ለሕይወቴ እሰጋለሁ ያለችው የዱባይ ገዢ ቤተሰብ አባል የቀድሞ ሚስት የተመድን ድጋፍ ጠየቀች

የዱባይ ገዢ የቤተሰብ አባል የሆነው ግለሰብ የቀድሞ ሚስት ጠበቆች የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ድጋፍን ጠየቁ።
ጠበቆቹ የመንግሥታቱ ድርጅት ጣልቃ ገብቶ የደንበኛቸውን ዘይነብ ጃቫድሊ እና ልጆቿ ደኅንነትን የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ባለሥልጣናት እንዲያረጋግጡ ጠይቀዋል።
በጠቆቹ የቀረበው ክስ እንደሚያመለክተው ከሆነ ጃቫድሊ ከሼክ ሰዒድ ቢን ማክቱም ቢን ራሺድ አል ማክቱም ጋር ከተለያየች በኋላ፣ ያፈሯቸውን ልጆች ማን ያሳድግ በሚል በፍርድ ቤት ክርክር በመግጠሟ ማስፈራሪያ እና ትንኮሳ እየደረሰባት ነው።
የሼክ ሰዒድ ቢን አል ማክቱም ጠበቆች ግን “ጃቫድሊ የእናትነት ኃላፊነትን ለመወጣት ብቁ የሆነች ሴት አይደለችም” በማለት ምንም አይነት የመብት ጥሰት አልተፈጸመባትም ብለዋል።
ቢቢሲ እጅ የገባ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ጃቫድሊ፤ “እባካችሁ እርዱኝ” ስትል ትታያለች። “እኔ እና ልጆቼ ለሕይወታችን እና ለደኅንነታችን ሰግተናል። . . . ቤት አልባ ሆነን ዱባይ ውስጥ ባለ ሆቴል ውስጥ እንገኛለን” በማለት ትናገራለች።
ከአዘርባጃን የሆነችው እና በአሁኑ ወቅት በዱባይ የምትገኘው የ31 ዓመቷ ጃቭድሊ፣ ትዳሯ እአአ 2019 ላይ ከፈረሰ በኋላ ከዱባይ አልወጣችም።
እርሷ እንደምትለው ከሆነ ከዱባይ ከወጣች ሦስት ሕጻናት ልጆቿን መልሳ ላታይ ስለምትችል እዚያው መቆየትን መርጣለች።
ጃቫልዲ ባለፉት ሦስት ዓመታት ልጆቻቸውን ማን ያሳድግ በሚል ከቀድሞ ባሏ ጋር በፍርድ ቤት ስትከራከር ቆይታለች።
ሼክ ሰዒድ ቢን ማክቱም ቢን ራሺድ አል ማክቱም የዱባይ ገዢ ቤተሰብ አባል ሲሆኑ፣ የዱባይ ገዢ የሼክ ሞሐመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም የወንድም ልጅ ናቸው።
ጥንዶቹ እአአ 2015 ላይ ከተጋቡ በኋላ ኑሯቸውን በዱባይ አድርገው ነበር።
መቀመጫቸውን ዩናይትድ ኪንግደም ያደረጉት የጃቫልዲ ጠበቆች ለተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ባቀረቡት አቤቱታ ላይ ደንበኛቸው በነጻነት የምቀሳቀስም ሆነ ሃሳብን የመግለጽ መብት የተገደቡ ናቸው ብለዋል።
ይሄው ሰነድ ላይ ከሁለት ዓመት በፊት የዱባይ ፖሊስ የጃቫድሊ መኖሪያ ቤትን ሰብሮ ሲገባ በወላጆቿ እና በልጆቿ ላይ ጥቃት አድርሶ ነበር ይላል።
ጃቫድሊ ይህን ክስተት በቀጥታ ያስራጨች ሲሆን፣ ጉዳዩ ዓለም አቀፍ ትኩረትን እንዲስብ አድርጎም ነበር። ከዚህ ክስተት በኋላ የጃቫድሊ ወላጆች ወደ አዘርባጃን ተመልሰዋል።
ጃቫድሊ ባለፉት ሦስት ዓመታት ፖሊስ በመኖሪያ ቤቷ ላይ ብርበራ ማካሄድ፣ የፍርድ ቤት ጥሪ መቀበል እና እስር ቋሚ የሕይወቷ አካል መሆናቸውን ትገልጻለች።
ለመንግሥታቱ ድርጅት የቀረበው ባለ 50 ገጽ ሰነድ እንደሚለው ከሆነ፣ ትክክለኛ የፍርድ ሥርዓትን ባልተከተለ መልኩ ልጆቹን ሼክ ሰዒድ እንዲያሳድግ ተፈቅዶለታል።
የሼክ ሰይድ ጠበቆች በበኩላቸው ጉዳያቸውን ሲመለከት ለነበረው የዱባይ ፍርድ ቤት ሲናገሩ፤ ጃቫድሊ ለእናትነት ብቁ አይደለችም።
ጃቫድሊ ልጆቿን ትምህርት ቤት መላክ የተሳናት፣ ለሕይወት ምቹ ያልሆነ ቦታ ልጆቹን እያኖረች እንደሆነ እና የመጨረሻውን ልጅ ጤና አደጋ ላይ መጣሏን ጠበቆች ለፍርድ ቤት ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ጃቫድሊ ልጆቿ መልሳ ላታይ እንደምትችል ስጋት ስለገባት ልጆቿን ትምህርት ቤት አትልክም። እርሷ እና ጠበቆቿ እንደሚሉት የዱባይ ፍርድ ቤት የአሳዳጊነት ፍቃዱን ለሼክ ሰዒድ የሰጠው ብይን በየትኛውም ጊዜ ተፈጻሚ ሊሆን ይችላል።
ይህ ክስ በዱባይ ገዢዎች ቤተሰብ ውስጥ የተፈጠረው ሌላኛው አወዛጋቢ ጉዳይ ሆኗል።
ከዚህ ቀደም የዱባዩ ገዢ ሼክ ሞሐመድ ቢን ራሺድ አል ማክቱም የቀድሞ ባለቤት ልዕልት ሃያ ለሕይወቴ እሰጋለሁ በማለት እአአ 2019 ላይ ዩናይትድ አረብ ኤሜሬቶችን ጥላ መሰደዷ ይታወሳል።
ከዚህ በኋላ ደግሞ የዱባዩ ገዢ ሴት ልጅ ሌላኛዋ ትልቅ መነጋገሪ ሆና ቆይታለች። ልዕልት ላቲፋ ነጻነትን ፍለጋ እአአ 2018 ላይ በጀልባ ልታመልጥ ስትሞክር ሕንድ ውቅያኖስ ላይ ተይዛ ወደ ዱባይ ተመልሳ ነበር።
ቀጥሎም ሾልኮ በወጣ ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ልዕልት ላቲፋ ከፍላጎቷ ውጪ እቅስቃሴዋ ተገድቦ እየኖረች እንደሆነ ተናግራ ነበር።
ከዚህ በኋላ ደግሞ በቀረበችባች ቪዲዮች ጤናዋ ተጠብቆ የምትመኝበትን ሕይወት እየኖረች እንደሆነ ተናግራ ነበር።












