አሜሪካ የእርዳታ ሠራተኞቿ ከዚምባብዌ መባረራቸውን አወገዘች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
አሜሪካ በዚምባብዌ የነበሩ የእርዳታ ሠራተኞቿ መዋከብ፣ መታሰር እንዲሁም ከአገር እንዲባረሩ ተደርገዋል ስትል ከሰሰች።
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) እንዳለው በዚምባብዌ ያሉ የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት እና ጊዜያዊ ሠራተኞች “በቃል እና በአካል ማስፈራሪያ ደርሶባቸዋል” ብሏል።
እነዚህ አካላት በዚምባብዌ የተገኙት “የዜጎችን ተሳትፎ፣ የዲሞክራሲ ተቋማትን እና የሰብዓዊ መብቶችን ለመደገፍ ነበር” ሲልም ዩኤስኤአይዲ ባወጣው መግለጫ አክሏል።
ነገር ግን ዚምባብዌ ዲሞክራሲዋን ለማሻሻል የነበራት ቁርጠኝነት “ባዶ ነው” ሲልም ተችቷል።
የዚምባብዌ መንግሥት ዩኤስኤአይዲ በሰነዘረበት ውንጀላ ላይ የሰጠው ምላሽ የለም።
ሰኞ ዕለት አሜሪካ የዚምባብዌው ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን በሙስና እና በሰብዓዊ መብቶች ረገጣ በመወንጀል አዲስ ማዕቀብ መጣሏን አስታውቃለች።
አዲሱ ማዕቀብ ከሁለት አስርት ዓመታት በፊት በአገሪቱ ተጥሎ የነበረውን ሰፊ ማዕቀብም ተክቷል።
ከፕሬዝዳንት ምናንጋግዋ በተጨማሪ ሌሎች 10 ሰዎች እና ሦስት የንግድ ድርጅቶችን የሚነካው ማዕቀብ በአሜሪካ ያሉ ንብረቶቻቸውን ማገድ እንዲሁም ጉዞ ማድረግን የሚከለክል ነው።
የፕሬዝዳንት ምናንጋግዋ ቃለ አቀባይ ማዕቀቡን በጠበኝነት ድርጊት የፈረጁት ሲሆን፣ የአሜሪካ መንግሥትንም “ስም በማጥፋት ወንጀል” ከሰውታል።
የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት ኃላፊ ሳማንታ ፓወር በሰጡት መግለጫ አንዳንድ አባላቶቻቸው “እስራት፣ ደኅንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ መጓጓዝ፣ ረዘም ያለ ምርመራ እንዲሁም የግል የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎቻቸው እንደተወሰደባቸው” ተናግረዋል።
ኃላፊዋ አክለውም ባለፉት ሁለት ዓመታትም የአሜሪካ መንግሥት ባለሥልጣናት እና ዜጎች ከዚምባብዌ ባለሥልጣናት “ትንኮሳ እና ተገቢ ያልሆነ አያያዝ” ያጋጠሙባቸው “ከባድ ክስተቶችን” ማስተናገዳቸውን ተናግረዋል።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር በሰጡት መግለጫ የእርዳታ ቡድኑ ወደ ዚምባብዌ በሕጋዊ መንገድ መግባቱን ገልጸው ይህም “የዚምባብዌ መንግሥት ለዲሞክራሲያዊ ማሻሻያው ያለውን ቁርጠኝነት ለመደገፍ ነው” ብለዋል።
ኃላፊዋ አክለውም ተቋማቸው በዚምባብዌ ውስጥ ያሉትን የሲቪል ማኅበረሰብ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን እና ነጻ ሚዲያዎችን አጠንክሮ ይደግፋል ካሉ በኋላ ነገር ግን “የዚምባብዌ ዜጎችን መሠረታዊ ነጻነቶችን እንዲሁም መልካም አስተዳደርን የሚነፍጉ አካላትን ተጠያቂ ለማድረግ ተጨማሪ እርምጃዎችን ከመውሰድ ወደ ኋላ አይልም” ሲሉም አስጠንቅቀዋል።












