አሜሪካ ፑቲን በዩክሬን ላይ የወሰዱትን የበቀል ጥቃት አወገዘች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ትናንት መስከረም 30፣ 2015 ዓ.ም ሩሲያ በዩክሬን ከተሞች ያደረሰችውን የሚሳኤል ጥቃት አሜሪካ ኮነነች።
ሩሲያ ኪየቭን ጨምሮ ቁልፍ የዩክሬን ከተሞች ላይ የሚሳኤል ጥቃት አድርሳለች።
ጥቃቱ ከደረሰባቸው ሥፍራዎች መካከል አንዳንዶቹ ወታደራዊ ዒላማ የሌላቸው ናቸው ተብሏል።
ከነዚህም መካከል አንድ ዩኒቨርስቲና አንድ የልጆች መጫወቻ ሜዳ ይገኝበታል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በዚህ ጥቃት ‘ክፉኛ ደንግጫለሁ’ ብለዋል።
ቭላድሚር ፑቲን የትናንቱ ጥቃት ዩክሬን ባለፈው ቅዳሜ በክራይሚያ ድልድይ ላይ ላደረሰችው ‘የሽብር ጥቃት’ በቀል እርምጃ ነው ብለዋል።
ዩክሬን እንዳለችው ትናንት ብቻ ከሩሲያ 83 ሚሳኤሎች መተኮሳቸውን እና ከነዚህ ውስጥ 43 መቀልበሳቸውን ተናግራለች።
‘አንበገርም’ የሚሉት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ ጥቃቱን ተከትሎ ለሕዝባቸው ባስተላለፉት የቪዲዮ መልእክት ‘እንዲህ ዓይነት ጥቃቶች ፍርሃት ውስጥ አይከቱንም፤ ይልቅ ይበልጥ ያጠናክሩናል።’ ብለዋል።
በትናንቱ ተከታታይ የሚሳኤል ጥቃት በትንሹ 14 ሰዎች ተገድለዋል። ከዚህ አሐዝ እጥፍ የሚሆኑ ደግሞ ቆስለዋል።
በርካታ ከተሞች የኤሌክትሪክ እና የዉሃ መቋረጥ አጋጥሟቸዋል። ይህም የሆነው የኃይል ማመንጫዎችና መሠረት ልማቶች ዒላማ በመደረጋቸው ነው።
የዩክሬን ዜጎች ሩሲያ ሆን ብላ በሥራ ቀን ሰው የሚበዛባቸው ስፍራዎች ላይ ጥቃት ሰንዝራለች ሲሉ ተናግረዋል።
ሚሳኤል ከወደቀባቸው አካባቢዎች መካከል ዩኒቨርስቲ፣ የሕጻናት መጫወቻ እና ታዋቂው የታራስ ሼቬንኮ ፓርክ ይገኝበታል።
የአውሮፓ ኅብረት ጥቃቱን አውግዞ የጦር ወንጀል ተፈጽሟል ብሏል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከፕሬዝዳንት ዘለንስኪ ጋር በስልክ ያወሩ ሲሆን ጥቃቱን ካወገዙ በኋላ መንግሥታቸው ለዩክሬን የሚያደርገውን ወታደራዊ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል።
ባይደን በተለይ ዩክሬን ከእንዲህ ዓይነቱ ጥቃት ራሷን መከላከል የሚያስችላትን የአየር መቃወሚያ ከአሜሪካ እንዲመሰጣት ቃል ገብተዋል።
በርካታ መንግሥታት የትናንቱን ጥቃት ያወገዙ ሲሆን ቻይናና ሕንድ ግን ሁለቱም ወገኖች ሁኔታዎችን ከማባባስ እንዲቆጠቡ መክረዋል።
የሩሲያ ሚሳኤሎች እየተወነጨፉ በመላው ዩክሬን ከተሞች ጥቃት ማድረስ የጀመሩት ትናንት ሰኞ ጠዋት የሥራ መግቢያ ሰዓት ላይ ነበር።
ፑቲን ይህ ጥቃት ሩሲያን ከክራይሚያ ጋር በሚያገናኘው የአውሮፓ ረዥሙ ድልድይ ላይ ለደረሰ ጥቃት አጸፋ ነው ቢሉም የዩክሬን መንግሥት ግን በድልድዩ ጥቃት በይፋ ኃላፊነት አልወሰደም።
የሩሲያ የደኅንነት ካውንስል ምክትል የሆኑት ዲሜትሪ ሜድቬድ ጥቃቱን ተከትሎ፣ ‘ይህ ጥቃት ገቢር አንድ ነው- ገቢር ሁለት ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።’












