ሱዳን በኢትዮጵያ ያሉትን አምባሳደሯን ወደ ካርቱም መጥራቷ ተነገረ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሱዳን በኢትዮጵያ ሠራዊት ተገድለውብኛል ባለቻቸው ወታደሮቿ ምክንያት ተቃውሞዋን ለመግለጽ በአዲስ አበባ የሚገኙትን መልዕክተኛዋን ወደ ካርቱም መጥራቷ ተዘገበ።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ሰኞ፣ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ዜጎቹ በሱዳን ግዛት ውስጥ ተይዘው ወደ ኢትዮጵያ ከተወሰዱ በኋላ ተገድለዋል በማለት ከሷል።
ይህንንም በማስመልከት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰኞ ከሰዓት በኋላ ባወጣው መግለጫ፣ ግጭቱ የተከሰተው በህወሓት ድጋፍ የኢትዮጵያን ድንበርን አልፈው በገቡ የሱዳን መደበኛ ወታደሮች መሆኑን በመግለጽ የሱዳንን ክስ አጣጥሎታል።
ሱዳን ግን ለክስተቱ ኢትዮጵያን ተጠያቂ በማድረግ ተቃውሞዋን ለመግለጽ አምባሳደሯን ከአዲስ አበባ ከመጥራቷ በተጨማሪ በካርቱም የኢትዮጵያን አምባሳደር መጠራታቸው ተገልጿል።
ሱዳን በአገሯ የሚገኙትን የኢትዮጵያን አምባሳደር የጠራችው በአወዛጋቢው ድንበር አካባቢ ተፈጽሟል ስላለችው የወታደሮቿ ግድያ ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ አመልክቷል።
እንዲሁም የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ስለ ክስተቱ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ይፋዊ ቅሬታውን ለማቅረብ እየተሰናዳ መሆኑንም ተጠቅሷል።
ሱዳን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት፣ ምርኮኛ የነበሩ ሰባት ወታደሮቿን እና አንድ ሲቪል ገድሏል ስትል በመከላከያ ኃይሏና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ክስ አቅርባለች።
የሱዳን መንግሥት በመገናኛ ብዙኃን ገጹ እንዳሰፈረው፣ አንድ ሲቪልን ጨምሮ ሰባት ወታደሮቹ በኢትዮጵያ መከላከያ ተገድለዋል ብሏል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ላይ፣ በሱዳን ሠራዊትና በአካባቢው ሚሊሻዎች መካከል በተከሰተው በዚህ ግጭት በጠፋው ህይወት የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሚያዝን ገልጾ ምርመራ እንደሚደረግም አመልክቷል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ይህ ክስተት በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የጠበቀ ግንኙነት ለማደናቀፍ ሆን ተብሎ የተቀነባበረ መሆኑን በማመልከት፣ የሱዳን መንግሥትም ሁኔታውን የበለጠ ከሚያባብስ እርምጃ እንደሚቆጠብ ተስፋ እንዳለው ገልጿል።
ትናንት ሰኔ 20 ቀን 2014 ዓ. ም. የሱዳን መከላከያ ኃይል ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ ወታደሮች ሱዳናውያኑን ከገደሉ በኋላ “አስክሬናቸውን ለሕዝብ በአደባባይ አሳይተዋል” ሲል ከስሷል።
የሱዳን መከላከያ አባላቱ በኢትዮጵያ ወታደሮች መገደላቸውን በገለጸበት መግለጫ “ለዚህ የክህደት ድርጊት ምላሽ እንሰጣለን” በማለት ዝቷል።
ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ በኩል ያሉ ሚሊሻዎችና በሱዳን ሠራዊት መካከል በተለያዩ ጊዜያት ባጋጠሙ ግጭቶች ምክንያት በሰውና በንበረት ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።
በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ለዓመታት ከዘለቀው የድንበር ግጭት ባሻገር በሕዳሴ ግድቡ ግንባታ የተነሳም ውጥረት ነግሦ ቆይቷል።
በአል-ፋሽጋ አካባቢ በተለያዩ ጊዜያት የሚነሱ ግጭቶች በተለያም ከሰሜኑ ጦርነት መነሳት ወዲህ መባባስ ታይቶበታል።
በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የትግራይን ጦርነት ሸሽተው በምሥራቃዊ ሱዳን ወደሚገኙ የስደተኞች መጠለያዎች መግባታቸው ይታወሳል።
ባለፈው ሳምንት በወጡ ዘገባዎች መሠረት፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን በሚዋሰኑበት የምዕራብ ጎንደሩ መተማ ከተማ ግጭቶች እንደነበሩ ተጠቁሟል።
በመተማ ከተማ በሚገኘው፣ ሽመት መገዱቃ በተባለው ቀበሌ፣ በሱዳን ታጣቂዎች ተፈጸመ በተባለ ጥቃት የአካባቢው አርሶ አደሮች የግበርና ሥራቸው እንደተስተጓጎለ መናገራቸው ተዘግቧል።
የአሜሪካ ድምጽ፣ የምዕራብ ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቢክስ ወርቄን ጠቅሶ ባወጣው ዘገባ፣ “በአንድ ዓመት ውስጥ በእርሻ ሥራ ላይ የተሰማሩ 246 ባለሀብቶች ሥራቸውን አቁመዋል” ብሏል።
ባለፈው ዓመት በትግራይ ጦርነት ሲጀመርና የኢትዮጵያ ሠራዊት አወዛጋቢውን አካባቢ ለቆ ሲወጣ የሱዳን ኃይሎች ቦታውን መቆጣጠራቸውን ተከትሎ ውዝግቡ ተባብሶ ቀጥሏል።
ሰፊና ለም በሆነው አወዛጋቢው አካባቢ በርካታ ኢትዮጵያውያን አርሶ አደሮች የነበሩ ሲሆን፣ የሱዳን ኃይሎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ አድርገዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ሱዳን ወታደሮቿን ከያዙት ቦታ እንድታስወጣና ከዚህ ቀደም ሲደረግ የነበረው ድርድር እንዲቀጥልና መፍትሔ እንዲያገኝ ሲጠይቅ ቆይቷል።
ኢትዮጵያ እና ሱዳን ለዓመታት የቆየ የድንበር ኮሚሽን አቋቁመው የይገባኛል ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ሲወያዩ ቢቆይም ከመፍትሔ ሳይደርሱ ቆይተዋል።
ሱዳን ሠራዊቷን ከተያዙት ቦታዎች እንደማታስወጣ ያሳወቀች ሲሆን ኢትዮጵያ ደግሞ የሱዳን እርምጃ ወረራ መሆኑን በመግለጽ ድርድር ከመደረጉ በፊት ቦታው እንዲለቀቅ ጠይቃለች።












