ትግራይ ውስጥ በረሃብ ሳቢያ ሰዎችና እንስሳት እየሞቱ ነው ተባለ

በትግራይ ያለው ረሃብ

የፎቶው ባለመብት, YASUYOSHI CHIBA

በጦርነት በተጎዳችው ትግራይ ክልል ሰዎች እና እንስሳት በረሃብ እና በመሠረታዊ የህክምና እንክብካቤ እጥረት እየሞቱ መሆኑን የክልሉ ግብርና ኃላፊ ገለጹ።

"በመንደሮች እና በከተሞች ውስጥ የምግብ እና የመድኃኒት እጥረት አለ። እናም በክልሉ ውሰጥ እየተከሰተ ያለው ቀውስ እኛ ከምናውቀው የበለጠ ሊሆን ይችላል" ሲሉ ዶ/ር አትንኩት መዝገቦ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።

ህወሓትም ባወጣው መግለጫ ላይ የክልሉን አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኤጀንሲን ዋቢ አድርጎ በነሐሴ ወር 150 ሰዎች በረሃብ መሞታቸው ተመዝግቧል ብሏል።

ረሃቡ የተከሰተው ማይ ቅኔጣል፣ ቆላ ተምቤን፣ ሃውዜን፣ በማዕከላዊ ዞን ታንኳ ምላሽ እንዲሁም ሽረ ውስጥ ባለ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ ውስጥ እንደሆነም ተገልጿል።

በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል እየተጠናቀቀ ባለው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ በተቀሰቀው ጦርነት ሳቢያ ከባድ ሰብአዊ ቀውስ ተከስቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በትግራይ ክልል ያለው ሁኔታንም አስመልክቶ "በአስርት ዓመታት ውስጥ በዓለም ላይ አስከፊው የረሃብ ሁኔታ" እንዲቀለበስ ከተፈለገ 5.2 ሚሊዮን ሰዎች የአስቸኳይ እርዳታ ሊቀርብላቸው እንደሚገባ አስታውቋል።

ቀደም ሲልም 400 ሺህ የሚሆን ሕዝብ በረሃብ አፋፍ ላይ መሆናቸውን አስታውቋል።

ነገር ግን ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለፉት ሁለት ቀናት ውስጥ በክልሉ የደረሱትን 152 የጭነት መኪኖችን ጨምሮ 500 እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች ወደ ክልሉ መግባታቸውን ገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ የእርዳታ አቅርቦቱን ለማፋጠን የፍተሻ የደኅንነት ኬላዎች ቁጥርም መቀነሱ ተነግሯል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ከነሐሴ 16 ጀምሮ አንድም እርዳታ የጫነ መኪና ወደ ትግራይ አልደረሰም ሲል ቅሬታ ያቀረበ ሲሆን በየቀኑም በ100 መኪኖች የተጫነ የእርዳታ አቅርቦት ለክልሉ ያስፈልጋሉ ብሏል።

የግብርና ኃላፊው በተጨማሪ ምን አሉ?

የግብርና ኃላፊው ዶ/ር አትንኩት መዝገቦ እንደሚናገሩት በምግብ ዕርዳታ ዕጥረት ምክንያት ረሃብ በመላው ክልሉ እየተስፋፋ ነው።

"ከዚህ ቀደም ነዋሪዎች የነበረቻቸውን ይቋደሱ ነበር ነገር ግን በአሁኑ ወቅት የሚበሉት የላቸውም" ብለዋል።

ለዚህም ደግሞ ነዳጅ አቅርቦት አለመኖሩ እንዲሁም የባንክ አገልግሎትና መብራት መቋረጥ ችግሩን በዋነኝነት እንዳባባሰው ያስረዳሉ።

በዚህም የምግብ እጥረት ዋነኞቹ ተጠቂዎችና ከፍተኛ ድርሻውን የያዙት ሴቶችና ህፃናት መሆናቸውንም ይናገራሉ።

በትግራይ ክልል በተጣለው መገናኛ አገልግሎት እገዳ ምክንያት እየተፈጠረ ያለውን የቀውስ መጠን በዝርዝር መረዳት አዳጋች ቢሆንም "ግለሰቦች በረሃብ ምክንያት ሲሞቱ በአይናችን እያየን ነው" ብለዋል።

"በምግብ እና በመድኃኒት እጥረት ምክንያት ሰዎች እየሞቱ እና የህመም እባጭ ምልክቶችን እያሳዩ ነው" በማለትም ያስረዳሉ።

የግብርና ቢሮ ኃላፊው እንደሚናገሩት በክልሉ ውስጥ እየተከሰተ ያለውን ቀውስ ለመግታት የምግብ ዕርዳታ እንደሚጠብቁ አስረድተዋል።

ምንም እንኳን በአሁኑ ወቅት ያለው የዝናብ ጥሩ ቢሆንም አርሶ ለማምረት ከሦስት እስከ አራት ወራት ይወስዳል እንዲሁም በአንዳንድ አካባቢዎች የአንበጣ ወረራ መገኘቱንም እንደ ስጋት አንስተዋል።

በተለይም የአንበጣ ወረራውን ለመግታት በሚደረገው ትግል የመገናኛ ዘዴዎች መዘጋታቸው አሳሳቢ አድርጎታል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ እንስሳቱ ክትባት ባለማግኘታቸው በተለያዩ በሽታዎች እየሞቱ እንደሆነም አስረድተዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የእርዳታ ቁሳቁስ የጫኑ 100 የጭነት መኪናዎች ወደ ትግራይ ክልል መዲና መቀለ መግባታቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትናንትናው ዕለት አስታውቋል።

3500 ቶን ይመዝናሉ የተባሉት የጭነት መኪናዎች ምግብና ምግብ ነክ ያልሆኑ ሕይወት አድን ቁሶችን ጭነው ነው ወደ ክልሉ የገቡት።

ባለፈው ሳምንት የተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ መንግሥት ለትግራይ የእርዳታ አቅርቦቶችን በጠበቀ መንገድ ዘግቷል ሲል ከሷል። በዚህም ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ለአደጋ እየተጋለጡ መሆኑን አስጠንቅቋል።

የፌደራሉ መንግሥት በበኩሉ ወደ ክልሉ የሰብዓዊ እርዳታ እንዳይገባ እክል የሆኑት የህወሓት አማጺያን ናቸው ይላል።