በኤርትራ ዕድሜያቸው ከ55 በታች የሆኑ ተጠባባቂ ኃይሎች በአስቸኳይ ጦሩን እንዲቀላቀሉ ታዘዙ

የኤርትራ ጦር አባላት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የኤርትራ ጦር አባላት

በኤርትራ ዕድሜያቸው ከ55 ዓመት በታች የሆኑ ተጠባባቂ የጦር ኃይሉ አባላት በአስቸኳይ ሪፖርት እንዲያደርጉ የአገሪቱ መንግሥት ማሳሰቡን ምንጮች ለቢቢሲ ገለጹ።

የበተለያዩ የአገሪቱ ክፍል ውስጥ የሚገኙና ከመደበኛው ሠራዊት ውጪ ያሉ የተጠባባቂ ኃይሉ አባላት ናቸው ቀርበው ሪፖርት እንዲያደርጉ ጥሪ የቀረበላቸው።

ቢቢሲ ያናገራቸውና ለደኅንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈቀዱ ምንጮች እናዳሉት በርካቶች ሐሙስ መስከረም 05/2015 ዓ.ም. በመዲናዋ አሥስመራ እንደተሰባሰቡ ገልጸዋል።

እነዚህ ጥሪ የተደረገላቸው የተጠባባቂው ኃይል አባላት በአጭር ጊዜ ውስጥ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር ወደ ምትዋሰንበት እና የጦርነት ስጋት አለባቸው ወደተባሉ አካባቢዎች ሊጓዙ እንደሚችሉ ምንጮቹ ጨምረው ተናግረዋል።

የፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ አስተዳደር ይህን ጥሪ ማቅረቡ የተሰማው ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ዳግም ባገረሸበት ወቅትና በጦርነቱ የኤርትራ ጦር ተሳታፊ መሆኑ ህወሓትን ጨምሮ በተለያዩ ወገኖች እየተገለጸ ባለበት ወቅት ነው።

ከጥቂት ቀናት በፊት የትግራይ ኃይሎች አዛዥ ጄኔራል ታደሰ ወረደ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጥምር ጦር ሽራሮን ጨምሮ ሌሎች የትግራይ አካባቢዎችን መያዛቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።

ዋና አዛዡ ማክሰኞ መስከረም 03/2015 ዓ.ም. እየተካሄደ ያለውን ጦርነት አስመልክተው በሰጡት መግለጫ፣ ከኤርትራ ድንበር በኩል በከፍተኛ ቁጥር የመጣው የኤርትራ እና ኢትዮጵያ ሠራዊት ሽራሮን ተቆጣጥሯል ብለው ነበር።

በተጨማሪም የአውሮፓ ኅብረት ባገረሸው ጦርነት ላይ የኤርትራ ጦር ተሳታፊ መሆኑን ገልጾ፤ ጎረቤት አገር ኤርትራ በጦርነት ተሳታፊ መሆኗ በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም ለማምጣት ለሚደረገው ጥረት እንቅፋት ሆኖ ቀጥሏል ሲል ረቡዕ ዕለት ባወጣው መግለጫ ጠቅሶ ነበር።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የኤርትራ መንግሥት ስላቀረበው ጥሪ መረጃ ለቢቢሲ የሰጡ ነዋሪዎች እንዳሉት ከሆነ፤ ወደ ጦር ግንባር የሚያቀኑት የተጠባባቂ ኃይሉ አባላት እንደ ብርድ ልብስ እና የውሃ ኮዳ የመሳሰሉ መሠረታዊ የግል መገልገያዎችን ይዘው እንዲገኙም ማሳሰቢያ ተሰጥቷቸዋል።

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በመዲዋ አሥመራ ጨምሮ በበርካታ የአገሪቱ አካባቢዎች በኤርትራ በሚካሄደው የግዴታ ብሔራዊ አገልግሎት ያልተሳተፉ እና ከዚህ አገልግሎት የኮበለሉ ወጣቶችን ለመያዝ የፀጥታ ኃይሎች ቤት ለቤት አሰሳ እያካሄዱ እንደነበር መዘገባችን ይታወሳል።

በአሁኑ ወቅትም የመንግሥት የደኅንነት አባላት በጎዳናዎች ላይ የሚንሳቀሱ ሰዎችን በማስቆም በአስገዳጁ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ያላቸውን ተሳትፎ እና የማይመለከታቸው መሆኑን እያጣሩ እንደሚገኙ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።

ኤርትራውያን በጤና እና በተለያዩ ምክንያቶች መሳተፍ እንደማይችሉ ፈቃድ ካላገኙ በስተቀር ማንኛውም የአገሪቱ ወጣት ዜጋ በብሔራዊ አገልግሎቱ የመሳተፍ ግዴታ አለባቸው።

በርካታ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ቡድኖች አገሪቱ ወጣቶችን ማብቂያ ወደ ሌለው የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ብግዳጅ እያስገባች ሰብአዊ መብቶችን እየጣሰች ለው ሲሉ በተደጋጋሚ ሲወቅሱ መቆየታቸው ይታወቃል።

ኤርትራውያኑ በብሔራዊ አገልግሎት ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ የተወሰኑት በሠራዊቱ ውስጥ እንዲቆዩ፣ ሌሎች ደግሞ በመምህርነት ወይም በሌላ የመንግሥት ሥራ ላይ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲቆዩ ይደረጋል።

ቃላቸው ለቢቢሲ የሰጡ ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ አሁን ላይ እናቶች፣ ሕጻናት እና ሚስቶች፤ ልጆቻቸው፣ አባቶቻቸው፣ ወንድሞቻቸው እና ባሎቻቸው ወደ ብሔራዊው አገልግሎት እያለቀሱ ሲሸኙ መመልከት አዲስ ክስተት አይደለም።