በኢትዮጵያ በሺዎች የሚቆጠሩ ዶሮዎችን የገደለው በሽታና የተጣለው የገበያ እግድ

በአዲስ አበባ የዶሮ ገበያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከሰሞኑ የዶሮ እርባታ ማዕከል በሆነችው በቢሾፍቱ፣ በአዲስ አበባና በአንዳንድ አጎራባች አካባቢዎች በተከሰተ ያልታወቀ የዶሮ በሽታ በበርካታ ሺህ የሚቆጠሩ ዶሮዎች መሞታቸውን ተከትሎ የግብርና ሚኒስቴር ዶሮና የዶሮ ውጤቶች ለገበያ እንዳይቀርቡ ሰኔ 03/2014 ዓ.ም እግድ ጥሏል።

በአንዳንድ የዶሮ እርባታ ጣቢያዎች ውስጥ መቶ በመቶ በሚባል ሁኔታ ዶሮዎችን ገድሏል የተባለው ያልታወቀ የዶሮ በሽታ፣ ምንነትና መፍትሔ እስኪገኝ ድረስ ዶሮ፣ ጫጩቶችና እንቁላሎች ከተለያዩ ክልሎች ማጓጓዝ አይቻልም።

በተጨማሪም ዶሮ አርቢዎች ዶሮና የዶሮ ውጤቶችን ለገበያ ማቅረብ እንደማይችሉ የግብርና ሚኒስቴር የእንስሳትና የእንስሳት ሃብት ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ፍቅሩ ረጋሳ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

በተለይ በሽታው በዋነኝነት በተከሰተባቸው በቢሾፍቱ፣ በአዲስ አበባና በአጎራባች አካባቢዎች ዶሮና የዶሮ ውጤቶችን ማጓጓዝ እንዲሁም ከውጭም ማስገባትም ሆነ ወደ ውጭ መላክ አይቻልም።

በሽታው በተከሰተባቸው ስፍራዎች ብቻ ተወስኖ እንዲቀርና ወደሌሎች አካባቢዎች እንዳይዛመት የእንቅስቃሴው ገደብ እንደተጣለ የሚናገሩት ዶክተር ፍቅሩ፣ ለተለያዩ ክልሎችም የየራሳቸውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

በአሁኑ ጊዜ መጀመሪያ ላይ እንደነበረው የዶሮዎች ሞት እየተከሰተ እንዳልሆነና የመቀነስ አዝማሚያ እንዳሳየ የሚናገሩት ሚኒስትር ዲኤታው ሆኖም ሙሉ በሙሉ አለመገታቱን አመልክተዋል።

ይህንንም ተከትሎ በሺዎች የሚቆጠሩ የተፈለፈሉ ጫጩቶች፣ እንዲሁም የደረሱ እንቁላሎች ለገበያ እንዳይውሉ እግድ በመጣሉ በርካታ ዶሮ አርቢዎች ለችግር ተጋልጠናል ብለዋል።

በሽታው ምንድን ነው? ያደረሰውስ ጉዳት?

የዶሮ በሽታው የተከሰተው ከሳምንት በፊት ሲሆን በኢትዮጵያ ውስጥ የተሻሻለ የዶሮ እርባታ ያላቸው በሚባሉት ስፍራዎች በአዲስ አበባ፣ በቢሾፍቱና በአጎራባች አካባቢዎች መሆኑን ከግብርና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያስረዳል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የበሽታው መዛመትም ከቢሾፍቱ እስከ አዳማ ባለው ኮሪደር በስፋት ተከስቶ የነበረ መሆኑንም ብርሃኑ ሚሊዮን የኢትዮጵያ ዶሮ አርቢዎችና አቀናባሪዎች ማኅበር ሥራ አስኪያጅ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ምንም እንኳን የዶሮ በሽታዎች በተደጋጋሚ ቢከሰቱም በሽታው በፍጥነት የመተላለፍና የመዛመት ባህርይ በማሳየቱ እንዲሁም በገባባቸው የዶሮ እርባታ ማዕከላት በብዛት እንዲሁም ሙሉ በሙሉ ዶሮዎችን መግደሉን ዶክተር ፍቅሩ ይናገራሉ።

በተለይም ያጠቃው አነስተኛ እና መካከለኛ የዶሮ እርባታ ማዕከላትን ሲሆን ሁሉም ዶሮዎች ያለቁባቸው ማርቢያዎችም ታይተዋል።

እስካሁን ባለው መቶ ሺህ ወይም ከዚያ በላይ ዶሮዎች ሞተዋል ተብሎ የሚገመት ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተጣራ መረጃ ላይ እንዳልደረሰና ገና ስለሁኔታ ግምገማም እያደረገ ነው።

“በዚህ አይነት ፍጥነት መዛመቱና ዶሮዎችን በከፍተኛ ሁኔታ መግደሉ ስጋት ፈጥሯል። ዝም ከተባለም ከአንድ እርባታ ማዕከል ወደ ሌላ እርባታ ማዕከል የመዛመት ሁኔታ ሲያሳይ ወደ እንቅስቃሴ ገደብ ገብተናል” ይላሉ ዶክተር ፍቅሩ።

ከሰሞኑ የተከሰተው ያልታወቀ የዶሮ በሽታ ትልልቅ የዶሮ ማርቢያዎችን ያላጠቃ ቢሆንም፣ እነዚህ ማዕከላትም ቢሆን ዶሮና የዶሮ ግብዓቶች ማጓጓዝም ሆነ መሸጥ አይችሉም።

የእንስሳት ህክምና ባለሞያ የሆኑት ዶክተር ደመቀ ወንድማገኝ መንግሥቴ፣ በሽታው በአነስተኛና በመካከለኛ ዶሮ እርባታ ማዕከል ያስከተለውን ከፍተኛ ሞት በማየት ክስተቱ ከበድ ያለ ሊሆን እንደሚችል ይጠቅሳሉ።

በሽታው ሁሉንም አይነት ዶሮዎች፣ ጫጩቶችን ጨምሮ መጠነ ሰፊ ሞት በማድረሱና ሰፊ ቦታ በመሸፈኑ የዶሮ በሸታ ወረርሽኝ ሊባል እንደሚችል ዶክተር ደመቀ ያስረዳሉ።

አቶ ብርሃኑ በበኩላቸው በሽታው እያጠቃ ያለው በበለጠ የእንቁላል ዶሮዎችን እንደሆነና ጫጩቶችን ወይም የሥጋ ዶሮዎችን እየገደለ እንዳልሆነ ይገልጻሉ።

እንቁላል

የተጣለው ክልከላ ያደረሰው ጫና

እስካሁን ስለበሽታው የታወቀ ነገር ስለሌለ ምንነቱን ለመለየት የግብርና ሚኒስቴር የምርምር ሥራዎችን በዋነኝነት እያከናወነ ይገኛል።

ሆኖም በተደረገው ዳሰሳና ከበሽታው ባህርይ በመነሳት በንክኪ ስለሚተላለፍ በአዲስ አበባ፣ በቢሾፍቱና በኦሮሚያ ክልል የዶሮና የዶሮ ውጤቶች ገቢም ሆነ ወጪ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ ውሳኔ ተላልፏል።

ለዚህ ውሳኔ ምክንያቱም አንዳንድ አርቢዎች ዶሮዎች ሲታመሙባቸው ከማስወገድ ይልቅ የመሸጥ ሁኔታ በመታየቱና በሌሎች ስፍራዎች ተዛምቶ በአጠቃላይ በአገሪቱ የዶሮ እርባታ ዘርፍን እንዳይጎዳ በሚል የተወሰደ እርምጃ እንደሆነ ሚኒስትር ዲኤታው ይጠቅሳሉ።

አቶ ብርሃኑ በበኩላቸው ጠበቅ ያለና ሙሉ እገዳ ነው የተጣለው ያሉ ሲሆን፣ እሳቸውም ሲጠቅሱ በኢትዮጵያ ደረጃ ከክልል ወደ ክልል ዶሮና የዶሮ ግብዓቶችን እንቁላልና ጫጩቶችን ማጓጓዝ አይቻልም። ከዶሮና የዶሮ ውጤቶች በተጨማሪ ከዶሮ ጋር ንክኪ የሚኖራቸውን መገልገያዎችን መኖን ጨምሮ ማጓጓዝ እንደተገደበ ያስረዳሉ።

ከዚህ ባለፈ ዶሮ፣ ጫጩቶች፣ ቄቦች፣ የዳበረ (የለማ) እንቁላል ከውጭ አገራትም እንዳይገቡ እንዲሁም ወደ ውጭ እንዳይላኩ እገዳው ይከለክላል። ለገበያ ማቅረቡም ሆነ የእንቅስቃሴ ገደቡ በሽታው ተለይቶ በቁጥጥር ስር እስኪውል ድረስም የሚቀጥል እንደሚሆን በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተገልጿል።

ባለፈው ሳምንት የሞት መጠኑ ከፍተኛ የነበረ ቢሆንም፣ ባለፉት ቀናት ግን ጋብ የማለት ምልክት እንዳሳየም ሚኒስትር ዲኤታው ዶ/ር ፍቅሩ፣ አቶ ብርሃኑ እንዲሁም ዶክተር ደመቀ ያስረዳሉ።

“ሞት ቆሟል ማለት በሽታው አይዛመትም ማለት ስለማይቻል፣ ምን አይነት ተፅእኖ እንደሚያመጣ ስለማይታወቅ፤ የኅብረተሰብ ጤና ጉዳይም ስለሚኖረው ያንን ማጣራት ያስፈልጋል” ይላሉ ዶክተር ደመቀ።

ሆኖም በአዲስ አበባ፣ በቢሾፍቱና አጎራባች አካባቢዎች ያሉ ዶሮ አርቢዎች ምርቶቻቸውን ማጓጓዝ እና ለገበያ ማቅረብ ባለመቻላቸው ለከፍተኛ ኪሳራ ተዳርገናል ይላሉ።

በተለይም አቶ ብርሃኑ እንደሚናገሩት አብዛኞቹ አነስተኛ የዶሮ አርቢዎች በመሆናቸው ከዶሮ ምርታቸው በሚያገኙት ገቢ ላይ ጥገኛ በመሆናቸው ከፍተኛ ጉዳት አስከትሎባቸዋል።

በዶሮዎች ላይ ከተከሰተው በሽታ ጋር በተያያዘ በተጣለው ገደቡ ምክንያት ባለፈው ሳምንት ውስጥ ብቻ 40 ሺህ የሚሆኑ ጫጩቶች በአንድ የእርባታ ስፍራ ተቀብረዋል ይላሉ።

አቶ ብርሃኑ እንደሚሉት አንዳንድ ማዕከላት ዋነኛ ተግባራቸው ጫጩት እያስፈለፈሉ መሸጥ ስለሆነ ይህም በሺዎች የሚቆጠሩ ጫጩቶች ያስፈለፈለው ማዕከል ማጓጓዝ ባለመቻሉ ለማስወገድ ተገዷል።

ሌላኛው አቶ ብርሃኑ የሚጠቅሱት የዶሮ እርባታና ማቀናበሪያ ማዕከል መፈልፈል የነበረባቸው 50 ሺህ እንቁላሎች እንደያዘ በመቆየቱ ከጥቅም ውጪ እንደሚሆን ነው።

በተጨማሪም ከውጭ አገራት በዶላር ከፍተኛ ክምችት አስገብተው እንቁላል መፈልፈልና መሸጥ ቢኖርባቸውም እነዚህ ማዕከላት ይህንን ማድረግ ባለመቻላቸው ለከፍተኛ ኪሳራ መዳረጋቸውንም ያስረዳሉ። በርካታ የዘር እንቁላሎችም ከጥቅም ውጪ በመሆናቸው ይህ ሁኔታ አርቢዎችን በተለይም አነስተኛ አርቢዎችን ከሥራ እያስወጣ መሆኑንም ይገልጻሉ።

ሌላኛው የሚያነሱት ችግር እነዚህ አርቢዎች ከሚያገኙት ገቢ መኖ መግዛት ባለመቻላቸው፣ እገዳው በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ዶሮዎቹ በረሃብ ያልቃሉ የሚል ስጋትም ተጋርጦባቸዋል። “ዶሮዎቹ ከበሽታው በበለጠ በረሃብ ሊያልቁ ይችላሉ” ይላሉ አቶ ብርሃኑ።

የአነስተኛ አርቢዎች ስጋት

የአገሪቱን ከሃምሳ በመቶ በላይ የሆነ የእንቁላል አቅርቦት የሚይዙት አነስተኛ አርቢዎች ናቸው የሚሉት አቶ ብርሃኑ፣ ከሞቱ በላይ ምርት አለመሸጥ ከፍተኛ ጉዳት ስላላው ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም ያስረዳሉ።

“ነገ ከነገ ወዲያ የእነዚህ የዶሮ እርባታ ማዕከላት ዕጣ ፈንታ ምንድን ነው?” ሲሉም ይጠይቃሉ።

ቅሬታቸውንም ለሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያቀረቡ ሲሆን በአጭር ጊዜም መፍትሄ ያገኛል የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸዋል።

በርካታ አባሎቻቸውም ከፍተኛ ቅሬታ እያነሱ ሲሆን አፋጣኝ ጥናት ተደርጎ በሽታው ከተለየና ሌላ ችግር የማያስከትል ከሆነ የጥንቃቄ እርምጃዎች እየተወሰዱ ወደ ሥራ የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንደሚፈልጉ አመልክተዋል።

ለአቶ ብርሃኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጣላቸው የእንቅስቃሴ ገደቦች ከባድ የሚባሉ መሆናቸውን ነው። በተጨማሪም በሽታው የከፋ ስጋት እንደማይደቅን ከሚጠቅሷቸው ምክንያቶች ዋነኛው ወደ ሰው አለመተላለፉን ነው።

የበሽታው ምንነት በአሁኑ ወቅት እየተመረመረ ቢሆንም ሚኒስትሩም ሆነ አቶ ብርሃኑ በሽተኛ ዶሮዎችን ሲንከባከቡ ከነበሩ ግለሰቦች እንዲሁም በማዕከላቱ ከተደረገው አሰሳ ወደ ሰው እንደማይተላለፍ ነው። በሽተኛ ዶሮዎችን ሲንከባከቡ የነበሩ ግለሰቦች ምንም አይነት የህመም ምልክት አላሳዩም።

ሌላኛው አቶ ብርሃኑ የሚጠቅሱት ምክንያት በአንዳንድ የእርባታ ማዕከላት አቅራቢያቸው ያለው ማዕከል በበሽታ ቢጠቃም ወደሌሎች አለመዛመቱ ሌላው የሚጠቅሱት ምክንያት ነው።

በተጨማሪም በባለፉት ሦስት እና አራት ቀናት ሞት እንዳልተከሰተ፣ በሽታውም የለም በሚባልበት ደረጃ ላይ እንዳለ እንዲሁም በትልልቅ የማራቢያ ማዕከላት ባለመከሰቱ መሆኑ ሌላኛው በጎ ምልክት ነው ይላሉ።

በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ላይ ባሉ ጣቢያዎች መከሰቱ የጥንቃቄ መላላት (ባዮ ሴኩሪቲ ደካማ) መሆን ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል ሲሉም ይጠቁማሉ።

“በሽታ አለ። ዶሮ ሁልጊዜም ከበሽታ ጋር ነው የሚኖረው። ለሰው ጤና ጉዳት የማያመጣ ከሆነ ሌላውን በክትባትም እየተቋቋምን መኖር እንችላለን። ለምሳሌ ኒውካስትል የሚባለው የዶሮ በሽታ 70 አስከ 80 በመቶ ገዳይ ነው። ይህም ተመሳሳይ በሽታ ከሆነ ማዕከላቱ ጥንቃቄ እያደረጉ ወደ ሥራ መመለስ ይኖርባቸዋል። አሁን በርካታ ጉዳቶች እየደረሱ ናቸው” ይላሉ።

ሚኒስትሩ የተጣሉት ገደቦች ከባድ ነው በሚለው አይስማሙም “ከባዱ ነገር ዶሮዎቹ ማለቃቸው ነው” ይላሉ።

ምንነቱ ያልታወቀው በሸታ በተለያዩ ከተሞች በሚገኙ የማርቢያ ማዕከላት ተዛምቶ ዶሮዎችን ቢጨርስስ? ብለው የሚጠይቁት ሚኒስትር ዲኤታው በአጠቃላይ የዶሮ እርባታና ማቀናበር ሥርዓቱን ሊገድል ይችላል ይላሉ። ሆኖም በዶሮ አርቢዎች ላይ ያለውን ተፅእኖና ኪሳራ እንደሚረዱ ገልጸዋል።

“ወደን ሳይሆን ከመጥፎው የተሻለ መጥፎን መምረጥ ነው። ለጊዜው እንቁላሉንም ሽያጩንም ያዝ አድርገው እኛ ደግሞ የተከሰተባቸው ቦታዎች ላይ እርምጃ ወስደን ከተቆጣጠርን በኋላ የተሻለ ነገር ይኖራል” ይላሉ።

 እንዲህ አይነት እርምጃዎች በበርካታ አገራት የሚወሰዱ የተለመዱ አሰራሮችም መሆናቸውንም አፅንኦት ይሰጣሉ።

ለዶክተር ደመቀም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የጣለው እገዳ ሳይንሱን ተከትለው ነው ይላሉ። የትኛውም አገር ላይ ወረርሽኝ ሲያጋጥም እንቅስቃሴ መገደብ የተለመደ መሆኑን የሚጠቅሱት ዶክተር ደመቀ፣ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት የተጣሉ የእንቅስቃሴ ገደቦችን ይጠቅሳሉ።

መሥሪያ ቤቱ በንክኪ መዛመትን ለመግታት እንቅስቃሴን መገደብን በዚህም ሕዝቡንም ሆነ የዶሮ እርባታ ማዕከላትን ለመጠበቅ፣ እንዲህ አይነት እርምጃ በበርካታ አገራት ተግባራዊ ይደረጋል ይላሉ።

ሆኖም ሳይንሱ ይህንን ቢልም በኢትዮጵያ አንድምታ አብዛኛው ዶሮ አርቢ መኖና የተለያዩ መገልገያዎች የሚገዛው ከቢሾፍቱ ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ በሽታ ያልገባባቸው አካባቢዎች በመኖና በሌሎች መገልገያዎች ጥገኛ ስለሚሆኑ በሎጂስቲክ መቋረጥ ምክንያት ችግር ውስጥ እንደሚገቡም ያስረዳሉ።

ሆኖም ይላሉ ዶክተር ደመቀ “እንዲህ አይነት ውሳኔዎች ሲወሰኑ በጣም መጥፎ ከሚባለው፣ የተሻለውን መጥፎ መምረጥ የሚለውን አሰራር ተከትሎ ነው።"

ዶሮ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ወረርሽኝ አለ ወይ?

ዶክተር ደመቀ እንደሚያስረዱት የዶሮ በሽታ ወረርሽኝ አለ የሚባለው ከሁለት በላይ የሆኑ የዶሮ እርባታ ማዕከላትን ሲያጠቃ ነው።

በዚህም ወቅት የተከሰተው በሽታ በርካታ ማዕከላትን ማጥቃቱ ወደ አጎራባች አካባቢዎች መዛመቱ የዶሮ ወረርሽኝ ሊባል ይችላል ይላሉ።

ከዚህ በፊት አጋጥሞ ቢያውቅም በዚህ ደረጃ እንዳልነበርና መለስ ያሉ የዶሮ መሞት መጠን እንደነበረና የተወሰነውንም መርጦ እንዳጋጠመ ያወሳሉ።

ዶክተር ፍቅሩም በአንዳንድ የዶሮ እርባታ ማዕከላት መቶ በመቶ ዶሮዎቹን በመጨረሱ ወረርሽኝ ነው ለማለት እንደሚያስችል ያስረዳሉ።

ወረርሽኝ በሚያጋጥምበት ወቅት እንቅስቃሴዎችን መገደብን ጨምሮ ሌሎች እርምጃዎች እንደሚወሰዱ የሚናገሩት አቶ ብርሃኑ፣ ወረርሽኝ ነው ተብሎ የሚታሰብ ከሆነ በፍጥነት መለየት እንዳለበት ያስረዳሉ።

“የዶሮ እርባታ ዘርፉ በቋፍ ላይ ነው” የሚሉት አቶ ብርሃኑ በርካታ ችግሮች ያሉበትና እድገት የማያሳይ ነው የሚሉትን ዘርፍ ሊያቀጭጨው እንደሚችልም ያስጠነቅቃሉ። አሁን ባለው ሁኔታም ላይነሳ ከሚወድቅበት ደረጃ ላይ በመሆኑ እግዱ ላላ ሊል ይገባል ይላሉ።

ወረርሽኝ ተከስቶ እንደማያውቅ የሚናገሩት አቶ ብርሃኑ በ1997ም ‘በርድ ፍሉ’ ነው በሚል እሳቤ በርካታ ዶሮዎች መገደላቸውን አስታውሰው። የላብራቶሪ ውጤቱ ግን ወረርሽኝ እንዳልሆነ በማሳየቱ የተወሰደው ትክክለኛ እርምጃ እንዳልነበር ያወሳሉ።

በዚህም ወቅት ተመሳሳይ እርምጃ እየተወሰደ እንደሆነ የሚናገሩት ሥራ አስኪያጁ በሽታው ታውቆ ለዚያ የሚሆን ትክክለኛ እርምጃ ቢወሰድ ችግር እንደሌለውም ያስረዳሉ።

ነገር ግን “በአሁኑ ወቅት ውጤቱ ባልታወቀበትና አመላካች ሁኔታዎች ብዙ ወረርሽኝ በማይመስሉበት ሁኔታ” ወደ እገዳ እርምጃ መገባቱ ትክክል እንዳልሆነም አፅንኦት ይሰጣሉ።

የዶሮ እርባታ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣ ዘርፍ ነው የሚሉት ዶክተር ፍቅሩ፣ ይህም እንዳይጎዳ ስለ በሽታው ምንነት በማያሻማ መልኩ ውጤቱ አስኪታወቅ ድረስ ገደቡ የሚቀጥል ሲሆን፣ አሁን በተያዘው ሁኔታ ረጅም ጊዜ ሊቆይ እንደማይችልም ያስረዳሉ።

የዶሮ አርቢዎች ማኅበር በተጨማሪ የሚያነሱት ቅሬታ በግብርና ሚኒስቴር እየተላለፉ ያሉ ውሳኔዎች ማኅበሩን ያገለሉ መሆናቸውን ነው። ማኅበሩ እንደ ዋና ባለ ድርሻ አካል በምርምሮቹና በመፍትሄዎቹ ላይ ተሳታፊ ቢሆን ለመከላከያ እርምጃውም የተሻለ ግብዓት እንዲሁም በተቀላጠፈ ጊዜ ቶሎ ውጤት ላይ ለመድረስ ይቻላል ብለው ያምናሉ።

እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችና ጥንቃቄዎች

ከተከሰተው የዶሮ በሽታ ጋር በተያያዘ ከተለያዩ ዘርፎች የተውጣጣ ግብረ ኃይል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አቋቁሟል። ግንዛቤ የማስጨበጥ እንዲሁም በሸታው በተከሰተባቸው ስፍራዎች የክትትል ሥራ፣ ምርምሮች፣ ምላሽ የመስጠት ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።

በርካታ ዶሮዎች በየጢሻው ተጥለው በመገኘታቸው በሽታው እንዳይስፋፋና በድጋሚ እንዳይከሰት እነዚህን የሞቱ ዶሮዎችን አሰባስቦ የማስቀበርና የማቃጠል ሥራዎች እየተሰሩ ነው።

በሽታው በተከሰተባቸው ስፍራዎች ሌላ በሽታ ሊቀሰቀስ ይችላል በሚል ኬሚካል የመርጨት ተግባር እየተከናወነ ነው። ትልልቆቹ የዶሮ እርባታ ማዕከላትም የደኅንነት አጠባበቃቸውን በማሳደግ በዚያው ምርቶቻቸውን እንዲይዙ ተደርጓል።

የዶሮ እርባታ ማዕከላት ላይ በሽታዎች የመከሰት ነገር የተለመደ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር ፍቅሩና ዶክተር ደመቀ፣ በሽታዎች ሲከሰቱ ሊያደርሷቸው የሚችሉ ጉዳቶችን በተመለከተ አስቀድመው መወሰድ ያለባቸው ጥንቃቄዎች (የባዮ ሴኩሪቲ ደኅንነት) ቢኖርም አንዳንዶች በትክክል ተግባራዊ እንደማያደርጉ ይናገራሉ።

በተጨማሪም ኬሚካሎችና የጽዳት ግብዓቶች (ዲስኢንፌክታንት) የማይጠቀሙ፣ ክትባትም ጊዜውን ጠብቀው በአግባቡ የማይሰጡ የእርባታ ማዕከላት ሲኖሩ በሽታዎች እንደሚከሰቱ ጠቅሰው፣ በአሁኑ ወቅት ጥንቃቄዎችን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ዶክተር ፍቅሩ ለአርቢዎች የሚመክሩት በአካባቢያቸው የሞቱና የተጣሉ ዶሮዎች ካሉ በአግባቡ ማስወገድ፣ የኬሚካል ርጭትም ካለ ያንን ማከናወን ከተሰማራው ግብረ ኃይል ጋር በከላከል ሥራው ላይ እንዲሳተፉ መክረዋል።

ኅብረተሰቡም ቢሆን ጥቆማ እንዲያደርግ የሚመክሩት ዶክተር ፍቅሩ፣ በተባባረ መንገድም በፍጥነት ለመቆጣጠርና ለማጥፋት ይረዳል ይላሉ።

በተለያዩ መንገዶች እየወጡ ያሉ መረጃዎች ኅብረተሰቡን ዶሮና እንቁላል ከመመገብ ፍርሃት ውስጥ የሚከቱ ናቸው የሚሉት አቶ ብርሃኑ በበኩላቸው፣ ለሰው ጤና አስጊ ባልሆነበት ሁኔታ ለመረጃዎች ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ይላሉ።

“ይሄንን ያህል የሚያስፈራ ነገር የለም። ነገር ግን በደንብ ያልታወቀ ጉዳይ ደግሞ እንዲህ አድርጉ ማለት አይቻልም። ምንም አይነት የገጠመ ወይም ሪፖርት የተደረገ የለም። ነገሮችን እስከምናውቅ ብሉ አትብሉ ልንል አንችልም” ይላሉ ዶክተር ፍቅሩ በበኩላቸው።

ዶክተር ደመቀ ሕዝቡ ዶሮንም ሆነ የዶሮ ተዋፅኦ የሚጠበቅበት መንድ አብስሎ ስለሆነ፣ በደንብ ማብሰልና ንፅህናውን የመጠበቅ ሁኔታ ካለ ተጠቃሚውን የሚያሰጋ ነገር ሊኖር ይችላል ብለው እንደማያስቡ ያስረዳሉ።

ሆኖም በአጠቃላይ ባለሙያው የሚያስተላልፉት መልዕክት የዶሮ እርባታ ወደ ኢንዱስትሪ ሊያድግ እንደሚችል ጠቅሰው፣ ይህም የራሱ ችግር ስለሚያመጣ ተገቢ የሆነ የዶሮ በሽታ መከላከልና መቋቋም ሥራ በተገቢው መንገድ መሰራት እንዳለበት ነው።

ይህንንም የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላትም ሆነ የግል ሴክተሩ አንድ ላይ ሆነው ፕሮግራም ቢቀርጹ ጥሩ ነው በማለት መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።