የተሻለ ነጻነትን ይሰጣል የተባለው መተግበሪያ ቻይናን አስቆጣ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ክለብሀውስ አዲስ መተግበሪያ ነው። መተግበሪያው የድምጽ መልዕክት መለዋወጫ ሲሆን፤ መጠቀም የሚችሉት ጥሪ የተደረገላቸው የተመረጡ ሰዎች ብቻ ናቸው።
ቻይና በዚህ መተግበሪያ ደስተኛ አይደለችም። ምክንያቱም ሕዝቡ እንዲያገኝ የማትፈልጋቸውን መረጃዎች ተጠቃሚዎች በነጻነት እየተለዋወጡ ይገኛሉ።
በሳንሱር የታፈነው የቻይና ኢንተርኔት በክለብሀውስ በኩል አንጻራዊ ነጻነት አግኝቷል። በአገሪቱ በግልጽ ከማይወሩ ርዕሰ ጉዳዮች መካከል የዊገር ማኅበረሰብ ላይ የሚደርሰው እንግልት፣ የሆንክ ኮንግ ተቃውሞ እንዲሁም የታይዋን ጥያቄ በክለብሀውስ መነጋገሪያ ሆነዋል።
አንዲት ክለብሀውስን መጠቀም የጀመረች ቻይናዊት "ኢንተርኔት ለመጀመሪያ ጊዜ ያገኘው መሰለኝ" ስትል ነው የገለጸችው።
የክለብሀውስ የቻይና ተጠቃሚዎች
ማንደሪን የሚናገሩ የቻይና እና ታይዋን ነዋሪዎች በመተግበሪያው ተገናኝተው ስለ አገራቸው እና ዴሞክራሲ ተወያይተዋል።
በታይዋን እና በተለያዩ የቻይና ግዛቶች የተወለዱ ሰዎች ታይዋን የቻይና ግዛት መሆን አለባት? የሚል ውይይት ሲያደርጉ ነበር። ይህ ደግሞ የተለመደ አጋጣሚ አይደለም።
ቻይና እንደ ዊቡ እና ዊቻት ያሉ ማኅበራዊ ሚዲያዎች አሏት። ሆኖም ግን ሳንሱር ስለሚደረጉ ዜጎች የሚለዋወጡት መረጃ ውስን ነው።
ክለብሀውስ ላይ ሳንሱር የለም። ተጠቃሚዎች የሚለዋወጡት የድምጽ መልዕክት ስለማይቀረጽም ነጻነት ይሰጣል።
5,000 ተጠቃሚዎች ያስተናገደ የድምጽ ውይይት የተሳተፈች አንድ የታይዋን ሴት "እነዚህ አመለካከቶች በመስማቴ ደስተኛ ነኝ። በሁለቱም ወገን ፕሮፓጋንዳ አለ። እርስ በእርስ በመወያየት ለመግባባት መሞከር አለብን" ብላለች።
የ28 ዓመቷ ታሶ ለቢቢሲ እንደተናገረችው፤ በሁሉም ወገን ያሉ ድምጾች የሚሰሙበት መድረክ መፈጠሩ የተለያዩ ትርክቶች እንዲሰሙ መንገድ ይፈጥራል።
ሌላዋ ቻይናዊት ጂጂ እንደምትው ደግሞ ለንግግር መድረክ መገኘቱ በሁሉም ወገን ያሉ ሰዎች ስለ ችግሮቻቸው እንዲያወሩና እንዲያገግሙም ይረዳል።
የዢንዣንግ ጉዳይ
ዢንዣንግ ግዛት ውስጥ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የዊገር ማኅበረሰብ አባላትና ሙስሊሞች በግዳጅ ማቆያ ታግተው እንደሚገኙ ይነገራል።
ቻይና እነዚህ ማቆያዎች "ከአሸባሪነትና አክራሪነት የሚያላቅቁ ትምህርት ቤቶች ናቸው" ትላለች።
ክለብሀውስ ላይ መነጋገሪያ ከነበሩት አጀንዳዎች አንዱ በዢንዣንግ ግዛት የግዳጅ ማቆያዎች አሉ? የሚለው ነው።
የሀን እና ተወላጅ ማኅበረሰቦች መካከል የተካሄደው ይህ ውይይት 12 ሰዓታት የወሰደ ነበር።
የግዳጅ ማቆያዎቹ መኖራቸውን እርግጠኛ ያልሆኑ የሀን ተወላጆች ከ ማኅበረሰብ በሰሙት የሰቆቃ ታሪክ ተገርመዋል።
አንድ ውይይቱን እየሰማ የነበረ የሀን ማኅበረሰብ ተወላጅ ያዳመጣቸው አሳዛኝ ታሪኮች በጣም አሳዝነውት እንደነበር ተናግሯል። እንባውን መቆጣጠር ስላልቻለ መኪናውን አቁሞ እንዳለቀሰም ያስታውሳል።
የቻይና የግዳጅ ማቆያዎችን በተመለከተ የተለየ እይታ ያላቸው የሀን ማኅበረሰብ ተወላጆች በውይይቱ ነበሩ። አንዲት ሴት "አሜሪካ እና አውሮፓም ሽብርን ለመግታት ጥብቅ እርምጃ ይወስዳሉ" ስትል ተከራክራለች።
ክለብሀውስ እና የቻይና ትችት
ክለብሀውስን ለመቀላቀል የመተግበሪያው ተጠቃሚ ግብዣ ሊልክልዎ ይገባል። በአይፎን እና አይፓድ ላይ ብቻ ነው የሚሠራው።
መተግበሪያውን የሚጠቀሙ አብዛኞቹ ቻይናውያን ከተማ ቀመስና የተማሩ ናቸው።
አንድ የዊቡ ተጠቃሚ ቻይናዊ እንደሚለው "ክለብሀውስ ቻይናን የሚነቅፉ ሰዎች ሐሳብ መለዋወጫ ነው።"
ክለብሀውስ አሁን ላይ ቻይና ውስጥ እገዳ ቢጣልበትም፤ ውይይት ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ማሳየቱን አሌክስ የተባለች ተጠቃሚ ትገልጻለች።
"ጭላንጭል ብርሀን አሳይቶናል" በማለትም አስተያየቷን ሰጥታለች።












