የኢትዮጵያ የፖለቲካ፣ የጤና እና የቴክኖሎጂ ድምጾች ለምን ወደ ክለብሀውስ ተሻገሩ?

የፎቶው ባለመብት, SOPA Images
"ሁላችንም ስለ አገራችን ተጨንቀናል" ይላል ኔዘርላንድስ የሚኖረው የፖለቲካ እና የደኅንነት ተንታኝ አደም ካሴ አበበ (ዶ/ር)።
በጦርነት፣ በዋጋ ንረት፣ በማኅበራዊ ቀውስ ውስጥ የምትዋዥቀው ኢትዮጵያ ወዴት ታመራለች? ለችግሮቿ መፍትሔ የሚገኘውስ እንዴት ነው? የሚሉና ሌሎችም ብዙ አሳሳቢ ጥያቄዎች አሉ።
በቡና ዙሪያ፣ ታክሲ ውስጥ፣ ምሳ ሲበላ፣ ቢሮ ውስጥ፣ ጸጉር ቤት. . . ባጠቃላይ ሰው በተሰበሰበበት ሁላ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ መነሳቱ አይቀርም።
ማኅበራዊ ሚዲያውም ሌላ የውይይት መድረክ ነው። ፌስቡክ ላይ ስለ ኢትዮጵያ ይወራል። በትዊተር ስለ ኢትዮጵያ ይወራል።
ዶ/ር አደም ስለ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውይይት ሲኖር ይሳተፋል። ይጽፋል። በማኅበራዊ ገጾቹም አስተያየቱን ይሰጣል።
በቅርቡ ደግሞ ክለብሀውስ ላይ ብቅ ብሏል።
"ሁሉም ሰው ስለ ኢትዮጵያ ጭንቀት ውስጥ ነው ያለው" የሚለው ዶ/ር አደም፤ ሁለት የክለብሀውስ ውይይቶች ላይ ተወያይ ነበር።
ሁለቱም ውይይቶች በትግራይ ክልል የተነሳው ጦርነት ላይ ያተኮሩ ናቸው። ከትግራይ፣ ከአማራ ክልል እንዲሁም ከሌሎች አካባቢዎች የተውጣጡ ተሳታፊዎች ሐሳብ ተለዋውጠዋል።
"ክለብሀውስ አንድና ሁለት ሰው ከሚያደርገው ንግግር የሰፋ መድረክ ይሰጣል። ሁሉም በአገሪቱ ባለው ሁኔታ ስለተጨነቀ ተለቅ ባለ ቡድን ውስጥ ሆኖ መነጋገር የተሻለ ስሜት ይሰጣል" ሲል ውይይቶቹን ይገልጻቸዋል።
ክለብሀውስ በይፋ ከተጀመረ ዓመት ሆኖታል። መስራቾቹ ፖል ዴቪሰን እና ሮሀን ሴት ይባላሉ።
መተግበሪያውን በተንቀሳቃሽ ስልካቸው የጫኑ ተጠቃሚዎች በማንኛውም ርዕሰ ጉዳይ ላይ የውይይት ቡድን መፍጠር ይችላሉ። ቡድኑን እንዲቀላቀሉ ለሚፈልጓቸው ሰዎች የግብዣ ጥሪ ይልካሉ።
መተግበሪያው የተለቀቀ ሰሞን መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። ያለ ሳንሱር ውይይት የሚደረግበት መድረክ መሆኑ ብዙዎችን ወደ ክለብሀውስ ስቧቸዋል።
በእርግጥ ሰዎች በአንጻራዊ ነጻነት መነጋገራቸው ምቾት የነሳቸው እንደ ቻይና ያሉ አገራት መተግበሪያውን ከነጭራሹ አግደውታል።
"ክለብሀውስ የተሳሳተ ግምትን ለማጥራት እድል ይሰጣል"
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ስለ አገራዊ ጉዳዮች ኢትዮጵያ ውስጥና ከኢትዮጵያ ውጪም የሚዘጋጁ የክለብሀውስ ውይይቶች እየተበራከቱ መጥተዋል።
የጤና፣ የቴክኖሎጂ፣ የሥነ ፆታ፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የፖለቲካ፣ የሙዚቃ ወዘተ. . . ጉዳዮች በክለብሀውስ መወያያ ሆነዋል።
ዶ/ር አደም ክለብሀውስን የተቀላቀለው በጓደኞቹ ገፋፊነት ነው።
ከሌሎች ማኅበራዊ ሚዲያዎች በተለየ ለውይይት፣ ጥያቄ ለማንሳት እና ሐሳብን በጥልቀት ለማብራራት እንደሚመች ይናገራል።
የተሳተፈባቸው ውይይቶች ስሱ የሆኑ ወቅታዊ የፖለቲካ ጉዳይ ላይ ያጠነጠኑ እንደመሆናቸው ተሳታፊዎች ጠንካራ ስሜት እንዳንጸባረቁ ያስታውሳል።
"በትዊተር ወይም በሌላ መንገድ መናገር እና መጻፍ ይቻላል። ክለብሀውስን የተለየ የሚያደርገው የውይይት ወይም የንግግር መድረክ መሆኑ ነው። ሐሳቦች ይነሳሉ። ጥያቄ ይቀርባል። ማብራራት የሚቻልበትም ነው።"
ሐሳብ በጽሑፍ ወይም በሌላ መንገድ ቀርቦ አንባቢዎች ወይም አድማጮች ጥያቄ ሲኖራቸው ከሐሳቡ ባለቤት ማብራሪያ ካላገኙ፤ አንዳንድ ነጥቦችን የሐሳቡ ባለቤት ለማለት ከፈለገው ወይም ከፈለገችው በተቃራኒው ሊረዱት ይችላል።
የሐሳቡ ባለቤት እንዲህ ለማለት ፈልጋ ወይም ፈልጎ ነው የሚል የተሳሳተ ግንዛቤ ተፈጥሮ ሳይግባቡ ከመለያየት፤ ለጥያቄ እና መልስ እድል የሚሰጡ መድረኮች የተሻሉ እንደሆኑ ዶ/ር አደም ያምናል።
"ክለብሀውስ የተሳሳተ ግምትን ለማጥራት እድል ይሰጣል። ላለመግባባት ብዙም ክፍተት አይሰጥም።"

የፎቶው ባለመብት, SOPA Images
ማኅበራዊ ሚዲያ አወንታዊ ገጽታ እንዳለው ሁሉ አፍራሽ ሚናም ይጫወታል። ሰዎች ይዘላለፋሉ፣ ጽንፈኛ አስተያየቶች ይሰነዝራሉ፣ ሐሰተኛ መረጃ ይሰራጫል።
ነገር ግን ሰዎች በአቋማቸው የሚገለሉበት አልያም በሰጡት ሐሳብ ምክንያት ማንነታቸው ላይ ያነጣጠረ ዘለፋ የሚደርስባቸው አጋጣሚዎችም አሉ።
እነሱ ከሚያምኑበት እና መስማት ከሚፈልጉት የተለየ አስተያየት ላላቸው ሰዎች እምብዛም ቦታ የሌላቸውም ብዙ ናቸው።
የክለብሀውስ ድረ ገጽ መተግበሪያውን የሚገልጸው 'people are at the center of every moment' ብሎ ነው። ሰዎች የማንኛውም ክስተት ማዕከል ናቸው እንደ ማለት ነው።
ዶ/ር አደም "ክለብሀውስ እንደ ቢላ ነው። ቢላ ጥሩ ነገር ሊሠራበት ወይም ሰው ሊገደልበትም ይችላል" በማለት የመተግበሪያው አገልግሎት የሚወሰነው በተጠቃሚዎች ባህሪ እንደሆነ ያስረዳል።
ማንኛውም ማኅበራዊ ሚዲያ ጥሩም መጥፎም የሚሆነው ከሰዎች አጠቃቀም አንጻር እንደሆነም ያክላል።
ሁሉን አቀፍ እንዲሁም ሐሳብ መር ፖለቲካዊ ውይይት የሚደረግባቸው መድረኮች ውስን ከመሆናቸው አንጻር ክለብሀውስ በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋለ ክፍተቱን ሊሞላ እንደሚችል ያምናል።
ዋናው ነገር ጤና- የጤና ወግ
ዶ/ር ፍጹም ጥላሁን በአሜሪካ የኩላሊት ሕክምና ስፔሻሊስት ነው። የጤና ወግ የተባለ ገጽ ከሙያ አጋሩ ጋር መስርቷል።
ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት የተጀመረው የጤና ወግ፤ በጤና ነክ ጉዳዮች ለማኅበረሰቡ ትክክለኛ መረጃ ለማቅረብ ነው በዋነኛነት የተጀመረው። የጤና ባለሙያዎች እንዲመካከሩ እና እንዲማማሩም ያግዛል።
የጤና ወግ በፌስቡክ 36 ሺህ፣ በትዊተር 4 ሺህ፣ በቴሌግራም 2 ሺህ አባሎች አሉት። ድረ ገጹን በየቀኑ ከ150 እስከ 200 ሰዎች ይጎበኙታል። እስካሁን 40 ክፍሎች የደረሰ ፖድካስትም ተላልፏል።
አሁን ደግሞ በሁለት ሳምንት አንዴ ክለብሀውስ ላይ የጤና ወግ ውይይት እየተደረገ ነው።
ዶ/ር ፍጹም እንደሚለው፤ በተለያዩ የጤና ዘርፎች የተካኑ ባለሙያዎችን በመጋበዝ ማብራሪያ እንዲሰጡ ይደረጋል።
"ክለብሀውስ አሳታፊ ነው። ለምሳሌ ፖድካስት ሲሠራ እኔና ዶ/ር ኤርምያስ [የጤና ወግ ባልደረባ] ብቻ ነን የምናወራው። ክለብሀውስ ላይ ግን አድማጩም ተናጋሪ ይሆናል። ስለዚህ ለሰዓታት ብናወራም አይሰለችም።"
ከዚህ በፊት በተካሄዱ የጤና ወግ የክለብሀውስ ውይይቶች ስለ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን የኮሮናቫይረስ ክትባት፣ ሐሰተኛ መረጃን ስለ መግታት እና ስለ አዕምሮ ጤና ተነስቷል።
ከጤና ሚንስትር እና ከሲዲሲ (ሴንተር ፎር ዲዚዝ ኮንትሮል) የተጋበዙ ባለሙያዎች ክትባትን የተመለከቱ የተዛቡ አሉባልታዎችን እንዲያጠሩ መድረክ እንደተሰጣቸው ዶ/ር ፍጹም ይናገራል።
ብዙዎች ካልታመሙ በስተቀር ስለ ጤና ጉዳይ መስማት ሊሰለቻቸው እንደሚችል ከግምት በማስገባት የጤና ወግ "ጃዝ አወር" ከተባለ ክለብሀውስ ጋር ጥምረት ፈጥሯል። እናም ውይይቶቹ ደረቅ አይደሉም። በለስላሳ የጃዝ ሙዚቃ ይታጀባሉ።
"ክለብሀውስን የተለየ የሚያደርገው ባለሙያዎች መጋበዛችን እና አድማጮች ባለሙያዎችን በቀጥታ መጠየቅ መቻላቸው ነው። ክለብሀውስ፤ ቡና ሲጠጣ ሄዶ የመቀላቀል ስሜት ይፈጥራል" ይላል ዶ/ር ፍጹም።
ክለብሀውስ ከአፕል እና ከአንድሮይድ ተጠቃሚዎች ውጪ ላሉ ተደራሽ አለመሆኑ መተግበሪያውን እንደሚገድበው ያምናል።
በሌላ በኩል ሰዎች ትክክለኛ ማንነታቸውን አሳውቀው ወደ ክለብሀውስ ስለሚገቡ የአሠራሩ ግልጽነት ደስ ይለዋል።
ክለብሀውስ የጤና ውይይት ከጃዝ ጋር የሚዋሀድበት ማለትም ለፈጠራ ዋጋ የሚሰጥ እንደሆነም ይናገራል።
ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ጤናን የተመለከቱ የተዛቡ መረጃዎች ይለቀቃሉ። የጤና ወግ ይህንን ማስተካከል ነው አላማው።
"መረጃውን እኛው ባለሙያዎቹ ብናዘጋጀው ማኅበረሰቡ ትክክለኛ መረጃ ይገኛል። ኃላፊነቱንም እኛ እንወስዳለን። አንድ ጉዳይ ላይ ብዥታ ሲፈጠር 'የጤና ወግን እንጠይቅ፤ እነሱን ነው የምናምነው' የሚሉ ሰዎች መኖራቸው ለእኛ ትልቅ ስኬት ነው።"
የቴክኖሎጂ ነገር- ሀበሻ ኢን ቴክ
ቴክኖሎጂን የተመለከቱ ውይይቶች ብዙ አይደሉም። ባሉትም የሚሳተፉት ጥቂቶች ናቸው።
ካናዳ በሚገኝ ባንክ ውስጥ በክላውድ ኢንተግሬሽን ክፍል ከፍተኛ ኃላፊ የሆነው ተፈሪ በቀለ ካሳ፤ ሀበሻ ኢን ቴክ የተባለ የክለብሀውስ ገጽ የከፈተውም የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች እንዲገናኙ ነው።
ባለሙያዎቹ የገጠሟቸውን ፈተናዎች እና ስኬታቸውን ያካፍላሉ። ከአድማጮች መካከል ባለሙያዎቹ በተማሪነት (ሜንተርሺፕ) የሚወስዷቸውም አሉ።
ተፈሪ ክለብሀውስ ላይ የሚደረጉትን ውይይቶች ቀድቶ ወደ ፖድካስት ይወስዳቸዋል።
"ማይ ቴክ ጆርኒ ወይም የእኔ የቴክኖሎጂ ጉዞ በሚል ሰዎች እየተጋበዙ ያወራሉ። በቴክኖሎጂው ስኬታማ ሰዎች ልምዳቸውን የሚያካፍሉበት ነው።"
በሳይበር ሰኪውሪቲ፣ በክላውድ ኮምፒውቲንግ እና በሌሎችም የቴክኖሎጂ ዘርፍች ውይይት ይደረጋል።
እስካሁን ከጋበዛቸው ባለሙያዎች መካከል የሊንክድኢን ዳይሬክተር ኦፍ ኢንጂነሪንግ በፍ አየነው፣ ሊሊ አምደማርያም፣ የቴክቶክ አዘጋጅ ሰለሞን ካሳ፣ አዲስ ዓለማየሁ፣ ማርቆስ ለማ፣ የቅኔ ጌምስ ፈጣሪ ዳዊት አብርሀም ይጠቀሳሉ።
የቴክኖሎጂ ሙያተኞች ስለ ሥራቸው በፌስቡክ ወይም በሌላ ማኅበራዊ ሚዲያ ከመጻፍ ስለሚቆጠቡ እንደ ክለብሀውስ ያሉ ገጾች ተመራጭ እየሆኑ እንደመጡ ይገልጻል።
ክለብሀውስ በሙያው ውስጥ ካሉ እና ቴክኖሎጂ ከሚወዱ ሰዎች ጋር መነጋገር የሚችሉበት ነው።
ክለብሀውስ ተወዳጅ መሆኑ ሌሎች መተግበሪያዎች ላይ ያሉ የድምጽ ውይይት መድረኮችን እንዳስተዋወቀ ተፈሪ ይናገራል። የስፖቲፋዩ ግሪንሩም እና የትዊተሩ ስፔስ ይገኙበታል።
ከፌስቡክ እና ከዩቲዩብ በተለየ ክለብሀውስ አሳታፊ ነው። ሐሳብ ከአንድ ወገን ብቻ የሚመነጭበት ሳይሆን የንግግር መድረክነቱ ያመዝናል።
"እውቀት ተኮር በሆኑ ጉዳዮች ከላይክ እና ከኮሜንት ባለፈ እርስ በእርስ ለማውራት ስለሚመች ተመራጭ እየሆነ መጥቷል" ሲል ያስረዳል።
በሀበሻ ኢን ቴክ በየሳምንቱ ከ50 እስከ 100 ሰዎች ይሳተፋሉ።
"እኔ የማረጋግጠው እኔ መኖሬን፣ ሚስቴ መኖሯን እና እንግዶቼ መኖራቸውን ነው። ሌላው ሰው በራሱ ፕሮግራም ወይም ፍላጎት ነው የሚመጣው።"
ቀጣይነት ያለው እና ባስፈለገ ጊዜ የሚገኝ የቴክኖሎጂ መድረክ መፍጠሩን የሚገልጸው ተፈሪ፤ ሀበሻ ኢን ቴክ በቀዳሚነት የጠቀመኝ እኔን ነው ይላል።
"እንግዶቼ ስለ ብርታታቸው ሲያወሩ፣ የወደቁበትን ሲያወሩም ብዙ ተምሬያለሁ። ከእንግዶቼ ጥሩ ምላሽ አግኝቻለሁ። አበረታተውኛል። አድማጮችም እንደሚያነሳሳቸው ይነግሩኛል።"
የክለብሀውስ መስራቾች ገጹን የሚያስተዋውቁት 'በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ስለ አስደናቂ ነገሮች እያወሩ ነው። እየሮጡ ወይም እየተራመዱም ቢሆን ያዳምጡ። እርስዎም ሐሳብዎን ያካፍሉ' በማለት ነው።
ንግድ እንዴት ያድጋል? ናይጄርያ እና ፖሊሶቿ፣ ሂፕ ሀፕ ሙዚቃ የሚሉና በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ገጾች በየቀኑ ያገኛሉ።
ተፈሪ በበኩሉ ክለብሀውስን የሚገልጸው "እዚህ ቦታ ድምጽ አለኝ የሚል ስሜት ይፈጥራል" ብሎ ነው።















