የሊቨርፑል አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ዳኛ ላይ በሰነዘሩት አስተያየት ተከሰሱ

የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ከዳኛ ፖል ቲርኒን ጋር ሲነጋገሩ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ከዳኛ ፖል ቲርኒን ጋር ሲነጋገሩ

የሊቨርፑሉ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ቡድናቸው ቶተንሃምን ባሸነፈበት ጨዋታ የመሐል ዳኛው ፖል ቲርኒን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት በእንግሊዝ እግር ኳስ ማኅበር ክስ ተመሰረተባቸው።

ዳኛው ከቡድኔ ጋር ችግር አለበት ሲሉ አስተያየት የሰጡት ጀርመናዊው በኋላም በአስተያየታቸው መጸጸታቸውን አስታውቀዋል።

የእግር ኳስ ማኅበሩ ክሎፕ አስተያየት “ተገቢ ያልሆነ ባህሪ” ውስጥ ይካተታል ብሏል።

አሰልጣኙ እስከመጪው አርብ ድረስ ለክሱ ምላሽ መስጠት ይጠበቅባቸዋል።

“አስልጣኙ ስለጨዋታው ዳኛ የሰጡት አስተያየት ያልተገባ ባህሪ ከመሆን ባለፈ አድልዎን የሚያሳይ እና የዳኛውን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ የከተተ ነው” ብሏል ማኅበሩ።

ረቡዕ ከፉልሃም ጋር ከሚያደርጉት ጨዋታ በፊት አስተያየታቸውን የሰጡት ክሎፕ “ሁሉም ነገር መፈጠር አልነበረበትም” ብለዋል።

“በወቅቱ በስሜት እና በንዴት የተፈጠረ ነገር ነው። ለዚህም ነው በዚያ መንገድ ደስታዬን የገለጽኩት።”

“ጨዋታውን 4 ለ 3 ብናሸንፍም እኔ ነኝ መነጋገሪያ ርዕስ የፈጠርኩት። በዚህም በጣም በጣም ተጸጽቻለሁ። መሆን ያልነበረበት ነገር ነው” ብለዋል።

ቶተንሃሞች ሦስተኛ ጎል ያስቆተሩበትን ቅጣት ምት ማግኘታቸውን ተቃወሙት አሰልጣኙ የማሸነፊያዋን ጎል ሲያስቆጥሩ ወደ አራተኛው ዳኛ ደስታቸውን እየገለጹ ሲሮጡ እግራቸው ላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ይታወሳል።

ክሎፕ በተቆጠረው ግብ ደስታቸውን ከገለጹ በኋላ የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመዞባቸዋል። በዚህ ወቅት ዳኛው ጥሩ ነገር እንዳልተናሯቸው ከጨዋታው በኋላ ገልጸዋል።

የፕሪሚየር ሊጉ የዳኞች አስተዳደር ኮሚቴ በሁሉም ጨዋታዎች ዳኞች የሚያደርጉት ንግግር የሚመዘገቡበት ሥርዓት መኖሩን ጠቅሶ ቲየርኒ በሕጋዊ መንገድ ኃላፊነታቸውን መወጣታቸውን አስታውቋል።

ክሎፕ በሰጡት አስተያየት መጸጸታቸውን ቢገልጹም ሐሰተኛ ነገር ተናግረዋል መባላቸውን አስተባብለዋል።

“ቲየርኒ አውቆ ባያደርገውም፣ ከእርሱ ጋር ታሪክ እንዳለን የምትክዱት አይመስለኝም” ብለዋል።

“እኔ ቂመኛ አይደለሁም። ነገር ግን ከዚህ ቀደም በነበሩ ወሳኝ ጨዋታዎች የተከሰቱ ነገሮች ሆን ብለው የተከሰቱ አይደሉም። ነገር ሁሌም ይኖራሉ።”

“ዳኞች በተናገርኩት ነገር በጣም ተናደዋል። ሁለት ነገሮችን መናገር አልነበረብኝም ነገር ግን አልዋሸሁም።”

ክሎፕ በጥቅምት ወር ከማንቸስተር ሲቲ ጋር በነበራቸው ጨዋታ የአንድ ጨዋታ እገዳ ተጥሎባቸው ነበር።

በወቅቱ 30,000 ፓውንድ የተቀጡ ሲሆን፣ ወደፊቱም ባህሪያቸውን እንዲያርሙ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል።

ዛሬ ምሽት ሊቨርፑል ፉልሃምን ሲያስተናግድ ማንቸስተር ሲቲ ደግሞ በሜዳው ዌስትሃምን ይገጥማል።