የመንግሥታቱ ድርጅት መርማሪ ኮሚሽን ጉብኝትን ተከትሎ የተነሱ ጉዳዮች

ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ፣ ስቲቨን ራትነር እና ራዲካ ኩማራስዋሚ

የፎቶው ባለመብት, fb

የምስሉ መግለጫ, ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ፣ ስቲቨን ራትነር እና ራዲካ ኩማራስዋሚ

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ያቋቋመው መርማሪ ኮሚሽን፣ ከሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን በተመለከተ ውይይት ለማድረግ አዲስ አበባ ይገኛል።

የሰብአዊ መብት ባለሙያዎችን የያዘው ኮሚሽን ከሐምሌ 18፣ 2014 ዓ. ም. እስከ ሐምሌ 24፣ 2014 ዓ. ም. በኢትዮጵያ ጉብኝት ያካሂዳል።

የተባበሩት መንግሥታት ይህንን ኮሚሽን ታኅሳስ ወር ላይ ካቋቋመው ወዲህ የኮሚሽኑ አባላት ወደ ኢትዮጵያ ሲያቀኑ የመጀመሪያቸው ነው።

ይህ ኮሚሽን በዋነኛነት በሰሜኑ ጦርነት ወቅት፣ በሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊ ወገኖች ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን፣ ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ድንጋጌ ጥሰቶችን እንዲሁም ዓለም አቀፍ የስደተኞች ሕግ ጥሰቶችን “በጥልቀት እና በገለልተኛነት” እንደሚመረምር ተመድ ያወጣው መግለጫ ይጠቁማል።

የኮሚሽኑ ሦስት ባለሙያዎች ኬንያዊቷ የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ፣ አሜሪካዊው ስቲቨን ራንተር እና ሲሪ ላንካዊቷ ራሲካ ኮማራስዋሚ ናቸው።

መርማሪ ኮሚሽኑ ወደ አዲስ አበባ ለመግባት ሀምሌ ላይ ከኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ እንደተሰጠው ይታወሳል።

የተመድ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ የጦር ወንጀሎችን እና የመብት ጥሰቶችን የሚመረምር ቡድን አባላትን የሰየመው በመጋቢት ነበር።

በወቀቱ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መርማሪ እንዲቋቋም የተላለፈውን ውሳኔ እንደማትቀበለውና “አንዳንዶች የሰብአዊ መብቶች ጉባዔን ለፖለቲካ ዓላማ ማራመጃነት ሲጠቀሙበት” ማየቷ እንዳሳዘናት ገልጻ ነበር።

የመርማሪ ኮሚሽን የማዋቀር እርምጃም በውስጥ ጉዳይዋ ለመግባት የሚደረግ ሙከራ መሆኑን በመጥቀስ እንደማትቀበለውና እንደማትተባበርም መግለጿ አይዘነጋም።

ግንቦት ላይ ግን የኮሚሽኑ አባላት ከኢትዮጵያ የፍትሕ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተው ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ፈቃድ ተሰጥቷቸዋል።

ኮሚሽኑ ለውይይት ወደ ኢትዮጵያ እንዲያቀና የተፈቀደው “ከኮሚሽኑ ጋር በምን መንገድ መተባበር የሚቻልባቸው መንገዶችን ለማጤን” እንደሆነ ተገልጿል።

የምርመራ ኮሚሽኑ የአዲስ አበባውን ውይይት ተከትሎ ጥቃት ወደተፈጸመባቸው አካባቢዎች ለመጓዝ እንዲሁም ከዓይን እማኞችና ከተጎጂዎች ጋር ለመነጋገር ፈቃድ እንደሚሰጠው ይጠብቃል።

የፌደራል መንግሥቱ ስለ ኮሚሽኑ ምን አለ?

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ኮሚሽኑ የተቋቋመው፣ በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን እና በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) አማካይነት የመብት ጥሰቶችና ወንጀሎች ምርመራ ከተደረገባቸው በኋላ በመሆኑ በኢትዮጵያ መንግሥት በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ነበረ።

የኢትዮጵያ መንግሥት፣ ኮሚሽኑ የተቋቋመበት ሂደት እና የተሰጠው ኃላፊነት “ግልፅነት የጎደለውና ፖለቲካዊ ዓላማን ያነገበ” ነው በሚል እንደማይቀበለውና በምርመራው እንደማይተባበር በይፋ አሳውቆ ነበር።

ነገር ግን የኢትዮጵያ መንግሥት እና የመንግሥታቱ ድርጅት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስዊዘርላንድ፣ ጄኔቭ ላይ ካደረጉት ውይይት በኋላ ኢትዮጵያ ከመርማሪ ኮሚሽኑ ጋር እንደምትተባበር በመግለጿ፣ ባለሙያዎች ውይይት ለማድረግ ለአንድ ሳምንት ያህል ለመቆየት ከትላንት ጀምሮ አዲስ አባባ ይገኛሉ።

የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ከኮሚሽኑ አባላት ጉብኝት ጋር በተያያዘ ባወጣው መግለጫ፣ ኮሚሽኑ የሚያከናውናቸው ተግባራት “የመንግሥትን መሠረታዊ አቋም ያገናዘበ፣ የዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ሥርዓትና የብሔራዊ ሕግ ሥርዓቱ ደጋፊና ሟሟያ ሆኖ መታየት ያለበት እንዲሁም የአሟይነት መርኅን ያከበረ” መሆን እንዳለበት አመልክቷል።

ጨምሮም፣ የኮሚሽኑ ሥራ ከፖለቲካ ፍላጎቶች የነጻ እንዲሁም የተመድ የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት እና ኢሰመኮ በጥምረት ያደረጉትን ምርመራ የማይደግም መሆን አለበት ብሏል።

መንግሥት በተደረገው ጥምር ምርመራ አማካይነት በተገኘው ውጤት መሠረት ተጠያቂነትን ለማስፈን እየወሰዳቸው ያሉ እርምጃዎችን በማያስተጓጉል መንገድ የተመድ ኮሚሽን የሚንቀሳቀስ ከሆነ እና “በዝርዝር የእንቅስቃሴ አቅጣጫዎች ማዕቀፍ ላይ መስማማት ከተቻለ ከኮሚሽኑ ጋር የመተባበርን ጉዳይ መልሶ የማጤን ዕድል እንደሚኖር” መገለጹን የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አክሏል።

የኮሚሽኑ አባላት ከአቶ ደመቀ መኮንን ጋር

የፎቶው ባለመብት, SM

በትግራይ በኩል ስለ ኮሚሽኑ ምን ተባለ?

የሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ ባለሙያዎች ወደ አዲስ አበባ የሚያደርጉትን ጉዞ በተመለከተ የትግራይ ባለሥልጣናት በውጭ ግንኙነት ጽሕፈት ቤት በኩል ያወጡት መግለጫ፣ ኮሚሽኑ ከትግራይ አመራሮች ጋር ለመገናኘት መዘግየቱ እንዳሰሰበው አመልክቶ “የትግራይ ሕዝብና መንግሥት በምርመራው ሂደት በአግባቡ ተሳታፊ መሆን አለባቸው” ብሏል።

በተባበሩት መንግሥታት እና በኢሰመኮ አማካይነት በተደረገው ምርመራ ላይ ያለውን ጥርጣሬ ያመለከተው መግለጫው፣ አሁንም መንግሥት የሚካሄደውን ምርመራ እራሱ በሚፈልገው መንገድ እንዲያመራ በማድረግ ተአማኒነቱን ሊያሳጠው ይችላል ሲል ስጋቱን ጠቅሷል።

ስለዚህም ኮሚሽኑ “ሥራው ላይ የነጻ እና ገለልተኝነት ጥያቄ እንዳይነሳበት ከመንግሥት በኩል ሙሉ ትብብር መጠየቅና ባለሥልጣናትም ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት እንዳይፈጽሙ መጠየቅ አለበት” ብሏል።

ሁለት ዓመት ሊሞላው ወራት በቀሩት ትግራይ ውስጥ ተቀስቅሶ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች በተዛመተው ጦርነት፣ መጠነ ሰፊ ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት በሁሉም ወገኖች መፈጸሙን በተባበሩት መንግሥታት እና በኢሰመኮ በጋራ በተደረገ ምርመራ እንዲሁም በበርካታ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ቡድኖች ሪፖርቶች መገለጹ ይታወሳል።

ኮሚሽኑ እንዴት ተቋቋመ?

ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን የሚያጣራ ዓለም አቀፍ መርማሪ አካል እንዲቋቋም የውሳኔ ሐሳብ የቀረበው በአውሮፓ ኅብረት የነበረ ሲሆን፤ የውሳኔ ሐሳቡን 21 አገራት ደግፈው፣ 15 አገራት ተቃውመውት፣ 11 አገራት ደግሞ ድምጸ ተአቅቦ አድርገውበት ፀድቋል።

በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ባወጣው መግለጫ ላይ የውሳኔ ሐሳቡን የተቃወመው ሲሆን፣ ከዚህ በፊት በመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት አማካይነት የተካሄደውን ምርመራ መሠረት በማድረግ እርምጃ እየወሰደ ባለበት ጊዜ ውሳኔው መተላለፉ "ፖለቲካዊ ፍላጎት" አለው ሲል ተቃውሞት ነበር።

ኮሚሽነሮቹ እነማን ናቸው?

ከምርመራ ኮሚሽኑ አባላት አንዷ ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ፣ በሽግግር የፍትሕ ሂደቶች የካበተ ሥራ ልምድ ያላቸው ናቸው።

በተጨማሪም በሴቶች ሰብአዊ መብቶች፣ በሥርዓተ ፆታ፣ በሕገ መንግሥት እና በአስተዳደር ሕጎች ላይ በርካታ ሥራዎችን አበርክተዋል።

በአሁኑ ጊዜ የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጠበቃ እና ተሟጋች የሆኑት ግለሰቧ፣ በአመፆችና በግጭቶች ውስጥ የሴቶችን ሰብአዊ መብት ከማስከበር ጋር በተያያዘ ሠርተዋል።

ሌላው የኮሚሽኑ አባል ስቲቨን ራትነር በአሁኑ ወቅት በሚቺጋን የሕግ ትምህርት ቤት የሕግ ፕሮፌሰር ናቸው።

ትምህርታቸውና ምርምራቸው በዓለም አቀፍ ሕግ፣ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግጋት፣ በፀረ ሽብርተኝነት ስልቶች፣ በሰብአዊ መብት ረገጣ ተጠያቂነት እና የውጭ ኢንቨስትመንትን በሚመለከት የድርጅት እና የመንግሥት ተግባራት ላይ ያተኩራል።

ሦስተኛዋ የምርመራ ኮሚሽኑ አባል ራዲካ ኩማራስዋሚ ቀደም ሲል የሲሪ ላንካ የሰብአዊ መብት ሊቀ መንበር ነበሩ።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቁ የሰብአዊ መብት ተሟጋች የሆኑት ራዲካ፣ ከአውሮፓውያኑ 1994 እስከ 2003 በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃትን አስመልክቶ የተባበሩት መንግሥታት ልዩ መልዕክተኛ ሆነው አገልግለዋል።