የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሱዳንን ምርኮኞች ገድሏል መባሉን አስተባበለ

የፎቶው ባለመብት, FDRE Defense Force
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የሱዳን ምርኮኞችን በአደባባይ ገድሏል በሚል የሱዳን ጦር ያወጣውን መግለጫ መሰረት የሌለው ነው ሲል ውድቅ አደረገ።
የመከላከያ ሠራዊት ግጭቱ በተነሳበት ስፍራ እንዳልነበርና የኢትዮጵያን ግዛት ዘልቆ ገብቷል ያለው የሱዳን ኃይል ከአካባቢው ሚሊሻዎች ጋር ተጋጭቷል ሲል ጦሩ ባወጣው መግለጫ አመልክቷል።
የሱዳን መከላከያ ኃይል ወደ ኢትዮጵያ ድንበር አልፎ በመግባት በስፍራው በነበሩ የኢትዮጵያ ሚሊሻዎች ላይ ጥቃት አድርሷል በማለት የመከላከያ ሠራዊት የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነን ዋቢ ያደረገው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።
የሠራዊቱ ባለሥልጣን በተጨማሪም በግጭቱ በሁለቱም ወገን በኩል ጉዳት መድረሱንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በአካባቢው ባልነበረበት ሁኔታ ምርኮኞችን ገድሏል በማለት የሱዳን ጦር መክሰሱ “ተቀባይነት የሌለውና መሰረተ ቢስ ነው” ብለዋል ኮሎኔል ጌትነት።
አክለውም በስፍራው ባይኖርም በአጠቃላይ ጦሩ ከዚህ ቀደም የምርኮኞችን አያያዝ በተመለከተም ሕግን በተከተለ መልኩ መፈጸም የሠራዊቱ መለያ ነው ብለዋል።
የደረሰውን ጥቃት በተመለከተ ማጣራት ለሚፈልግ ከሁለቱ አገራት መከላከያ ሠራዊት ተወካዮች የተውጣጣ ኮሚቴ በማዋቀር እንዲጣራ ትብብር ያደርጋል በማለት የሠራዊታቸውን አቋም ማሳወቃቸውን የኢዜአ በዘገባው አስነብቧል።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በትናንትናው ዕለት ሰኔ 20/2014 ዓ.ም ከሱዳን ግዛት የተወሰዱ ወታደሮቹ ወደ ኢትዮጵያ ከተወሰዱ በኋላ ተገድለዋል እንዲሁም አስከሬናቸው በአደባባይ እንዲታይ ተደርጓል ሲል ክስ አቅርቧል።
የመከላከያ ሠራዊቷ አባላት ነበሩ ያለቻቸው ሰባት ወታደሮችና አንድ ሲቪል መገደልንም በማስመልከት ምላሽ እንደምትሰጥ ሱዳን የገለፀች ሲሆን ስለ እርምጃው ምንም አልተባለም።
ይህንንም በማስመልከት የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰኞ ከሰዓት በኋላ ባወጣው መግለጫ፣ ግጭቱ የተከሰተው በህወሓት ድጋፍ የኢትዮጵያን ድንበርን አልፈው በገቡ የሱዳን መደበኛ ወታደሮች መሆኑን በመግለጽ የሱዳንን ክስ አጣጥሎታል።
ሱዳን ግን ለክስተቱ ኢትዮጵያን ተጠያቂ በማድረግ ተቃውሞዋን ለመግለጽ አምባሳደሯን ከአዲስ አበባ ከመጥራቷ በተጨማሪ በካርቱም የኢትዮጵያን አምባሳደር መጥራቷ ተገልጿል።
በኢትዮጵያ እና በሱዳን ኃይሎች መካከል ግጭቶች ባለፉት አስርት ዓመታት የተለመደ ቢሆንም በባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ግን እየተባባሰ መጥቷል።
ሁለቱ አገራት በጋራ ድንበራቸው አቅራቢያ ባለው አል ፋሻጋ ለም የእርሻ ቦታ ላይ የይገባኛል ጥያቄ ውጥረት ነግሷል።
በአውሮፓውያኑ 2008 በሁለቱ አገራት መካከል የተፈረመ ስምምነት ቢኖርም የሁለቱን አገራት ግጭት ማስቆም አልቻለም ።
ኢትዮጵያ እና ሱዳን በአባይ ወንዝ ላይ በሚገነባው ግዙፉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ላይም ውዝግብ ውስጥ ናቸው።












