ጥቂት “በጋዛ የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል ተባባሪ አልሆንም” ብሎ ራሱን ስላቃጠለው የአሜሪካው አየር ኃይል አባል

የፎቶው ባለመብት, Anadolu
አንድ እሁድ ጠዋት አሜሪካዊው የአየር ኃይል አባል “ከእንግዲህ በኋላ የዘር ማጥፋት ወንጀል ተባባሪ አልሆንም” ብሎ ራሱን አቃጠለ።
የ25 ዓመቱ አሮን ቡሸኔል የአየር ኃይል የደንብ ልብሱን እንደለበሰ ነበር ዋሽንግተን ዲሲ ወደ ሚገኘው የእስራኤል ኤምባሲ ያቀናው።
ራሱንም አቃጥሎ እየነደደ መሬት ላይ እስኪወድቅ ድረስ “ፍልስጤም ነጻ ትውጣ” [ፍሪ ፓለስታይን] እያለ ነበር።
ሆስፒታል ቢወሰድም ከሰዓታት በኋላ ሕይወቱ አለፈ።
አሮን እራሱን ሲያቃጥልም በቀጥታ ስርጭት እየተላለፈ ነበር።
እርምጃውንም “ከፍተኛ ተቃውሞ” ሲል አሮን የገለጸው ሲሆን፣ ቪዲዮውም በዓለም ዙሪያ ታይቷል።
መጀመሪያ ላይ ቪዲዮው ከማኅበራዊ ሚዲያ እንዲወገድ ቢደረግም፣ በኋላ ግን ከፍተኛ ዕይታ አግኝቷል።
መስዋዕትነቱ ሰዎችን አስደንግጧል፣ አስገርሟል እንዲሁም አነሳስቷል ሌላም ሌላም።
እስራኤል በጋዛ ላይ እየፈጸመችው ባለው የተቀናጀ ጥቃት አብዛኞቹ ህጻናት እና ሴቶች የሆኑ ከ30 ሺህ በላይ ፍልስጤማውያን መገደላቸውን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።
እስራኤል በጋዛ ላይ እየፈጸመችው ያለውን የማያባራ ጥቃት እየተቃወሙ ያሉ በርካቶችም በአሜሪካ የአሮንን ሕይወት በማሰብ ሻማ አብርተዋል።
አሮን በፍልስጤማውያን ላይ እየደረሰ ያለውን ተቃውሞ ራሱን ማቃጠሉ የቅርብ ጓደኞቹን ሳይቀር አስደንግጧል። በሐዘን እና በድንጋጤ መካከል ያሉት ጓደኞቹ በዓለም ላይ የሚዲያ ቀልብ መሳቡም ጠምዶ የያዛቸው ጉዳይ ነው።
አሮን ቡሽኔል ከአውሮፓውያኑ 2020 እስካለፈው ዓመት መጨረሻ በላክላንድ አየር ኃይል ጣቢያ ተመድቦ መኖሪያውን በሳን አንቶኒዮ ቴክሳስ አድርጎ ነበር። እዚያ የሚያውቁት የመብት እንቅስቃሴ ተሟጋቾች እና በማኅበረሰቡ ዘንድ ሞቱ “ከፍተኛ ድንጋጤ” እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ።
“መጀመሪያ ላይ ከፍተኛ ድንጋጤ እና ሐዘን ነበር የተሰማን። የሚታገልለት ጉዳይ ትኩረት እንዲያገኝ ይህ ብቸኛው እርምጃ እንደሆነ ተሰምቶት ነበር” ሲል በቅርበት የሚያውቀው ሜሰን እስካሚላ በሳን አንቶኒዮ ፓርክ አሮንን ለማሰብ በተካሄደው የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት በፊት ተናግሯል።

“ይህንን እርምጃ መምረጡ ከባድ ነው። ለፍልስጤም ሕዝብ ለሚጨነቁ እና ለሚራሩ እንኳን ሁኔታውን ለመቀበል ከባድ ነው” ይላል።
በሻማ የማብራት ሥነ ሥርዓቱ ላይ ፍልስጤማውያንን ጨምሮ ቢያንስ 200 ሰዎች ተገኝተው ነበር። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኙትም ጓደኞቹም የአሮን ሕይወትን ለማስታወስ እና ሐዘናቸውን በመግለጽ ንግግር አድርገዋል።
ከዚያች እሁድ በፊት አሮን “ብዙም ባይናገር ተግባቢ፣ ቀልድ የሚወድ” እንደሆነ ነበር ሜሰን የሚያውቀው።
ሩት ቢር የተሰኘውን ለስላሳ የሚወድ፣ የግራ ዘመም ርዕዮተ ዓለም ያለው እንዲሁም ቤት አልባዎችን ከሚረዱ ቡድኖች ጋር በፈቃደኝነት የሚሠራ ነበር። የአየር ኃይል አባሉ ሹገር (ስኳር) የምትባል ድመት ነበረችው፤ እንዲሁም ሎርድ ኦፍ ዘሪንግስን ፊልምንም ይወድ እንደነበር ሜሰን ያስታውሳል።
ሙን የተባለው ሌላኛው ጓደኛው ከአሮን ጋር የተገናኙት በበጎ ፈቃድ ሥራ በሚሳተፉበት ወቅት ሲሆን፣ አሮንንም የሚገልጸው “ጠንካራ ዓላማ ያለው ሰው እንደሆነ ነው።”
የሕይወቱ የመጨረሻ የሆነውን ቪዲዮ “ለማየት በጣም ፈታኝ ነበር” ብሏል።
የሻማ የማብራት ሥነ ሥርዓቱ ላይ የተገኘችው የ32 ዓመቷ ፍልስጤማዊት አስተባባሪ ሳራ ማስዑድ የአሮን ሞት መስማት “በእውነቱ በጣም አሳዛኝ ነው” ትላለች።
አሮን የፈጸመው አስደንጋጭ ድርጊት “ራሱን ለማቃጠል የገፋፋው አሳዛኝ ሁኔታ” በብዙ አክቲስቶች ዘንድ መወያያ እንደሆነም ትናገራለች።
አሮን አናርኪስት ነበር “ሁሉም የሥልጣን ተዋረድ እና ልዩነት ሕጋዊ በሆነ መንገድ ሊፈርስ እንደሚገባም” በአንድ ወቅት ጽፎ ነበር።
በሳን አንቶኒዮ ይኖር በነበረበት ወቅት በተለያዩ ማኅበረሰባዊ ድርጅቶች እና የእርዳታ ቡድኖች ንቁ ተሳትፎ የነበረው ሲሆን፣ በተለይም ቤት የሌላቸውን በመርዳት ቀዳሚ ተሰላፊ እንደነበር ጓደኞቹ ይናገራሉ።
ከበርካታ ከሚረዳቸው ጋርም ጥብቅ ቁርኝት እንደመሠረተም ሜሰን ያሰረዳል።

አሮን በወታደራዊ አገልግሎቱ እና በፖለቲካዊ እምነቱ ባለው ቅራኔ ምክንያት ከፍተኛ ውጥረት ይሰማው እንደነበር ሜሰን ይናገራል።
አስርት ዓመታትን ያስቆጠረው የእስራኤል እና የፍልስጤም ጉዳይ ከወራት በፊት ሲፈነዳ አሮን በወታደራዊ አገልግሎት ውስጥ ነበር።
ሐማስ መስከረም መጨረሻ ላይ በደቡባዊ እስራኤል ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ 1 200 ሰዎች ተገድለዋል። 250 የሚጠጉ ታጋቾችም ወስደዋል።
እስራኤል አጸፋዊ ነው በምትለው የማያባራ ምላሽ ህንጻዎች ፈራርሰው ወድመዋል። በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን በህንጻዎች ስር ተቀብረዋል።
እስራኤል ጋዛን በሙሉ ከበባ ውስጥ ያስገባቻት ሲሆን፣ በረሃብ ህጻናት እየሞቱ እንደሆነ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል። ሐማስን ለማጥፋት ነው በሚልም ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጋ ሕዝብ ለመፈናቀል ተገዷል።
አሮን የፍልስጤም ደጋፊ እንዲሁም ከአካባቢው የመብት ተሟጋች ቡድኖች ጋር ቁርኝት ቢኖረውም በጋዛ እየተፈጸመ ያለውን ጥቃት በመቃወም ሕይወቱን ያጠፋል ብሎ የጠበቀ አልነበረም።

የፎቶው ባለመብት, Friends of Aaron Bushnell
የአሮን ውልደት እና እድገት
አሮን ተወልዶ ያደገው በኦርሊንስ፣ ማሳቹስቴስ ውስጥ ነው።
እንደ ጓደኞቹ ከሆነ ያደገው ‘የኢየሱስ ማኅበረሰብ’ [ኮሙዩኒቲ ኦፍ ጂሰስ] በመባ የሚታወቅ ጥብቅ የሃይማኖት ማኅበረሰብ ውስጥ ነው።
የልጅነት ጓደኛው አሽሊ ሹማን ለኒው ዮርክ ታይምስ እንደገለጸችው በአውሮፓውያኑ 2019 ማኅበረሰቡን ትቶ እንደወጣ ነግሯታል።
አሮን ከኢየሱስ ማኅበረሰብ ብቻ ሳይሆን ራሱንም ከቤተሰቡ አግልሎ እንደነበር ሜሰን ለቢቢሲ አስረድቷል።
አንዳንድ የቀድሞ የማኅበረሰቡ አባላት የሥነ ልቦና ጥቃት እንደደረሰባቸው በአውሮፓውያኑ 2021 ኤቢሲ በሠራው የምርመራ ዘገባ ተካቷል።
ቢቢሲ የአሮን ወላጆች እንዲሁም የማኅበረሰቡ አባላት እና የቀድሞ የማኅበረሰቡ ሠራተኛን አስተያየት ጠይቆ የነበረ ቢሆንም ሁሉም ጥያቄውን ውድቅ አድርገውታል።
አሮን በታዳጊነቱ ስፕሪት ዊንተር ፐርከሺን የተባለ የትርዒት ቡድን አባል ነበር። ከስድስት ዓመት በፊትም ደማቅ ዩኒፎርም ለብሰው ባሸበረቁ አባላት መካከል አሮን ፈገግ ብሎ የተነሳው ፎቶ በፌስ ቡክ ገጹ ላይ አለ።
“በዚያን ወቅት ከስፖርት፣ ከሙዚቃ እና ከመሳሳሉት ርዕሶች ውጪ ብዙም አያወራም ነበር” ሲል የቡድኑ አባል የነበረው ብርያን ስፔንሰር ለቢቢሲ ተናግሯል።
“ሁልጊዜም ጥሩ ሰው ነበር። እርዳታ ለሚፈልግ በሙሉ ቀድሞ ደራሽ ነበር” ሲልም ያስረዳል።
አሮን ከአውሮፓውያኑ 2020 ጀምሮ የአሜሪካ አየር ኃይል አባልነት አገልግሏል። የቅርብ ጊዜ የስራ ድርሻውም በሳይበር መከላከያ ውስጥ ነበር። ባለፈው ዓመት መገባደጃ ላይ ሳን አንቶኒዮን ለቆ ከወጣ በኋላ እስከ ሞቱ ድረስ በኦሃዮ ይኖር እንደነበር ጓደኞቹ ያስረዳሉ።
ጆርጅ በሊንክደን ገጹ ላይም ወታደራዊ ሰራተኞች የአገልግሎት ጊዜያቸው ከተጠናቀቀ በኋላ ወደ ሲቪል ስራ እንዲሸጋገሩ በሚያስችለው ስኪል ብሪጅ ውስጥ መካተት እንደሚፈልግ ጽፏል።
አሮን የአሜሪካ የአየር ኃይል የዕድሜ ልክ አባል ነበር።
“በአየር ኃይል አባሉ አሮን ቡሽኔል ሞት የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን ለቤተሰቦቹ እና ለወዳጆቹ እንገልጻለን” ሲሉም የአሜሪካ የአየር ኃይል አባሉ ኮሎኔል ሴሊና ኖይስ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል።
ለአሮን መታሰቢያ በተካሄደው የሻማ ማብራት ሥነ ሥርዓት ላይ ጓደኞቹ ያምንባቸው ለነበሩ ነገሮች ትኩረት በመስጠት አስበውታል።
በዚህ ሥነ ሥርዓትም ላይ ከአሮን ጋር በበጎ ፈቃደኝነት ትሠራ የነበረች ሴት ስለአሮን “ብዙ አሳዛኝ ነገሮችን ትሰማለህ ነገር ግን በጣም ብዙ ታላላቅ ጉዳዮችንም ትሰማለህ” ብላለች።
“ምክንያቱም ይህች የመጨረሻው እሳት የተቃጠለበት ወቅት የሕይወቱ ድምር አልነበረም” ስትልም ተናግራለች።












