ክርስቲያኖ ሮናልዶ የዓለማችን ቁጥር አንድ ከፍተኛ ተከፋይ ስፖርተኛ ሆነ

ክርስቲያኖ ሮናልዶ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በከፍተኛ ክፍያ ወደ ሳዑዲው አል ናስር ክለብ ያቀናው ክርስቲያኖ ሮናልዶ

ክርስቲያኖ ሮናልዶ ወደ ሳዑዲ አረቢያው የእግር ኳስ ቡድን አል ናስር ከተዘዋወረ በኋላ ከአውሮፓውያኑ 2017 ወዲህ በዓለም ከፍተኛ ገንዘብ የሚከፈለው ስፖርተኛ ሆነ።

የ38 ዓመቱ ፓርቱጋላዊ የእግር ኳስ ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ባለፉት 12 ወራት ውስጥ 136 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ ማግኘቱን ፎርብስ አመልክቷል።

ሮናልዶ ከሳዑዲው ቡድን አል ናስር ጋር በገባው ውል መሠረት በዓመት ከ200 ሚሊዮን ዶላር በላይ ያገኛል።

የዓለም ዋንጫ ባለድሉ የአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን አምበል የሆነው ሊዮኔል ሜሲ ደግሞ 130 ሚሊዮን ዶላር በማግኘት ሁለተኛው ከፍተኛ ተከፋይ ሆኗል።

ፎርብስ ይፋ ካደረጋቸው ከፍተኛ ተከፋይ 10 ስፖርተኞች መካከል የቅርጫት ኳስ ኮከቡ ለብሮን ጄምስ እና ቦክሰኛው ካኔሎ አልቫሬዝ የሚገኙበት ሲሆን፣ ለ20 ጊዜ የሜዳ ቴኒስ ሻምፒዮን የሆነው ሮጀር ፌደረር ደግሞ በዝርዝሩ ውስጥ 9ኛ ደረጃ ላይ በመቀመጥ ብቸኛው ጡረተኛ ስፖርተኛ ሆኗል።

አነጋጋሪ በሆነ ፍጥነት ከፍተኛ ክፍያ ከሚያገኙ ስፖርተኞች መካከል ጥቂት የማይባሉ የጎልፍ ተጫዋቾችም በስፖርት ባለጸጎች በዝርዝሩ ውስጥ ተካተዋል።

ፎርብስ በዝርዝሩ ውስጥ ያካተታቸው ከፍተኛ ገቢ የሚያገኙ ስፖርተኞች ከሚከፈላቸው ደሞዝ በተጨማሪ በሽልማት፣ በጉርሻ በስፖንሰርሽፕ እና በተለያዩ መንገዶች የሚያገኙትን ገቢም ያካትታል።

የፎርብስ ከፍተኛ ተከፋይ ስፖርተኞች

  • ክርስቲያኖ ሮናልዶ፣ እግር ኳስ ተጫዋች፣ ገቢው 136 ሚሊዮን ዶላር
  • ሊዮኔል ሜሲ፣ እግር ኳስ ተጫዋች፣ ገቢው 130 ሚሊዮን ዶላር
  • ኪሊያን ምባፔ፣ እግር ኳስ ተጫዋች፣ ገቢው 120 ሚሊዮን ዶላር
  • ለብሮም ጄምስ፣ የቅርጫት ኳስ ተጫዋች፣ ገቢው 119.5 ሚሊዮን ዶላር
  • ካኔሎ አልቫሬዝ፣ ቦክሰኛ፣ ገቢው 110 ሚሊዮን ዶላር
  • ደስቲን ጆንሰን፣ ጎልፍ ተጫዋች፣ ገቢው 107 ሚሊዮን ዶላር
  • ፊል ሚከልሰን፣ ጎልፍ ተጫዋች፣ ገቢው 106 ሚሊዮን ዶላር
  • ስቴፈን ከሪ፣ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች፣ ገቢው 100.4 ሚሊዮን ዶላር
  • ሮጀር ፌደረር፣ የሜዳ ቴኒስ ተጫዋች፣ ገቢው 95.1 ሚሊዮን ዶላር
  • ኬቪን ዱራንት፣ ቅርጫት ኳስ ተጫዋች፣ ገቢው 89.1 ሚሊዮን ዶላር