ጋዛ፡ በስልክ እርዳታ ስትማጸን የነበረችው የ6 ዓመት ታዳጊ ሕይወቷ አልፎ ተገኘ

የ6 ዓመት ታዳጊ ሂንድ

የፎቶው ባለመብት, RAJAB FAMILY

የምስሉ መግለጫ, የ6 ዓመት ታዳጊ ሂንድ

ባለፈው ወር በጋዛ የጠፋችው የ6 ዓመቷ ታዳጊ ከእስራኤል የታንክ ድብደባ በኋላ ከበርካታ ዘመዶቿ እና ከሁለት የእርዳታ ሰራተኞች ጋር ሞታ ተገኝታለች።

ታዳጊዋ ሂንድ ራጃብ ከአክስቷ፣ ከአጎት እና ከሦስት ልጆቻቸው ጋር በመኪና ጋዛን ጥለው በመሸሽ ላይ ነበሩ።

በታዳጊዋ እና በአደጋ ጊዜ ሰራተኞች መካከል የነበረ የድምጽ ቅጂ፣ በመኪና ውስጥ የነበሩት በሙሉ ተገድለው እንደነበር እና ሂንድ በእነሱ አስክሬን ውስጥ ከእስራኤል ኃይሎች ተደብቃ እንደነበር አመላክቷል።

የታዳጊዋ የስልክ እርዳታ ተማጽኖ የተኩስ ደምጽ ከተሰማ በኋላ ተቋርጧል።

ይህ ከሆነ ከቀናት በኋላ፣ የውጊያ ቀጠና በመሆኑ ተዘግቶ ወደ ነበረው ቦታ የፍልስጤም የቀይ ጨረቃ ማኅበር ተጉዘው የታዳጊዋን እና የቤተሰቦቿን አስክሬን አግኝተዋል።

ባለፈው ቅዳሜ ወደ ስፍራው የተጓዙት የእርዳታ ሰራተኞች፣ ሂንዳ እና ቤተሰቦቿ የተጓዙበት ተሽከርካሪ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ተመልክተዋል።

አንድ የእርዳታ ሰራተኛ ሂንዳ ቤተሰቦቿ በተኩስ እና የመሳሪያ ድብደባ ስለመገደላቸው የሚያሳዩ ምልክቶች አሉ ብሏል።

ሂንድ የነበረችበት ተሽከርካሪ

ታዳጊዋ ከነበረችበት ተሽከርካሪ ጥቂት ሜትሮች ራቅ ብሎ ሙሉ በሙሉ የወደመ ተሽከርካሪ ቅሪት የተገኘ ሲሆን የቀይ ጨረቃ ማኅበሩ ሂንዱን ለመታደግ የተላከ አምቡላንሰ እንደነበር አስታውቋል።

በተሽከርካሪው ውስጥ የነበሩት ሁለት የእርዳታ ሰራተኞች በእስራኤል ቦምብ ድብደባ መገዳላቸውንም ማኅበሩ ገልጿል።

ማኅበሩ ባወጣው መግለጫ አምቡላንሱ ልክ እንደደረሰ የእስራኤል ጦር ሆን ብሎ ጥቃት እንዳደረሰበት ጠቁሟል።

ማኅበሩ የወደመውን አምቡላንስ ወደ ሂንድ ለመላክ የእስራኤል ጦር እክል በመፍጠሩ ሰዓታት እንደፈጀ ለቢቢሲ ገልጿል።

ቀይ ጨርቃ ማኅበሩ የኔ ነው ያለው አምቡላንስ ከደረሰበት ጥቃት በኋላ
የምስሉ መግለጫ, ቀይ ጨርቃ ማኅበሩ የኔ ነው ያለው አምቡላንስ ከደረሰበት ጥቃት በኋላ

አምቡላንሱ የ6 ዓመቷን ታዳጊ እንዲታደግ ፍቃድ እንዳገኘ የማኅበሩ ቃል አቃባይ ኒባል ፋራስካ ተናግራለች።

ሆኖም አምቡላንሱ መድረሱን እና ታዳጊዋ ያለችበትን ተሽከርካሪ እንደተመለከቱ ከተናገሩ በኋላ “የሰማነው የተኩስ ደምጽ ነው” ብላለች።

ታዳጊዋ ከእርዳታ ሰራተኞቹ ጋር ያደረገችውን የስልክ ልውውጥ ቅጂ የቀይ ጨረቃ ማኅበሩ ለሕዝብ ያደረሰው ሲሆን ሂንድ ላይ የተፈጠረው ምን እንደሆነ የሚጠይቅ ዘመቻን ቀስቅሷል።

የሂንድ እናት የልጇን መሞት ከማረጋገጧ በፊት መምጣቷን በጉጉት ስትጠብቅ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግራለች።

አሁን ደግሞ ለዚህ ጥፋት ተጠያቂ የሚሆን ሰው መኖር እንዳለበት ተናግራለች።

“አንድ ቀን በፈጣሪ ፊት እፋረዳቸዋለሁ” ያለችው የሂንድ እናት “ኔታኒያሁ፣ ባይደን እና ሌሎች እኛ ላይ የተባበራችሁ፣ ጋዛ እና ሕዝቦቿ ላይ የተባበራችሁ ፈጣሪ የእጃችሁን እንዲሰጣችሁ ከልቤ እጸልያለሁ” ስትል ለቢቢሲ ገልጻለች።

የልጇን መምጣት ሆስፒታል ሆና ስትጠባበቅ የነበረችው እና ከሞቷ ዜና በኋላም ለልጇ ይዛ የነበረውን ሮዝ ቦርሳ ይዛው ታይታለች። በቦርሳው ወስጥ ሂንድ የእጅ ጽሑፍ የምትለማመድበትን ደብተር ይዛበት ነበር።

“ምን ያህል እናቶች ይህ ስቃይ እንዲደርስባቸው እየጠበቃችሁ ነው? ምን ያህል ህጻናት እንዲገደሉ ነው የምትፈልጉት?” ሰትልም ጠይቃለች።

ቢቢሲ ስለጉዳዩ የእስራኤል ጦርን ሁለት ጊዜ የጠየቀ ሲሆን ሁኔታውን እያጣራሁ ነው ብሏል።

እስራኤል ቀደም ብላ ሀማስ አምቡላንሶችን እንደ መሸሸጊያ ይጠቀማል ስትል ከሳለች።