ሊዮኔል ሜሲ ወደ ሳዑዲ አረቢያ በመሄዱ በክለቡ ፓሪስ ሴን ዠርሜን ቅጣት ተጣለበት

ሜሲ ወደ ሳኡዲ የሄደው የአገሪቱ የቱሪዝም አምባሳደር በመሆኑ ነው
የምስሉ መግለጫ, ሜሲ ወደ ሳኡዲ የሄደው የአገሪቱ የቱሪዝም አምባሳደር በመሆኑ ነው

የአርጀንቲናው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ በክለቡ ፓሪስ ሴን ዠርሜን የሁለት ሳምንት እግድ ተጥሎበታል።

ቅጣቱ የተጣለበት ሜሲ ክለቡ ሳይፈቅድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ በመጓዙ ምክንያት ነው።

ሜሲ ቅጣቱ የሚጸናበት ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ሲሆን፣ በእነዚህ ጊዜያት ከየትኛውም የፒኤስጂ ልምምድ እና ጨዋታ ውጪ እንዲሆን ይደረጋል።

ሜሲ ወደ ሳዑዲ ያቀናው ክለቡን ፍቃድ ጠይቆ ከተከለከለ በኋላ ነበር።

ይህም የሆነው እሑድ በሜዳው በሎሪየንት 3 ለ l በሆነ ውጤት መሸነፉን ተከትሎ ነው። በዚያ ጨዋታ ሜሲ 90 ደቂቃ ተሰልፎ ተጫውቷል።

የ35 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ ወደ ሳዑዲ አረቢያ የተጓዘው የሳዑዲ የቱሪዝም አምባሳደር በመሆኑ ከሥራ ጋር በተያያዘ ነው ተብሏል።

የሳዑዲው የቱሪዝም ሚኒስትር አሕመድ አልካቲብ በትዊተር ገጻቸው ሜሲን “ወደ እንግዳ ተቀባይዋ ሳዑዲ እንኳን ደህና መጣህ ብዬ ስቀበል ላቅ ያለ ደስታ ይሰማኛል” ሲሉ ጽፈዋል።

የኳታርን ዓለም ዋንጫን ለአገሩ ብሔራዊ ቡድን ጋር በቅርቡ ያነሳው ሜሲ ከክለቡ ፒኤስጂ ጋር የሁለት ዓመት ኮንትራቱ የሚያበቃው በመጪው የፈረንጆቹ በጋ ላይ ይሆናል።

የባርሴሎና ምክትል ፕሬዝዳንት ራፋኤል ዩስቴ ከዚህ ቀደም እንደተናገሩት ደግሞ ክለባቸው ሜሲን ወደ ካምፕ ኑ ለመመለስ ንግግር ጀምሯል።

ሜሲ ከፒኤስጂ ጋር በነበረው ቆይታ 31 ጎሎችን ያስቆጠረ ሲሆን በ71 ጨዋታዎች 34 ግብ መሆን የቻሉ ኳሶችን ማቀበል ችሏል።

ከክለቡ ጋር አንድ ጊዜ ዋንጫን ማንሳትም ችሏል። ይህም የሆነው ባለፈው የውድድር ዘመን ነው።

ሜሲ ይህ ቅጣት ስለተጣለበት ክለቡ ፒኤስጂ በመጪው እሑድ እና በሚቀጥለው ቅዳሜ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ አይሰለፍም።

የቢቢሲው ስፖርት ዘጋቢ ሳይምን ስቶን እንደሚለው ከሆነ ሜሲ ፍቃድ ሳይሰጠው ወደ ሳዑዲ ጉዞ ማድረጉ ከፒኤስጂ ጋር የነበረው ቆይታ ማብቃቱን አመላካች ነው።

በእርግጥ ፓሪስ ሴን ዠርሜን ሜሲ ቅጣቱን ከጨረሰ በኋላ በሊጉ ገና ሦስት ጨዋታዎች ይቀሩታል።

ፒኤስጂ የዓለም ዋንጫውን ንጉሥ ሜሲን በዚህ ሁኔታ መቅጣታቸው ልዩ ነገር አድርገው አልተመለከቱትም ይላል ሳይመን።

“በእነርሱ አእምሮ አንድን ያልተገባ ተግባር የፈጸመን ሠራተኛ ተገቢውን ቅጣት ሰጥተዋል።”

ነገር ግን ይህ ድርጊታቸው የክለቡን የወደፊት ዕቅድ እና ሕልም አመላካችም ነው ብሏል የኳስ ተንታኙ ሳይመን።

ይህም ከዚህ ወዲህ ፓሪስ ሴን ዠርሜን የሚገነባው በወጣት ተጫዋቾች ስለመሆኑ ማንም ጥርጣሬ እንዳይገባው ማሳያ ነው።

ሳይመን እንደሚለው የፒኤስጂ ደጋፊዎችም ቢሆን ከዚህ ወዲያ ሜሲን አይፈልጉትም። ኮንትራቱም እንደማይታደስለት የተረጋገጠ ጉዳይ ነው።