ሩሲያ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ማበረታት የሚከለክለውን ህጓን በድጋሚ አራዘመች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሩስያ የታችኛው ምክር ቤት ማንኛውንም የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነቶች ማበረታታት የሚከለክለውን ህግ በድጋሚ እንዲራዘም ወሰነ።
ተሻሽሎ በቀረበው በዚህ ህግ ላይ ማንኛውንም የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን የሚያስተዋውቁ መጽሃፍትን፣ ፊልሞችን እንዲሁም በኢንተርኔት ላይ ያሉ ይዘቶች ከባድ ቅጣት ያስከትላል።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን “ሐሳብን በነጻነት የመግለፅ መብትን የሚጥስ” በማለት መተቸታቸውን ተከትሎም ህጉ “ለብሊንከን መልስ” የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቶታል።
በዘርፉ ያሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች የሩሲያን የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪን ማህበረሰብን ለመጨቆን የተደረገ ተጨማሪ እርምጃ ነው ሲሉ ተችተውታል።
ህጉ ዱማ በተሰኘው የሩሲያ የታችኛው ምክር ቤት ያለ ምንም ድምጸ ተአቅቦ በ397 ድምጽ ጸድቋል።
ህጉ በላይኛው ምክር ቤት ውስጥ ማለፍና በፕሬዳንት ቭላድሚር ፑቲን መፈረም አለበት።
ነገር ግን ይህ ሂደት በአብዛኛው እንደ አስተዳደራዊ እርምጃ ነው የሚታየው።
አወዛጋቢው “የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ፕሮፓጋንዳ” ህግ የጸደቀው በአውሮፖውያኑ 2013 ነበር።
ባህላዊ ያልሆኑ ግንኙነቶችን እንደ ተመሳሳይ ጾታ ግንኙነቶችና በልጆች መካከል ማንኛውንም ማስታወቂያና ምስሎች ማሳየት የሚከለክል ነው።
የተመሳሳይ ጾታዊ ግንኙነቶችን በአዎንታዊ መልኩ በየትኛውም ሚዲያ ያስተዋወቀ የወሲብ ቪዲዮችን እንዳሰራጨ፣ ሁከቶችን እንዲሁም የዘር እና የሃይማኖት ጥቃቶችን እንዳደረሰ ነው የሚቆጠረው።
በዚህም መሰረት የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን በበጎ መልኩ የሚያሳዩ መጽሃፎች እና ፊልሞች ይታገዳሉ።
ይህም ሁኔታ የሩሲያ ጥንታዊ ስነጽሁፍን ሊጎዳ ይችላል ሲሉ ተሟጋቾች ስጋታቸውን አንስተዋል።
ስለ ተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት የሚናገሩ የትኞቹም የኢንተርኔት ክርክሮች ይታገዳሉ እንዲሁም የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነትን የሚያመላክቱ ምልክቶችም ሆኑ መፈክሮች ይከለከላሉ።
እነዚህን ህጎች የጣሰ ማንኛውም ሰው 400 ሺህ ሩብል (6ሺህ 60 ዶላር) ቅጣት የሚጠብቀው ሲሆን ኩባንያዎች ደግሞ 5 ሚሊዮን ሩብል (82 ሺህ 100 ዶላር) ቅጣት ተጥሎባቸዋል።












