸው ከገፋ በ50 ዓመታቸው ነው ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ የገቡት። ለቃላት የነበራቸው መሰጠትን በማየትም በርካቶች ታላቅ ፀሐፊ ሊሆኑ እንደሚችሉም ይገምቱ ነበር።

ሕይወታቸው ያለፈውም በ83 ዓመታቸው በ1998 በሚወዱት ወንበር ላይ የሚገመግሙትን መጽሐፍ እንደያዙ ነው። ለረጅም ዘመን ያሰቡትም ልብወለድ የመጻፍ ህልማቸውም ተቀበረ።

ሳውል ሲወለድ ክርስቶፈር 57 ዓመታቸው ነበር። ለሦስተኛ ትዳራቸውም ብቸኛ ልጅ ነው። ይሄም ትዳራቸው በጸብ የተሞላ ነበር።

ሳውል አባቱ ይመኙት የነበረ የልብወለድ ጽሁፋችውንም ማሳኪያቸው የቀረው ልጃቸው እንደሆነ ያስቡ ነበር። “ሳውል የምኖረው በአንተ ነው” ይሉትም እንደነበር ይነግሩት ነበር።

ለረጅም ጊዜም ይህንን ሸክምም ይዞ መኖሩም የጤና እክል ፈጥሮበትም ነበር።

አባት እና ልጅ በጋራ የሚጋሩት አንደኛው ለስፖርት ያላቸው ፍቅር ነው ክርስቶፈር ግን ሕይወታቸው በሙሉ እንቆቅልሽ ነበር።

“ስለ ሕይወቱ ሳይቀር በርካታ ነገሮችን ይፈጥር ነበር።”

“ስለ እሱ ምሥጢራዊ እና ብዙ ላይታወቁ የሚችሉ ነገሮች ነበሩት። እሱም ይህንን ይወደው ነበር” ይላል ሳውል ስለ አባቱ ሲያስታውስ።

የጋዜጠኛው ማስታወሻዎች

የፎቶው ባለመብት, Saul Wordsworth

አባቱ ከነገሩት የተጋነኑ ታሪኮች መካከል አንደኛው ሂትለር አሁንም በሕይወት አለ የሚለውን ታሪክም ያስታውሳል።

ይህም አባባላቸው ‘አለን ስቱብ፣ ናዚ ሃንተር’ የሚለውን አስቂኝ ልብወለዱን ለመጻፍ መነሻ ሆኖታል።

ይህንንም መጽሐፍ በማሳተም አባቱ ያልቋጩትን ህልማቸውን ማሳካት ቻለ።

ክርስቶፈር የጻፏቸው ማስታወሻዎች ከአውሮፓውያኑ 1953 እስከ 1963 ያለውን ጊዜ ይሸፍናል። በዚህ ወቅት በሰሜን ዌልስ ገጠራማ ቦታ በአንዲት ጎጆ ከባለቤታቸው ተፋትተው፣ ምንም ገንዘብ ሳይኖራቸው መጻፍ አቅቷቸው በነበረ ወቅት ያሰፈሩት ነው።

ሳውል ስለ ማስታወሻዎቹ ለዓመታት ቢያውቅ በአንድ ወቅት ነው ካሉበት ፈልጎ ለማንበብ የተነሳው። ማንበብ ሲጀምር ግን የእጅ ጽሁፋቸው አስቸጋሪ በመሆኑ ይህንን ለመገልበጥ ኤማ የምትባል ሴት ቀጠረ።

ኤማም ጽሑፎቹን መገልበጥ እንደምትችል ነገረችው። ከሳምንት በኋላም በአውሮፓውያኑ 1953 የጻፉት የመጀመሪያ ማስታወሻቸው ቅጂን አገኘ።

የክርስቶፈር ማስታወሻዎች አንድ ሰው በሕይወቱ ዝቅ ያለ እና የወረደበትን ደረጃ የሚያሳዩ ናቸው። “ገንዘብ፣ ቤት፣ ስም፣ ጓደኞች፣ ዘመዶች፣ ሁነኛ ሰዎች፣ ስኬት በለው ምንም የለኝም። በልብ ወለድም ውስጥ ቢሆን እንዲህ አይነት አወዳደቅን ማየት የሚቻል አይመስለኝም” ሲሉም ስለ ሕይወታቸው አስፍረዋል።

በሚቀጥሉት ስድስት ሳምንታት አራት ተጨማሪ ማስታወሻዎች በአጠቃላይ 60 ሺህ የሚጠጉ ቃላቶችን የያዙ ማስታወሻዎች ወጣቸው።

ሳውል “በጽሁፉ ጥራት አልተገረምኩም፤ ነገር ግን የቃላት አጣጣሉ፣ የሐረጎቹ ውበት፣ እንዲሁም ምን ያህል ቃላቶች ይታዘዙለት እንደነበር ማየቴ በጣም አስደነቀኝ” ብሏል።

“ነገር ግን መጻፍ ባለመቻሉ ራሱን እያሰቃየ እና እያወገዘ ነበር። ለእሱ መጻፍ ማለት ልብወለድ ማሳተም ብቻ ነበር” ይላል።

ሳውል ከእነዚህ ማስታወሻዎችም ስለ አባቱ ብዙ ነገር ተረዳ።

አባቱ የሦስት ዓመት ህጻን እያሉ ነበር ኦስዌስትሪ በምትባለው ከተማ ከዘመድ ጋር ትተውት ወላጆቹ ወደ ሕንድ የተመለሱት። ከዚያም አዳሪ ትምህርት ቤት ገቡ እንዲሁም ባይጨርሱትም ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ገብተው ነበር።

ክርስቶፈር ያገኙትን ከፍተኛ ውርስም አባክነው ከጓደኞቻቸው እና ከቤተሰቦቻቸውም ይለምኑ ነበር። እህታቸው በአንድ ወቅት ለመዝናናት ወደ ሌላ ስፍራ በሄደችበትም ወቅት ሳታውቅ ቤቷንም ለመሸጥ ሞክረዋል።

ጋዜጠኛው ክርስቶፈር ወርስዎርዝ

የፎቶው ባለመብት, Saul Wordsworth

ማስታሻዎቹ በምሥጢር የታጨቁ ናቸው። ከጓደኞቻቸው ሚስቶች ጋር እንዴት እንደወሰለቱ እንዲሁም ሌሎች ልጆች ሊኖሯቸውም እንደሚችልም ፍንጭ የሰጡ ናቸው።

ፈላስፋ እና የሂሳብ ሊቅ የነበረው በርትራንድ ራስል ልጅ የሆነችው ሱ ረስል ጋር የነበረውን የተመሰቃቀለ የአምስት ዓመት የፍቅር ግንኙነትም በዝርዝር በማስታወሻቸው ላይ ሰፍሯል።

ሳውል ስለ አባቱ ባህርይ ሲገልጽ “ለሰዎች ግድ የማይሰጠው”፣ “ራስ ወዳድ” እንዲሁም በግልጽ መጎዳቱ የሚታወቅ እና ተስፋ የቆረጠ ነበርም ይላል።

በማስታወሻ ውስጥ ከሰፈረው አንደኛው “በሕይወቴ ውስጥ ከማንኛውም ነገሮች በላይ ሁለት ክስተቶች እስረኛ አድርገውኛል። ነፍሰጡር የነበረችውን ጆአንን መምታቴ እንዲሁም በኢራቅ የተፈጠረችው ያች ቅጽበት” ይላል።

ምን ማለት ነው? የመጀመሪያው ግልጽ ነበር። የመጀመሪያ ሚስታቸውን መደብደባቸውን የሚያሳይ ነው። የኢራቁ ግን ምንድን ነው?

“ክርስቶፈር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት በሕንድ ጦር ውስጥ በማገልገል እያለ ሰው ገድሎ ይሆን?” ፣ ሳውል የሚጠይቀው ጥያቄ ነው።

“በኢራቅ በዚያች ቅጽበት ምን ተፈጠረ? ስለሚለው ነገር ምንም ነገር የለም፤ እናም ሆን ተብሎ የተደረገ ይመስለኛል” ይላል ሳውል።

ጋዜጠኛው ክርስቶፈር ወርስዎርዝ ከጓደኞቹ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Saul Wordsworth

“ስለ ክስተቱ በዝርዝር ቢያወራ እና ምናልባት ማስታወሻው ሲገኝ ተጠያቂ እሆናለሁ ብሎ ስለፈራ ይመስለኛል” ሲልም መላምቱን ያስቀምጣል።

ሳውል የሕንድ የጦር መዛግብትን በመመርመር እንዲሁም የአባቱን የቀሩ ጓደኞችንም ጠይቋል።

ሳውል ካናገራቸው የአባቱ ጓደኞች መካከል በ90ቹ የዕድሜ አጋማሽ ላይ የነበረችው ኤሌኖር ብሩክስ አንዷ ናቸው። እሳቸውም “በእርግጥ ከእሱ ጋር እንዳይገናኝ የፈራው ጉዳይ ሊኖር ይችል ይሆን” ብለው መናገራቸውን ሳውል ያስረዳል።

ሳውልም ወደ ልጅነቱ ተመልሶ ሲያስብ አባቱ ተቀምጠው እጃቸውን ራሳቸው ላይ ጭነው በጨለምተኛነት ስሜት ውስጥ ብዙ ጊዜ አግኝቷቸዋል።

“ብዙውን ጊዜ ስለባከነ ወጣትነት ያወራ ነበር። ስለማይመለሱ ወቅቶች ያወራል። እናም በህሊናው ላይ ከባድ ሸክም የተጫነው ሰው እንደሆነ ይሰማኛል” ይላል።

ሳውል በተጨማሪም አባቱ ሰክሮ በመኪና አንድ ሰው ገድሎ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ አለው።

ጋዜጠኛው ክርስቶፈር ወርስዎርዝ

የፎቶው ባለመብት, Saul Wordsworth

ሳውል በፖድካስቱ ላይ የራሱ መደምደሚያ ላይ ሲደርስ ይሰማል። ነገር ግን ያልተመለሱ ጥያቄዎች አሉ እናም ተጨማሪ ምርመራዎችን ለማድረግም አቅዷል።

ከባድ ርዕሰ ጉዳይ ቢሆንም ለሳውል ይህንን ፖድካስት መሥራት አርኪ እና “በጣም አስደሳች ተሞክሮ” እንደሆነ ይናገራል።

ምንም እንኳን ያነሳቸው በርካታ ጉዳዮች አባቱን በመጥፎነት ቢያሳዩዋቸውም ሳውል አባቱን አያወግዛቸውም እንዲሁም አይኮንናቸውም።

“እኔ እንደማስበው መጥፎ ባህርያት ቢኖሩበትም ጭራቅ ነው ብዬ አላስብም። ቆስሎ እንደሚራመድ ሰው ነው” በማለትም ያስረዳል።

አክሎም “በእሱ ለተሰቃዩ ማንኛውም ሰው ርህራሄ አለኝ” ብሏል።

ከእነዚህም መካከል ሳውል በአባቱ የሚዛመዱት ወንድሞቹ እና እህቶቹ ናቸው።

አባቱ ምንም ሳያያቸው እና ድጋፍ ሳያደርግላቸው ማደጋቸው ጋር ተያይዞ “ይቅር የማይባል ስህተት ነው” ይላል ሳውል።

አባቱ ከሞቱ ከ25 ዓመታት በኋላ እውን የሆነው ፖድካስት አቀራርቧቸው ይሆን?

“ቅርብ ቢሆንም እንደቀድሞው በጣም ሩቅም ነው” ሲልም ሳውል ምላሹን ይሰጣል።

“በመጨረሻ የሁላችንንም ማንነት አይታወቅም። ነገር ግን አንዳንዶች ደግሞ ልክ እንደ አባቴ ማንነታቸው የማይታወቁ ጥቂት ሰዎች አሉ” ብሏል።

ሳውል ወርድስዎርዝ ከአባቱ ክርስቶፈር ጋር

የፎቶው ባለመብት, Saul Wordsworth