የቀድሞ የአይሲሲ አቃቤ ህግ በኢትዮጵያ ጦርነት የተፈጸሙ ጥሰቶችን የሚያጣራው ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሆነው ተሾሙ

ፋቱ ቤንሱዳ (ጋምቢያ)፣ ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ (ኬንያ)፣ስቲቨን ራትነር (አሜሪካ)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images/Kaari/Michigan University

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ የጦር ወንጀሎችን እና የመብት ጥሰቶችን የሚመረምር የምርመራ ቡድን አባላትን ሰየመ።

የቀድሞ የዓለም አቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት (International Criminal Court) ዐቃቤ ሕግ ፋቱ ቤንሱዳ በኢትዮጵያ ለሚሰማራው ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ሊቀመንበር አድርገው የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አምባሳደር ፌዴሪኮ ቪሊጋስ መሾማቸውንም ምክር ቤቱ የካቲት 23/2014 ዓ.ም ባወጣው መግለጫው አመልክቷል።

ከጋምቢያዊቷ ፋቱ ቤንሱዳ በተጨማሪ፣ ኬንያዊቷ ጠበቃና የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ እና በሚቺጋን የሕግ ትምህርት ቤት ፕሮፌሰር የሆኑት አሜሪካዊ ስቲቨን ራትነር በጦርነቱ ተፈፅመዋል ለተባሉ ዓለማቀፍ ወንጀሎች መርማሪ ቡድን አባላት ሆነው ተሾመዋል።

ሦስት አባላት ላሉት ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንም ፋቱ ቤንሱዳ በመሪነት ያገለግላሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በትግራይ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ተቀስቅሶ በአጎራባቾቹ አማራና አፋር ክልልሎች በተዛመተው የእርስ በርስ ጦርነት የተፈጸሙ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች፣ የስደተኛ ሕጎችና ሌሎች ጥሰቶችን የሚያጣራና ገለልተኛ ምርመራ የሚያካሂድ መርማሪ ቡድን ለማቋቋም የውሳኔ ሃሳብ ያሳለፈው ባለፈው ታኅሣሥ ወር ላይ ነበር።

በአውሮፓ ሕብረት ጠያቂነት በተካሄደው የምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ በሰብዓዊ ምክር ቤቶች ፕሬዚዳንት የሚሾሙ አባላትን የያዘ ዓለም አቀፍ ኮሚሽን ለማቋቋም ውሳኔ ላይ ደርሷል።

በወቀቱም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ መርማሪ እንዲቋቋም የተላለፈውን ውሳኔ እንደማትቀበለውና አንዳንዶች የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔን ለፖለቲካ ዓላማ ማራመጃነት ሲጠቀሙበት በድጋሚ ማየቷ እንዳሳዘናት በመግለፅ በውስጥ ጉዳይዋ ለመግባት የሚደረግ ሙከራን እንደማትቀበል፤ እንደማትተባበርም ገልጻ ነበር።

በተጨማሪም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንም (ኢሰመኮ) በበኩሉ የመንግሥታቱ ድርጅት ሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት በጦርነቱ ለተፈጸሙ የመብት ጥሰቶች አዲስ የመርማሪ ቡድን ለማቋቋም ማቀዱ እንዳሳሰበው ለድርጅቱ በላከው ደብዳቤ ላይ መግለጹ ይታወሳል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ምክር ቤት ባወጣው መግለጫ ሦስቱ የኮሚሽን አባላት ተፈጸሙ የተባሉ ጥሰቶች በተመለከተ ሁኔታዎችን ማጣራት፣ መረጃዎችን መሰብሰብና መጠበቅ እንዲሁም ተጠያቂ የሆኑ አካላትን መለየት ያስችል ዘንድ እንዲሁም ለወደፊቱም ቀጣይነት ባለው ሁኔታ ኃላፊነት ሊወስዱ የሚገባቸውንም አካላት ተጠያቂ ለማድረግ የሚያስችል ሥራ እንዲሰሩ ተጠይቀዋል።

በዚሁ 47 አባላት ባሉት ምክር ቤት ታኅሣሥ ላይ ባሳለፈው የውሳኔ ሃሳብ መሰረት ኮሚሽኑ የተመድ ሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ጽህፈት ቤት እና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን በጋራ የሰሩትን ሪፖርትን በማጠናከር ለኢትዮጵያ መንግሥት በቴክኒክ ድጋፍ ላይ ምክረ ሃሳቦችን እንዲያቀርብ አዟል። ይህም ተጠያቂነት ለማምጣትና እንዲሁም እርቅ ለማስፈንም ያስችል ዘንድ እንደሆነም ተጠቁሟል።

በግለሰብ ደረጃ የሚያገለግሉት እነዚህ ኮሚሽነሮች በመጪው ሰኔ/ሐምሌ በሚካሄደው የሰብዓዊ ምክር ቤቶች 50ኛው ጉባኤ ላይ የቃል ገለፃ እንዲያቀርቡ እና መስከረም/ጥቅምት ወር በሚካሄደው 51ኛው የምከር ቤቱም ጉባኤ የጽሁፍ ሪፖርት እንዲያቀርቡ ተጠይቀዋል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል።

በኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ያሉ ሁሉም ወገኖች በተለያየ ደረጃ እንደ ጦር ወንጀል ሊቆጠሩ የሚችሉ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ሕግና የስደተኛ ሕግ ጥሰቶችን መፈፀማቸውን የመብት ተቆርቋሪዎች ያወጧቸው ሪፖርቶች ያመለክታሉ።

ጥቂት ስለ ኮሚሽነሮቹ

ፋቱ ቤንሱዳ (ጋምቢያ)

የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ሆነው የተመረጡት ፋቱ ቤንሱዳ በዓለማቀፉ ወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) (International Criminal Court) በዐቃቤ ሕግነት ከአውሮፓውያኑ 2012 እስከ 2021 አገልግለዋል።

በዚህ የኃላፊነት ቦታ ከመቀመጣቸው በፊት በፍርድ ቤቱ ምክትል ዐቃቤ ሕግ ሆነውም ለዓመታት አገልግለዋል። ጋምቢያዊቷ ፋቱ አይሲሲን ከመቀላቀላቸው በፊት በሩዋንዳ ጉዳይ ለዓለም አቀፉ የወንጀል ገላጋይ በከፍተኛ ሕግ አማካሪነትና ጠበቃ በመሆን በታንዛኒያ አገልግለዋል።

በአገራቸው ጋምቢያም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና የፍትህ ሚኒስትርን ጨምሮ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ሰርተዋል። ለጋምቢያ ፕሬዚዳንት እና ካቢኔም ዋና የሕግ አማካሪ ሆነው ማገልገላቸውም የምክር ቤቱ መረጃ ያስረዳል።

ካሪ ቤቲ ሙሩንጊ (ኬንያ)

በሽግግር የፍትህ ሂደቶች የካበተ ሥራ ልምድ ያላቸው ካሪ ቤቲ በተጨማሪም በሴቶች ሰብአዊ መብቶች፣ በሥርዓተ-ፆታ፣ በሕገመንግስት እና በአስተዳደር ሕጎች ላይ በርካታ ሥራዎችን አበርክተዋል።

በአሁኑ ጊዜ የኬንያ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጠበቃ እና ተሟጋች የሆኑት ግለሰቧ በአመፆችና በግጭቶች ውስጥ የሴቶችን ሰብአዊ መብት ከማስከበር ጋር በተያያዙ ሥራዎች ላይ አተኩረዋል።

ከምክር ቤቱ ድረገፅ ባገኘነው መረጃ መሰረት ካሪ ቤቲ የኬንያ እውነት ፍትህ እና እርቅ ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር እና ኮሚሽነር ሆነው በአውሮፓውያኑ 2009 እሰከ 2010 ባለው ጊዜ አገልግለዋል።

በተጨማሪም በዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ለተጎጂዎች የትረስት ፈንድ የዳይሬክተሮች ቦርድ የአፍሪካ ተወካይ፣ በደቡብ ሱዳን የጋራ ክትትል እና ግምገማ ኮሚሽን ከፍተኛ የሽግግር የፍትህ አማካሪነት ሰርተዋል።

እንዲሁም በሰብዓዊ ምክር ቤቶች ምክር ቤት በተመሰረተው በወረራ ለተያዘው የፍልስጥኤም ግዛት ገለልተኛ የምርመራ ኮሚሽን አባልም ነበሩ።

ስቲቨን ራትነር (አሜሪካ)

ስቲቨን ራትነር በአሁኑ ወቅት በሚቺጋን የሕግ ትምህርት ቤት የሕግ ፕሮፌሰር ናቸው። ፕሮፌሰር ራትነር ትምህርታቸውና ምርምራቸውና ዓለም አቀፍ ሕግ፣ በዓለም አቀፍ የሰብአዊ ሕግጋት፣ የፀረ-ሽብርተኝነት ስልቶች፣ በሰብአዊ መብት ረገጣ ተጠያቂነት እና የውጭ ኢንቨስትመንትን በሚመለከት የድርጅት እና የመንግሥት ተግባራት ላይ ያተኩራል።

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጥላ ስር የካምቦዲያ ባለሙያዎች ቡድን እና በሲሪላንካ የተጠያቂነት የባለሙያዎች ቡድን አባል በመሆን አገልግለዋል።

በተጨማሪም ከአውሮፓውያኑ 2008-2009 ባለው ጊዜ ወቅት በጄኔቫ የዓለም አቀፍ ቀይ መስቀል ኮሚቴ የሕግ ክፍል ውስጥ ሰርተዋል።

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በዓለም አቀፍ ሕግ አማካሪ ኮሚቴ ውስጥ እና በተለያዩ የግልግል ዳኝነት ላይ የዓለም አቀፍ ኢንቨስትመንት ባለሙያም ሆነው መስራታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ጠቁሟል።