ተጠናክሮ በቀጠለው የኤርትራ አፈሳ ‘ቤቶች እና የንግድ ድርጅቶች እየታሸጉ ነው’ ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በቅርቡ በኤርትራ መንግሥት የቀረበውን ክተት ጥሪ ተከትሎ እየተካሄደ ያለው አፈሳ በተጠናከረ ሁኔታ እንደቀጠለ ምንጮች ለቢቢሲ ገለጹ።
ኤርትራ የሚገኙ የቢቢሲ ምንጮች በተለይም በአሥመራ እና በሌሎችም አካባቢዎች ከቅርብ ቀናት ወዲህ የቤት ለቤት ፍተሻ፣ የንግድና የመኖሪያ ቤቶች ማሸግ እንዲሁም ተሽከርካሪዎችን ማስቆም በስፋት እየታየ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም መንግሥት ያወጣውን ጥሪ ተግባራዊ ያላደረጉ ሰዎችን የማፈሱ ተግባርም በተጠናከረ ሁኔታ እየተፈጸመ መሆኑን አስረድተዋል።
ይህ ሰፊ ዘመቻ “ከሠራዊቱ የከዱ እና የተጠባባቂ ኃይል አባላት ወደ ግንባር እንዲከቱ ለቀረበው ጥሪ ምላሽ ያልሰጡትን ለማደን ነው” በማለትም ለደኅንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ምንጮቻችን ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ልጆቻቸው በብሔራዊ አገልግሎት ሥልጠና ያልተሳተፉ ቤተሰቦች ልጆቻቸውን የሚጠበቅባቸውን ግዴታ እንዲወጡ ካላስረከቡ ቤታቸው እንደሚታሸግ ተነግሯቸዋል።
በርካታ ወጣቶች፣ ለረዥም ጊዜ በህመም ላይ ያሉ ግለሰቦች ሳይቀር ወላጆቻቸው ከሚሰቃዩና መኖሪያ ቤቶቻቸው ከሚታሸጉ በሚል ወደ ሠራዊቱ እየተቀላቀሉ ነው።
በዚህ ውስጥ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ያልሆኑት ደግሞ በየኮረብታ እና በየሸለቆው ተደብቀው እንደሚገኙ በተለያዩ የኤርትራ አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ለቢቢሲ አስረድተዋል።
ኤርትራ በቅርቡ ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በታች የሆኑ የአገሪቱ ተጠባባቂ ኃይል አባላት በአስቸኳይ ሪፖርት እንዲያደርጉ መንግሥት ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
በዚህም በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙና ከመደበኛው ሠራዊት ውጪ ያሉ የተጠባባቂው ኃይል አባላት ወደ ጦር ግንባር እንዲከቱ ተነግሯቸዋል።
ነገር ግን የኤርትራ የማስታወቂያ ሚኒስትር የሆኑት አቶ የማነ ገብረመስቀል ለአንድ የጀርመን ድረ ገጽ እንደተናገሩት፣ ለተጠባባቂው ኃይል የቀረበውን ጥሪ “ሆን ተብሎ እውነታው እንዲዛባ እና እንዲጋነን ተደርጓል” ብለዋል።
ሚኒስትሩ ጨምረውም መሬት ላይ ያለው እውነታ ሆን ተብሎ እንዲዛባ እና እንዲጋነን ተደርጓል በማለት “የተወሰኑ የተጠባባቂ ኃይል አባላት የተጠሩ ቢሆንም ቁጥራቸው በጣም ጥቂት ነው” ነው ሲሉ አስተባብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Socia Media
ሆኖም ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በታች ብቻ ሳይሆን 60 እና ከዚያ በላይ የሆኑ የእድሜ ባለጸጎች ሳይቀር እንዲቀላቀሉ መገደዳቸውም ይናገራሉ።
ከእነዚህም በተጨማሪ ጥሪውን ያልተቀበሉ ሴቶችም ጭምር እየታፈሱ እና መንገላታት እየተፈጸመባቸው መሆኑ ተገልጿል።
ከዚህ በፊት ኤርትራ ውስጥ አፈሳ የተለመደ ነገር ቢሆንም፣ በአብዛኞቹ አጋጣሚዎች ግን ሴቶችን የሚያስገድድ አልነበረም። በአሁኑ ወቅት ግን ሁኔታዎች ተቀይረዋል የሚሉት ነዋሪዎች፣ ሴቶችም በግዴታ እየተያዙ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የአፈሳውን አስከፊነት ለቢቢሲ የተናገሩ ነዋሪዎች እንዳስረዱት የጤና እክል ያለባቸው ነዋሪዎች በአንዳንድ የአሥመራ ከተማ አስተዳደራዊ ጽህፈት ቤቶች የህክምና ማስረጃቸውን ቢያቀርቡም “ጉዳያችሁ እዚያው ይታያል” በማለት በድንገት መኪና ላይ ተጭነው ተወስደዋል ብለዋል።
በከረን የሚኖር አንድ ኤርትራዊ አባቱ በህመም ምክንያት ለረጅም ዓመታት ከቤት መውጣት ሳይችሉ እንደቆዩና ከቤት አስወጥተው አስገድደው እንወሰዷቸው ለቢቢሲ ተናግሯል።
“አባቴ እጆቹ፣ እግሮች እና መላ አካሉ ነው የሚያንቀጠቅጠው። እሱን ለማሳከም ሞከረን ግን ኤርትራ ውስጥ ምንም አይነት ህክምና የለም። አሁን እሱ ምን ያደርግላቸዋል? አባቴ የጥይት ሰለባ እንዳይሆንብኝ ስጨነቅ መተኛት አልቻልኩም” ብሏል።
በከረን እና አካባቢዋም በከባድ ህመም እና በእርጅና ምክንያት ከሠራዊቱ በጡረታ የተገለሉ የዕድሜ ባለጸጋዎች ሳይቀሩ በአስገዳጅ መልኩ ወደ ሠራዊቱ እንዲቀላቀሉ መደረጉን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም. በፌደራል መንግሥትና በትግራይ ኃይሎች መካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት የኤርትራ ጦር ከፌደራል ኃይሎች ጋር በመወገን ተዋግቷል።
የትግራይን የተወሰኑ ስፍራዎችን ተቆጣጥሮ እንዳለ የሚገለጸው የኤርትራ ጦር መደፈር፣ የዘፈቀደ ግድያና እንደ ጦር ወንጀልና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ጥሰቶችን ትግራይ ውስጥ እንደፈጸመ በርካታ ሪፖርቶች አመልክተዋል።
ለአምስት ወራት የቆየውና ጦርነቱን ጋብ ያደረገው የሰብዓዊ ተኩስ አቁም ስምምነት ፈርሶ ጦርነቱ ካገረሸ በኋላ የኤርትራ ጦር ተሳታፊ እንደሆነና በተለያዩ ግንባሮችም እየተዋጋ መሆኑ ተነግሯል።
ኤርትራ እና ኢትዮጵያ በሚዋሰኑበት ድንበር ላይ ከፍተኛ የጦር ሠራዊት እና የጦር መሳሪያ ክምችት እንዳለም የሳተላይት ምስሎች አሳይተዋል።
በተለይም የጦርነቱ ማገርሸቱን ተከትሎ በሁሉም የኤርትራ አካባቢዎች በወጣቶች ላይ የሚደርሰው የግዳጅ አፈሳ ተጠናክሮ መቀጠሉን ቢቢሲ በኤርትራ ካሉ ነዋሪዎች ሰምቷል።
በብዙ የኤርትራ ገጠራማ አካባቢዎች ወደ ጦርነቱ እንዲከት የሚፈለገው ሰው በማይገኝበት ወቅት ወላጆቹን ከመኖሪያ ቤታቸው አውጥተው እንደሚቆልፉባቸው እና ከብቶቻቸውን በበረት እንደሚዘጉባቸው ሲነገር ቆይቷል።
“በገጠር አካባቢዎች ሲፈፅሙት የነበረ እንግልት በአሥመራ ከተማም ጀምረውታል። ወላጆችን በቀበሌ ኩፖን፣ ፈቃድና ሌሎች ሰበቦች ማሰቃየት ጀምረዋል” ሲል አንደኛው ነዋሪ ለቢቢሲ ተናግሯል።
በተጨማሪም “ሕዝቡን በቀበሌ እየሰበሰቡ በማደናገጥና በማስፈራራት ‘አሁን በመጨረሻው የኅልውና ደረጃ ላይ እንገኛለን፤ ወያኔ መቀበር አለበት፤ ልጆቻችሁን ካላመጣችሁ፣ በሚደርሰው መዘዝ ተጠያቂዎች ናችሁ’ በማለት ያስፈራሩታል” ብሏል።
የመኖሪያ ቤቶቻቸውን በማሸግ፣ የንግድ እና ሌሎች የፈቃድ እና መረጃዎች እንደሚወስዱባቸው ከማስፈራራት በተጨማሪ ተግባራዊ በማድረግ ሕዝቡን እያንገላቱት ነው ሲል ይኸው ነዋሪ ገልፆልናል።
በኤርትራ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆኑ በኤርትራ ያሉ እህት ወንድሞቻቸው እና ወላጆቻቸው ደኅንነት በከፍተኛ ሁኔታ እያስጨነቃቸው እንደሆነ የሚናገሩት በውጭ የሚኖሩ እና በቅርቡ ከአገሪቱ የተመለሱ ዜጎች የሚባለው አፈሳና እና እንግልት ትክክል መሆኑን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በዴንማርክ የሚኖርና ስሙ እንዳይገለፅ የፈለገ ኤርትራዊ የ67 ዓመት አዛውንት አባቱ ወደ ጦር ግንባር እንዲሄዱ ባይደረግም በእድሜ ሆነ በጤና እክል ምክንያት በከተሞች የቀሩት ጥቂት ሰዎች በመሆናቸው አካባቢያቸውን እንዲጠብቁ እያስገደዷቸው መሆኑን አስረድቷል።
ግለሰቡ አክሎም “የአባቴ ሁኔታ ጥሩ ነበር ነገር ግን ዋናው ጭንቀቴ የታናሽ እህቴ ጉዳይ ነው” ሲል ተናግሯል።
ታናሽ እህቱ ድንበር አቋርጣ ለመውጣት ስትሞክር ስለተያዘች አቆርደት በተሰኘ አካባቢ አቅራቢያ በሚገኘው ‘ኮርመናዕ’ በሚባለው ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ወታደራዊ ሥልጠና ስትወስድ እንደነበርና አሁን ግን ድምጿ መጥፋቱን ለቢቢሲ ገልጿል።
ወደ’ለዚና በሚለው ቅፅል ስሙ የሚታወቀውና በአንጎላ የሚኖር ሌላ ኤርትራዊ ከሞቱት እና ከተሰደዱት ወንድሞቹ ሌላ አንድ የተረፈ ወንድሙ ቤተሰቦቹን ሲንከባከብ ቆይቶ፣ በአሁኑ ወቅት ግን የት እንዳለ የሚታወቅ ነገር አለመኖሩ በጣም እንዳሳሰበው ተናግሯል።
“ቤት ድረስ እየመጡ ሚስቱን ሲያንገላቷት ስለቆዩ የያዙት አይመስለኝም። ቢይዙት አይመላለሱም ነበር። ቢሆንም ግን ‘እዚህ ነኝ’ አላለም። ሚስቱም ማስፈራራቱ ሲበዛባት ከብቶቹን ለወላጆቻችን ትታ ከልጆቿ ጋር ቤተሰብ ቤት ተደብቃለች” ብሏል።
ለብዙ ዓመታት በጣሊያን በስደት የኖረች እና ባለፈው ክረምት ወደ አሥመራ ደርሳ የተመለሰችው ሌላኛዋ ኤርትራዊት “ይህ እልቂት ብቻ ነው። በሕይወቴ ሙሉ ስለ ወንድሞቼ እና እህቶቼ እያሰብኩ እና እየተጨነቅኩ ኖሬያለሁ” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
“ድሮ በደርግ ዘመን የትግል ወቅት ወንድሞቼን ሳስብ፤ ነፃነት ከመጣ በኋላም ወደ ብሔራዊ አግልግሎት ስለሄዱት ወንድሞቼ ስጨነቅ፤ ከዚያም የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጦርነት ሲከትም ስለ ደኅንነታቸው ሳስብ መቼ እረፍት አገኘሁ?” በማለት ዛሬ ላይ ደግሞ የተሰዋው ወንድሟ ልጆች ጉዳይ ጭንቀት ውስጥ እንዳስገባት ታስረዳለች።
በተለይም ወታደራዊ ሥልጠና ከወሰደች በኋላ የራዲዮ ኦፕሬተር ሆና ካገለገለች በኋላ ከሠራዊቱ ኮብልላ ላለፉት ሁለት ዓመታት ቤቷ ውስጥ ስትኖር የቆየችው የወንድሟ ልጅ ጉዳይ ደጋግማ ታነሳለች።
በየቤቱ እየመጡ አፈሳውን የሚፈጽሙ የመንግሥት አካላት የወንድሟን ልጅ ስላጧት መኖሪያ ቤት በመቆለፍ ወላጆቻቸውን ማንገላታት ሲጀምሩ አማራጭ ስላጣች በመጨረሻ ውትድርና እንደተቀላቀለች ታስረዳለች።
ቢቢሲ ያነገረው ኤርትራ ውስጥ ነዋሪ ግለሰብ “ካድሬዎች ይህ የኅልውና ጉዳይ ነው፤ ወያኔ መቀበር ነው ያለባት” እያሉ ሕዝቡን ለማነሳሳት እየሞከሩ መሆኑን ያስረዳል።
“ዛሬ ላይ ያልዘመተ ወይም ልጆቹ እንዳይዘምቱ የደበቀ አልያም እንዲደበቁ የተባበረ ከባድ አገራዊ ክህደት እንደፈጸመ ነው የሚቆጠረው” እያሉ እንደሚያስፈራሩም ጨምሮ ገልጿል።
“ሕዝቡ ሁሉም ነገር መሮታል። እምቢተኝነቱን በተለያየ መንገድ እየገለፀ ነው። ሕዝቡ ጦርነቱን አይደግፈውም፣ አይፈልገውም። ነገር ግን የንግድ ድርጅቶችን እና መኖሪያ ቤቶችን ከማሸግ በተጨማሪ ታይቶ የማይታወቅ ግፍም ሊፈጽሙ ይችላሉ” ብሏል።












