በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር እየተካሄደ ያለው ምንድን ነው?

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ባለፈው ሳምንት ኢትዮጵያና ሱዳን በሚዋሰኑበትና የይገባኛል ጥያቄ በቀረበባቸው የድንበር አካባቢዎች የተከሰተን ግጭት ተከትሎ በሁለቱ አገራት በኩል ውዝግብ ተፈጥሯል።
በዚህም ሳቢያ ሱዳን ተገደሉብኝ ባለቻቸው ወታደሮቿ ሳቢያ ወታደራዊና ዲፕሎማሲያዊ እርምጃን የወሰደች ሲሆን፣ ኢትዮጵያ በበኩሏ ክስተቱን ተመርምሮ መፍትሔ እንዲፈለግ ጥሪ አቅርባለች።
ይህ የድንበር ውዝግብ ያሳሰበው የአፍሪካ ኅብረት በሁለቱ አገራት መካከል የተፈጠረውን ውጥረት ለማርገብ ኢትዮጵያ እና ሱዳን እራሳቸውን ከየትኛውም እርምጃ እንዲቆጥቡና በውይይት መፈትሔ እንዲፈልጉ ጠይቋል።
የኅብረቱ ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሐማት በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር አካባቢ የተከሰተው ግጭት “በጣሙን እንዳሳሰባቸው” ዛሬ ረቡዕ ባወጡት መግለጫ ላይ አመልክተዋል።
ሱዳን በኢትዮጵያ ላይ ክስ ማቅረቧን ተከትሎ ሠራዊቷ በኢትዮጵያ በኩል ያሉ የድንበር አካባቢዎችን በከባድ መሳሪያ መደብደቡን የአካባቢው ባለሥልጣንና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ባለፈው ሳምንት በሱዳን ሠራዊት እና በአካባቢው ባሉ ሚሊሻዎች መካከል በተከሰተው ግጭት ሱዳን ሰባት ወታደሮቿ እንደተገደሉባት በመግለጽ በኢትዮጵያ ላይ ክስ መሰንዘሯ ይታወሳል።
ይህንንም ተከትሎ የሱዳን ጦር በአዋሳኝ አካባቢዎች ላይ በመድፍ፣ በሞርታር እና በሌሎች ከባድ መሳሪያዎች ለቀናት የዘለቀ ድብደባ መፈጸማቸውን በምዕራብ ጎንደር ዞን የምዕራብ አርማጨሆ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ አያና ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ነዋሪዎችም በተለይ ሰኞ ዕለት የተፈጸመው የከባድ መሳሪያ ድብደባ ጠንካራ እንደነበር ተናግረው ማክሰኞ ዕለትም እስከ ከሰዓትበኋላ ጥቃቱ መቀጠሉን ገልጸዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች ከሱዳን በኩል በሚተኮሱ ከባድ መሳሪያዎች ምክንያት ተደጋጋሚ ተኩስና ፍንዳታ መስማት ከጀመሩ አስከ ማክሰኞ ከሰዓት ድረስ ሦስት ቀን እንደሆናቸው አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ እና በሱዳን ድንበር አካባቢው ዳግም ውጥረቱ ያገረሸው ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ሰኔ 16/2014 ዓ.ም ተከስቷል በተባለው ግጭት ሰባት ወታደሮችና አንድ ሰላማዊ ሰው በኢትዮጵያ ኃይሎች እንደተገደሉበት በመግለጽ የሱዳን መንግሥት ከከሰሰ በኋላ ነው።
ከሱዳን ጋር በሚዋሰነውና ግጭቱ ያጋጠመበት ወረዳ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ደሳለኝ አያና እንደተናገሩት፣ የሱዳን ወታደሮች ከዚህ ቀደም በኃይል ከያዟቸው አካባቢዎች ባሻገር ወደ ኢትዮጵያ ግዛት በገቡበት ጊዜ ከወረዳው ሚሊሻዎች ጋር መታኮሳቸውንና ጉዳት መድረሱን ገልጸዋል።
የሱዳን መንግሥት ግን ግጭቱ በኢትዮጵያ ሠራዊት አማካይነት መፈጸሙንና በሱዳን ግዛት ውስጥ መከሰቱን በመግለጽ ነበር መግለጫ ያወጣው።
የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በበኩሉ የሱዳን ምርኮኞችን በአደባባይ ገድሏል በሚል ከሱዳን የቀረበበትን ክስ ውድቅ በማድረግ፣ ሠራዊቱ ግጭቱ በተከሰተበት ስፍራ እንዳልነበርና የኢትዮጵያን ግዛት ዘልቆ የገባው የሱዳን ኃይል ከአካባቢው ሚሊሻዎች ጋር መጋጨቱን ገልጿል።
አቶ ደሳለኝ እንደሚሉት መንግሥት የድንበር ችግሩ በንግግር ይፈታል ያለውና የሱዳን ኃይሎች ባለፈው ዓመት በኃይል ገፍተው የያዙት 30 ሺህ ሄክታር መሬትን አልፈው በገቡበት ጊዜ ነው ግጭት የተፈጠረው።
ጨምረውም በግጭቱ እሳቸው የሱዳን ወታደሮችን እየመሩ የመጡ ናቸው ያሏቸውን አራት “የህወሓት ተላላኪዎችን” ጨምሮ ሰባት ሰዎች መገደላቸውንና ከሚሊሻው በኩል ደግሞ አንድ ሰው መሞቱንና የቆሰሉም እንዳሉ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰኞ ዕለት በሱዳን በኩል ለተሰነዘረው ክስ በሰጠው ምላሽ፣ ግጭቱ የተከሰተው በህወሓት ድጋፍ የኢትዮጵያን ድንበርን አልፈው በገቡ የሱዳን መደበኛ ወታደሮች መሆኑን በመግለጽ የሱዳንን ክስ ውድቅ አድርጎታል።
ህወሓት በግጭቱ ውስጥ ተሳትፏል መባሉን የሚያስተባብል መግለጫ በማውጣት የቀረበበት ክስ መንግሥት የትኩረት አቅጣጫን ለማስቀየር ህወሓትን ተጠያቂ ማድረጉን በመግለጽ፣ በክስተቱ ውስጥ እንደሌለበት አመልክቷል።
ለረጅም ጊዜ ኢትዮጵያና በሱዳን የይገባኛል ጥያቄ ሲያነሱበት በነበረው የድንበር አካባቢ በተለያዩ ጊዜያት በሁለቱም ወገኖች በኩል ባሉ ታጣቂዎች አማካይነት አልፎ አልፎ ግጭት ሲያጋጥም የነበረ ሲሆን የአሁኑ ግን ለቀናት የዘለቀ ፍጥጫን አስከትሏል።
በድንበር አካባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችና የወረዳው አስተዳደር እንዳሉት ባለፈው ሳምንት የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ እስከ ማክሰኞከሰዓት በኋላ ድረስ ከሱዳን በኩል የከባድ መሳሪያ ጥቃት ሲፈጸም ቆይቷል።
በዚህም ሳቢያ ነዋሪዎች ግጭቱ ሊባባስ ይችላል የሚል ስጋት ያላቸው ሲሆን አንዳንዶችም በአቅራቢያ ወዳሉ አካባቢዎች የመሄድ ሃሳብ እንዳላቸው ገልጸዋል።
ባለፉት ሦስት ቀናት ተፈጸመ በተባለው የከባድ መሳሪያ ጥቃት በሰው ላይ ጉዳት አለመድረሱን የተናገሩት የምዕራብ አርማጨሆ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ አያና፣ የከባድ መሳሪያዎቹ በእርሻ ቦታዎችና የግብርና ካምፖች ላይ ጉዳት አድርሰዋል ብለዋል።
በተጨማሪም በጥቃቱ ምክንያት በነዋሪው ላይ በተፈጠረው ስጋት ሳቢያ ባለፉት ቀናት በእርሻ ማሳቸው ላይ የተለመደውን የዕለት ከዕለት ሥራቸውን ከማከናወን ተቆጥበዋል ብለዋል።
የከባድ መሳሪያ ጥቃቱ በርካታ የድንበር ቦታዎች ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ በአካባቢው ያለው የንግድና የሥራ እንቅስቃሴ መስተጓጎሉን የገለጹት ነዋሪዎች ሱዳንና ኢትዮጵያ የሚገናኙበት የድንበር ከተማ የሆነችው የገለባት መተላለፊያ መዘጋቱንም አስተዳዳሪው ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሱዳን ክስን ተከትሎ የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን በሁለቱ አገራት ወታደሮች መካከል ከሰኞ ወዲህ ጦርነት እየተካሄደ መሆኑን ሲዘግቡ የቆዩ ቢሆንም፣ አቶ ደሳለኝ ግን በአካባቢው ጦርነት እንዳልተካሄደ በመግለጽ ያለው ሁኔታ ከሱዳን በኩል የሚፈጸመው የከባድ መሳሪያ ጥቃት መሆኑን ተናግረዋል።
የሱዳን ጦር ኃይሎች ቃል አቀባይ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ጦር ሠራዊቱ እየተጠቀሰ የሱዳን ኃይሎች ወደ ደንበር መንቀሳቀሳቸውንና ከአል ፋሽካ አካባቢ የኢትዮጵያ ወታደሮች ስለመማረካቸው የሚወጡትን ዜናዎች ትክክል እንዳልሆኑ ገልጸዋል።
የሱዳን የሽግግር ሉዐላዊ ምክር ቤት ፕሬዝዳንትና የአገሪቱ ጦር ሠራዊት ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት ጄኔራል አብዱል ፋታህ አልቡርሃን ግጭቱን ተከትሎ ባለፈው ሰኞ ምሥራቃዊውን የአገሪቱን ክፍል በመጎብኘት ከነዋሪዎች እና ከሠራዊቱ ጋር መገናኘታቸውን የሱዳን ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ በሰሜን ኢትዮጵያ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ የሱዳን ወታደሮች አወዛጋቢ ቦታዎችን በኃይል ተቆጣጥረው የያዙ ሲሆን፣ ኢትዮጵያም ሱዳን ወታደሮቿን እንድታስወጣ እና ውይይት እንዲደረግ ስትጠይቅ ቆይታለች።
የአካባቢው አስተዳዳሪ እንደሚሉት በሁለቱ አገራት መካከል የይገባኛል ጥያቄ የሚነሳባት 10 ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን ሲሆን፣ በቁጥጥራቸው ውስጥ ያስገቡት ግን ወደ 30 ሺህ ሄክታር መሬት እንደሚሆን ገልጸዋል።
ከሱዳን ጋር በቅርበት የሚዋሰነው የምዕራብአርማጨሆ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ አያና ለቢቢሲ እንደተናገሩት የሱዳን ኃይሎች ስናር፣ ገላሉባን፣ ጎረደም፣ ታች እና ላይ አቦጠር እንዲሁም ሰላም በር የተባሉትን ቦታዎችን በቁጥጥር ስር አድርገው ቆይተዋል።
ሰፊና ለም በሆነው አወዛጋቢው አካባቢ በርካታ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች የነበሩ ሲሆን፣ የሱዳን ኃይሎች አካባቢውን ለቅቀው እንዲወጡአድርገዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሱዳን ወታደሮቿን ከያዙት ቦታ እንድታስወጣና ከዚህ ቀደም ሲደረግ የነበረው ድርድር እንዲቀጥልና መፍትሔ እንዲያገኝ ሲጠይቅ ቆይቷል።
ኢትዮጵያ እና ሱዳን ለዓመታት የቆየ የድንበር ኮሚሽን አቋቁመው የይገባኛል ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ሲወያዩ ቢቆይም ከመፍትሔ ሳይደርሱ ቆይተዋል።
ሱዳን ሠራዊቷን ከተያዙት ቦታዎች እንደማታስወጣ ያሳወቀች ሲሆን ኢትዮጵያ ደግሞ የሱዳን እርምጃ ወረራ መሆኑን በመግለጽ ድርድር ከመደረጉ በፊት ቦታው እንዲለቀቅ ጠይቃለች።












