በከፋ ረሃብ ምክንያት የማይበሉ ነገሮችን የሚመገቡ የዓለማችን ዜጎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ረሃብ፣ ድህነት፣ ጦርነት፣ በሽታ የምንመገባቸውን ምግቦች ከሚቀይሩ ምክንያቶች የተወሰኑት ናቸው።
ክፉ ቀን የማያደርገው ነገር የለም።
ረሃብ ጊዜ አይሰጥም እንደሚባለው፣ የሰው ሥጋም የተበላበት ጊዜ እንዳለ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።
ተስፋ አስቆራጭ በሚባል ሁኔታ ውስጥ ያሉ ሰዎች በሕይወት ለመቆየት ለመስማት የሚከብዱ ነገሮችን ይመገባሉ።
ነገን ለማየት አበባ፣ ቅጠል፣ አይጥ፣ የተጣሉ አጥንቶች፣ የአንስሳት ቆዳ እና ሌሎችንም ምግብ ብሎ ለመጥራት የሚቀፉ ነገሮችን ይመገባሉ።
ጠኔ፣ ቸነፈር እና ረሃብ በበርካታ የዓለማችን ክፍሎች ባሉ አገራት ዋነኛ ገፅታ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብ ፕሮግራም መረጃ ያሳያል።
በየምሽቱም እስከ 828 ሚሊዮን የሚደርሱ የዓለማችን ሕዝቦች በረሃብ ሌሊቱን ያሳልፋሉ። በተጨማሪም 345 ሚሊዮን ሕዝብ ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ችግርን እየተጋፈጠ ነው።
የዓለም የምግብ ቀን ጥቅምት 06/2015 ዓ.ም. ይከበራል።
ቢቢሲም ይህችን ዕለት ለማስታወስ ክፉኛ ረሃብ አጋጥሟቸው የተረፉ አራት ሰዎችን ከተለያዩ አገራት በማነጋገር እንዴት እንደተረፉ ጠይቋቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Rani
“የአይጥ ሥጋ ብቻ ነበር መግዛት የምችለው”
“ከልጅነቴ ጀምሮ የአይጥ ሥጋ እየበላሁ ነው ያደግኩት፤ ምንም አይነት የጤና ችግር አጋጥሞኝ አያውቅም። የሁለት ዓመት የልጅ ልጄን የአይጥ ሥጋ ነው የምመግባት። ለምደነዋል” ስትል የደቡብ ሕንድ ተወላጅ የሆነችው ራኒ ትናገራለች።
የ49 ዓመቷ ራኒ በቼናይ ግዛት አቅራቢያ የምትኖር ስትሆን፣ ይህም በአገሪቱ ካሉ በጣም የተገለሉ ማኅበረሰቦች የአንዱ መኖሪያ ነው።
ራኒ ትምህርቷን ከአምስተኛ ክፍል በኋላ አልቀጠለችም ።
በሕንድ የሕዝብ አመዳደብ ውስጥ በዝቅተኛ ደረጃ ከሚመደቡ ማኅበረሰቦች ውስጥም ናት ራኒ።
በዚህ አመዳደብ ምክንያት ማኅበረሰቡ ለዘመናት የማያቋርጥ ግፍና ሰቆቃ ደርሶበታል።
እንደ ባርያ ከሚቆጠሩት ኢሩላ ማኅበረሰብ ተወላጅ የሆነችው ራኒ በአሁኑ ወቅት ከዚህ ነጻ ለማድረግ በሚሠራ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት ውስጥ ትሠራለች።
“ሁልጊዜ የምንኖረው ከከተሞች እና መንደሮች ውጪ ነው። ወላጆቻችን እና አያቶቻችን በርካታ ጊዜ የሚበሉት እንዳልነበራቸው ይነግሩን ነበር። በእነዚህ ፈታኝ ወቅቶች ነው አይጦች ምግብ የሆኑን” ስትል ራኒ ለቢቢሲ ተናግራለች።
አክላም “ከልጅነቴ ጀምሮ አይጦችን እንዴት መያዝ እንደሚቻልም ተምሬያለሁ” ትላለች።
ራኒ በልጅነቷ የተማረችው ሕይወትን ለማስቀጠል ምንም ማድረግ የሚለው ችሎታ አሁንም የራሷን ቤተሰብ ለመመገብ ረድቷታል።
ከቤተሰቧ ጋር ቢያንስ በሳምንት ሁለት ጊዜ አይጦችን አብስለው ይመገባሉ።
የኢሩላ ማኅበረሰብ የሚመገቧቸው አይጦች በተለምዶ በቤት ውስጥ የሚገኙትን ሳይሆን በማሳ ውስጥ የሚገኙትን የአይጥ ዝርያዎችን ነው።
“የአይጧን ቆዳ ከገፈፍን በኋላ በእሳት ጠብሰን እንበላታለን። አንዳንድ ጊዜም ሥጋውን ቆራርጠን ከምስርና ከእርድ ጋር አብረን ሠርተን እንበላለን” ትላለች።
“ዶሮ ወይም ዓሣ መብላት የምችለው በወር አንድ ጊዜ ብቻ ነው። አይጦች በብዛት ይገኛሉ፣ ነጻም ናቸው" ስትል ታስረዳለች።

የፎቶው ባለመብት, Abdulkadir Mohamed/ NRC
“ጭቃ የተቀላቀለበት ውሃ ጠጥቻለሁ፤ በየመንገዱ የሞቱ እንስሳትን የሚበሉም ነበሩ”
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሶማሊያ በአስከፊ ረሃብ እንደተመታችና በአገሪቱ በ40 ዓመታት ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ድርቅ ምክንያትም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች መፈናቀላቸውን ገልጿል።
የአርባ ዓመቷና የሰባት ልጆች እናት የሆነችው ሻሪፎ ሐሰን ዓሊ በሶማሊያ ከተፈናቀሉት መካከል አንዷ ነች።
ሕይወቷን ለማትረፍ ቀዬዋን ጥላ 200 ኪሎ ሜትር በእግሯ ተጉዛለች።
ከታችኛው ሸበሌ ግዛት ተነስታ ከመዲናይቱ ሞቃዲሾ ወጣ ብሎ ወደሚገኝ ጊዜያዊ መጠለያ ደረሰች። እዚህም ለመድረስ አምስት ቀናት ፈጅቶባታል።
“በጉዟችን ወቅት የምንበላው በቀን አንድ ጊዜ ብቻ ነበር። ብዙ ምግብ በማይኖርበት ጊዜ ልጆቻችንን መግበን እኛ እንራባለን” ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Abdulkadir Mohamed / NRC
ወደ ሞቃዲሾ ባደረገችው ጉዞ ላይም አንዳንድ አስደንጋጭ ክስተቶች ገጥመዋታል።
“ወንዙ ሙሉ በሙሉ ደርቋል። ለዓመታትም ከወንዙ የሚፈሰው ትንሽ ውሃ ስለነበር ጭቃ የተቀላቀለበት ውሃ መጠጣት ነበረብን” ትላለች ሻሪፎ።
“በዚህ ጉዞ ላይ በመቶዎች የሚቆጠሩ የሞቱ እንስሳትን አይቻለሁ። በርካቶችም የእንስሳቱን ሬሳ እና ቆዳዎችን እየበሉ ነበር።”
ሻሪፎ 25 ላሞች እና 25 ፍየሎች የነበሯት ሲሆን፤ ሁሉም በድርቁ አልቀዋል።
“ዝናብ የለም እና በእርሻዬ ላይ ምንም የሚበቅል እህል የለም” ትላለች።
በአሁኑ ወቅት በልብስ አጠባ ኑሮዋን ለመግፋት እየሞከረች ነው።
በቀን ከሁለት ዶላር በታች የምታገኝ ሲሆን፣ ምግብ ለመግዛትም አይበቃም።
“በማገኘው ገንዘብ አንድ ኪሎ ሩዝ እና አትክልት መግዛት በጣም ይከብደኛል። ለሁላችንም በጭራሽ አይበቃም፤ ይህ ድርቅ በጣም ከብዶናል” ትላለች።
ከእርዳታ ድርጅቶች የተወሰነ ድጋፍ ብታገኝም በቂ እንዳልሆነ ታስረዳለች።
“ምንም የለንም” ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, Felix Lima/ BBBC NEWS BRASIL
“ቤተሰባችንን በሕይወት ለማቆየት የተጣሉ ቆዳዎች እና አጥንቶች እየተመገብን ነው”
በብራዚል ሳኦ ፖሎ ነዋሪነታቸውን ያደረጉት የ63 ዓመቷ ጡረተኛ ሊንዲናልቫ ማሪያ ዳ ሲልቫ ናሲሜንቶ ላለፉት ሁለት ዓመታት ከአካባቢው ሥጋ ቤቶች የሚጣል አጥንት እና ቆዳ እየተመገቡ ይገኛሉ።
ግለሰቧ ባለቤታቸውን፣ አንድ ወንድ ልጃቸውን እና ሁለት የልጅ ልጆቻቸውን ለመመገብ አራት ዶላር ዕለታዊ በጀት አላቸው።
በዚህም ገንዘብ ሥጋ መግዛት ስለማይችሉ ወደተለያዩ ሥጋ ቤቶች ሄደው የተራረፉ የዶሮ ሥጋዎችንና ቆዳ ይገዛሉ። ይሄ ራሱ በኪሎ 70 የአሜሪካን ሳንቲም ያስወጣቸዋል።
“በቆዳው ውስጥ የተረፈውን የሥጋ ቁርጥራጭና አጥንቶችን አንድ ላይ አበስላለሁ። ለጣዕምም ባቄላ እጨምርበታለሁ” ይላሉ።
የዶሮው ቆዳ ዘይት በሌለበት ብረት ምጣድ ላይ የሚጠበስ ሲሆን፣ ከዚያ የሚገኘው ቅባትና ስብን ያጠራቅሙታል።
ያንንም ቅባት ሌሎች ምግቦችን ለማብሰል ይጠቀሙበታል።

“ፍራፍሬ፣ አትክልት ወይም ጣፋጭ ምግቦችን ለመግዛት እንኳን አላስብም። ከዚህ በፊት ሥጋ እና አትክልት የተሞላ ፍሪጅ ነበረኝ። በተጨማሪም በጎመን፣ ቲማቲም፣ ሽንኩርት የተሞላ ነበር። ምግቡ የተትረፈረፈ ነበር” ይላሉ።
“ዛሬ ሁሉ ነበር ባዶ ነው። ያለኝ ነገር ቢኖር አንድ ሽንኩርት እና የፍራፍሬ ሳህኑ ብቻ ነው” በማለትም ይናገራሉ።
ሊንዲናልቫ ሥራቸውን ያጡት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎ ሲሆን ልጃቸውም ሥራ የለውም።
“የማውቃቸው ሰዎች ምግብ ይሰጡኛል። እንዲሁም በአካባቢው ካለ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን አንዳንድ እርዳታዎችን አገኛለሁ። በዚሁ መንገድ ነው ሕይወቴን ለማስቀጠል እየሞከርኩ ያለሁት” ይላሉ።
የብራዚል የምግብ ዋስትና መረብ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት መሠረት በአገሪቷ ከ33 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በረሃብ ውስጥ ይኖራሉ።
በሰኔ ወር ይፋ የተደረገው ይህ አዲስ ጥናትም ከግማሽ በላይ የሚሆነው ሕዝብ በምግብ እጦት እንደሚሰቃይ አረጋግጧል።
“እኔ እና ልጆቼ ቀይ ቁልቋል እየተመገብን ነው ሕይወታችንን ያተረፍነው”
“ዝናብም ሆነ ምርት የለም። ስለዚህም የምንሸጠው ነገርም ሆነ ገንዘብ የለንም። ሩዝ ገዝቶ የመብላት አቅም የለኝም።”
ይህንን የምትለው የ25 ዓመቷ የሁለት ልጆች እናት የማዳጋስካር ነዋሪዋ ፌፊኒያና ናት።
በባለፉት ሁለት ዓመታት ባጋጠመ የዝናብ እጥረት ምክንያት ሰብሎች ወድመዋል፣ እንዲሁም የቤት እንስሳት ረግፈዋል።
በዚህም የተነሳ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ የማዳጋስካር ሕዝብ በረሃብ አፋፍ ላይ እንደሆነ የተባበሩት መንግሥታት ገልጿል።
ፌፊኒያና በድርቅ ከተጠቁ አካባቢዎች አንዷ በሆነችው አምቦሳሪ ከተማ ትኖራለች።
እሷ እና ባለቤቷ ውሃ በመሸጥ ኑሮን ለመግፋት እየሞከሩ ነው።
“ገንዘብ ሳገኝ ሩዝ ወይም ካሳቫ እገዛለሁ። ምንም ከሌለኝ ቀይ ቁልቋል መብላት አለብኝ ወይም በረሃብ መተኛት ነው ያለች አማራጭ” ስትል ለቢቢሲ ተናግራለች።
“ባለፉት አራት ወራት ስንበላው ቆይተናል። ነገር ግን በአሁኑ ወቅት ሁለቱም ልጆቼ በተቅማጥ እየተሰቃዩ ነው” በማለትም ታስረዳለች።

የፎቶው ባለመብት, UNICEF
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ባለፈው ዓመት እንዳስታወቀው በደቡባዊ ማዳጋስካር ነዋሪዎች ረሃባቸውን ለማስታገስ ነጭ ሸክላ፣ የቁልቋል ቅጠል እና ሌሎች ስሮች እየተመገቡ ነው።
ፍሬው የፌፊኒያና ቤተሰብን በሕይወት ለማቆየት ሊረዳ ይችላል። ነገር ግን ሰውነታቸው የሚፈልገው ቫይታሚኖች የሉትም።
የአራት ዓመት ልጇ በምግብ እጥረት የተነሳ ሕክምና ከሚደረግላቸው በርካቶች አንዱ ነው።
ፌፊኒያና “እንዲያው የተወሰነ ትንሽ ዝናብ ቢዘንብ የተወሰነ ምርት እናገኛለን። ድንች፣ ስኳር ድንች፣ ካሳቫ እና ፍራፍሬ መብላት እንችል ነበር" ትላለች።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ዓለም ከምንጊዜውም በላይ በረሃብ እየተሰቃየች ነው ብሏል።
ይህ ቀውስ በአራት ምክንያቶች የተነሳ ሲሆን፤ እነሱም ግጭት፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምጣኔ ሀብታዊ መዘዝ እና የዋጋ ግሽበት ናቸው።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ወርሃዊ የሥራ ማስኬጃው በአውሮፓውያኑ 2019 ከነበረው 44 በመቶ ወይም በአማካይ 73.6 ሚሊዮን ዶላር በላይ ጭማሪ አሳይቷል።
“አሁን ለሥራ ማስኬጃ የሚወጣው ተጨማሪ ወጪ አራት ሚሊዮን ሰዎችን ለአንድ ወር ይመግብ ነበር” ብሏል ተቋሙ።
ሆኖም ተቋሙ እንደሚለው ገንዘብ ብቻውን ቀውሱን አያቆመውም።
ጦርነቶችን ለማስቆም ፖለቲካዊ ፍላጎት ካልታየ እና የዓለም ሙቀት መጨመርን ለመቆጣጠር ቁርጠኝነት ከሌለ “ዋነኞቹ የረሃብ መንስኤዎች በእሽክርክሪት መንገድ ይቀጥላሉ” ሲል ሪፖርቱ አጠቃሏል።












