ሚስቱን እና ሦስት ልጆቹን ጨምሮ 103 ዘመዶቹን ያጣው ፍልስጤማዊ አባት

አህመድ አል-ጉፈሪ
የምስሉ መግለጫ, አሕመድ አል-ጉፈሪ

እስራኤል በጋዛ ላይ እያካሄደችው ባለው ወታደራዊ ዘመቻ ምክንያት የአሕመድ አል-ጉፈሪ ቤተሰቦች ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ አልቀዋል።

በጋዛ ከተማ በቤተሰቦቹ ላይ በተፈጸመ ጥቃት 103 ዘመዶቹ ተገድለዋል። እሱ የተረፈው 80 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው በዌስት ባንኳ ኢያሪኮ ከተማ ስለነበረ ነው።

መስከረም 26 ሐማስ ወደ እስራኤል ድንበር ዘልቆ ጥቃት ሲፈጸም አሕመድ ቴል አቪቭ ውስጥ በግንባታ ሥራ ላይ ነበር። ጥቃቱን ተከከትሎ ጦርነት ተከፈተ። በእስራኤል ጦርም እገዳ ተጣለ። ይህም ወደ ሚስቱ እና ሦስት ሴት ልጆቹ እንዳይመለስ አደረገው።

ስልክ ከሠራ ሁሉንም ቤተሰቦቹን አንድ ላይ ያናግራል። ቤተሰቡ ላይ ኅዳር 25 ነበር ጥቃት የተፈጸመው። በዕለቱ አሕመድ ሚስቱ ሺረንን አናግሯታል።

“እንደምትሞት አውቃው ነበር። በእኔ ላይ ላደረገችው መጥፎ ነገር ሁሉ ይቅር እንድላት ጠየቀችኝ። እንደዚህ ማለት እንደማያስፈልግ ነገርኳት። ይህ የመጨረሻው ንግግራችን ነበር” ብሏል።

ማምሻውን በአጎቱ ቤት ላይ በደረሰ የቦምብ ጥቃት ሚስቱ እና ሦስት ሴት ልጆቹን - ታላ፣ ላና እና ናጅላ ተገደሉ።

የአሕመድ እናት፣ አራት ወንድሞቹ እና ቤተሰቦቻቸው እንዲሁም በርካታ አክስቶቹ፣ አጎቶቹ እና የአጎቶቹ ልጆች ተገደሉ። በአጠቃላይ ከ100 በላይ ቤተዘመዶቹ ተገድለዋል። ይህ ከሆነ ሁለት ወራት ቢያልፉም የአንዳንዶቹ አስከሬን ከፍርስራስ ውስጥ አልወጣም።

ባለፈው ሳምንት የመጨረሻ ልጁን ልደት አክብሯል። ናጅላ ሁለት ዓመት ይሞላት ነበር። አሕመድ ከእውነታው ጋር በመታረቅ ለመረዳት እየሞከረ ነው።

የልጆቹን አስከሬን ለማቀፍም ሆነ በችኮላ በተከናወነው ቀብራቸው ላይ ለመገኘትም አልታደለም። ይህ ሁሉ ተደማምሮ ፊቱ ካራሰው እንባው ውጪ የሚነበብ ምንም ስሜት የለም።

“ሴቶች ልጆቼ ለእኔ ትናንሽ ወፎች ነበሩ። ህልም ላይ እንደሆንኩ ነው የሚሰማኝ። በእኛ ላይ የደረሰውን ማመን አልቻልኩም” ብሏል።

አህመድ እና ሦስት ሴት ልጆቹ ታላ፣ ላና እና ናጅላ

ትዝታቸውን ፍራቻ የልጆቹን ፎቶዎች ከስልኩ እና ከላፕቶፑ ላይ አጥፍቷል።

ከተረፉት ጥቂት ዘመዶቹ እና ጎረቤቶቹ የሚሰማውን መረጃ በመገጣጠም የተፈጠረውን ታሪክ ለመረዳት ይሞክራል።

መጀመሪያ የቤተሰቡ ቤት መግቢያ ነበር በሚሳኤል የተመታው።

“ፈጥነው በአቅራቢያው ወዳለው የአጎቴ ቤት ተሸሸጉ። ከአስራ አምስት ደቂቃ በኋላ ተዋጊ ጄት ቤቱን መታው።”

ቤተሰቡ የተገደሉበት ባለ አራት ፎቅ ህንጻ በጋዛ ከተማ ዘይቱን በሚባለው ሰፈር የሚገኘው ነው። በአቅራቢያው ሰሃባ የህክምና ማዕከል ይገኛል።

አሁን አካባቢው በፈራረሱ ኮንክሪቶች ተሞልቷል። የፕላስቲክ ኩባያ እና በአቧራ የተሸፈነ ልብስ እዚህም እዚያም ተጥሎ ይታያል።

የአህመድ ቤተሰቦች ተገደሉበት ቤት
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የተሰባበረ መኪና በተንጠለጠሉ የኮንክሪት ፍርስራሾች ስር ተቀምጧል።

በሕይወት ከተረፉ የአሕመድ ዘመዶች አንዱ ሃሚድ አል ጉፉሪ ነው። ጥቃቱ ሲጀመር ሌላ ቦታ የሸሹት መትረፋቸውን እና በቤቱ ውስጥ የተጠለሉት መገደላቸውን ሃሚድ ለቢቢሲ ተናግሯል።

“የማያባራ እሳት ነው የዘነበው። ከአጠገባችን ባሉት አራት ቤቶች ላይም ጥቃት ተፈጸመ። በየ10 ደቂቃው ልዩነት ቤቶችን እየመቱ ነበር።”

“110 ከሚሆኑት የጉፈሪ ቤተሰቦች ከጥቂቶቹ በስተቀር ሁሉም ተገድለዋል።”

የ98 ዓመቷን አያት ጨምሮ ከዘጠኝ ቀናት በፊት የተወለደች ልጅ በጥቃቱ ተገድለዋል።

አሕመድ የሚባል የአጎቱ ልጅ በአየር ድብደባው ሁለት ትላልቅ ፍንዳታዎች መፈጠራቸውን ገልጿል።

“ምንም ቅድመ ማስጠንቀቂያ አልነበረም። [አንዳንድ] ሰዎች ይህን አካባቢ ለቀው ባይወጡ ኖሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ይገደሉ ነበር ብዬ አስባለሁ።

“አካባቢው አሁን ፍጹም የተለየ ቦታ ይመስላል። በአካባቢው የመኪና ማቆሚያ ቦታ፣ ውሃ የሚከማችበት ቦታ፣ ሦስት ቤቶች እና አንድ ትልቅ ቤት ነበር። ፍንዳታው አካባቢውን በሙሉ የደመሰሰ ነው” ብሏል።

ሃሚድ እንደገለጸው ከሆነ በሕይወት የተረፉት ሰዎች አስከሬኖችን ከፍርስራሹ ስር ለማንሳት እስከ ማለዳ ድረስ ለፍተዋል።

አሕመድ የሚባለው የአጎቱ ልጅ “አውሮፕላኖች በሰማይ ላይ እያንዣበቡ ነበር። አስከሬን ለማውጣት ስንሞክር እየተኮሱብን ነበር” ብሏል።

“ቤት ውስጥ ተቀምጠን ሳለ ነው ራሳችንን ከፍርስራሹ ስር ያገኘነው” ሲሉ ኡሙ አሕመድ አል ጉፈሪ ለቢቢሲ ተናግረዋል። “ከአንድ ጥግ ወደ ሌላው ተወረወርኩ። እንዴት እንዳወጡኝ አላውቅም። ሞትን ፊት ለፊት ተመልክተነዋል” ብለዋል።

ከሁለት ወር ተኩል በኋላም ከፍርስራሹ ስር የተቀበሩትን አንዳንድ አስከሬኖች ለማውጣት እየሞከሩ ነው። ቤተሰቡ ገንዘብ በማሰባሰብ ቆፋሪ ቀጥሮ ፍርስራሹን ለማንሳት የተቻላቸውን በማድረግ ላይ ናቸው።

“የወንድሜን ሚስት እና የወንድሜ ልጅ መሐመድን ጨምሮ አራት አስከሬኖችን አውጥተናል። አስከሬናቸው ለ75 ቀናት በፍርስራሹ ውስጥ ቆይቷል” ሲል አሕመድ ለቢቢሲ ተናግሯል።

በጊዜያዊነት በአቅራቢያው በሚገኝ ባዶ መሬት ላይ እንዲቀበሩ ተደርጓል። ቦታው በአንጨት እና በፕላስቲክ ምልክት ተደርጎበታል።

አሕመድ ከኢያሪኮ መውጣት አልቻለም። የተረፉትን ቤተሰቦቹንም ሆነ የመቃብር ቦታውን አልጎበኘም።

“እናቴን፣ ባለቤቴን፣ ልጆቼን እና ወንድሞቼን የሚያስነጥቅ ምን ተግባር ፈጸምኩ? ሁሉም ሲቪሎች ናቸው” ብሏል።

ነዋሪዎች የተቀበሩ ሰዎችን ለማግኘት በእጃቸው ፍርስራሾችን ሲያነሱ

ይህ ሁሉ ቤተሰብ ያለቀበትን የአየር ጥቃትን በተመለከተ የእስራኤል ጦርን ጠይቀን ነበር። ጦሩ ስለጉዳዩ እንደማያውቅ ገልጾ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት ከሐማስ ጋር በሚያደርገው ጦርነት የዜጎችን ጉዳት ለመቀነስ “በቂ ጥንቃቄዎችን አድርጓል” ብሏል።

ከአል-ጉፈሪ ቤት በስተደቡብ በሚገኘው በሸጃያ አካባቢ፤ የአሕመድ ቤተቦች ከመገደላቸው በፊት እና በኋላ ባሉት ቀናት በእስራኤል ወታደሮች እና በሐማስ ታጣቂዎች መካከል ከፍተኛ ጦርነት ተካሂዶ ነበር።

ጦሩ ኅዳር 26 ባወጣው ዕለታዊ መግለጫው፤ በሸጃያ ሠራዊቱ ላይ ያነጣጠሩ ናቸው የተባሉትን “ፀረ ታንክ ሚሳኤሎች የታጠቁ በርካታ አሸባሪዎችን ለይቼ” በሄሊኮፕተር እንዲመቱ አድርጌያለሁ ብሏል።

የአስራኤል አየር ኃይል ተዋጊ ጄቶች በጋዛ ሰርጥ የሚገኙ የሽብር ዒላማዎችን ሲመቱ መቆየታቸውንም ገልጿል።

በአንድ ወቅት የቤተሰቡ ቤት የነበረበት የዘይቱን አካባቢ አሁን በእስራኤል ጦር አዲስ ዘመቻ ተከፍቶበታል።

በኢያሪኮ የሚገኘው አሕመድ አንዳንድ ጊዜ በጋዛ ያሉትን ዘመዶቹ ዘንድ ስልክ ይደውላል። ወደ ሚወደው ቤቱ እንዳይመለስ ታግዷል። እመለሳለሁ የሚል ተስፋ ቢኖረውም እርግጠኛ ግን ሆኖ አያውቅም።

“ህልሜ በጋዛ ተቀብሯል። ማንን ብዬ ተመልሼ ልሂድ? ማን አባባ ብሎ ይጠራኛል? ማን ነው ውዴ የሚለኝ? ሚስቴ ሕይወቷን ሙሉ ውዴ ትለኝ ነበር። አሁን ማን ይጠራኛል?" ብሏል።