በምግብ እጥረት ተጎድታ ለሕክምና ወደ ጣሊያን የተወሰደችው ፍልስጤማዊት ሕይወቷ አለፈ

የፎቶው ባለመብት, EPA
በረሃብ ክፉኛ ተጎድታ እና ከስታ የነበረችው ፍልስጤማዊት ለሕክምና ወደ ጣሊያን ከተወሰደች በኋላ በሆስፒታል ውስጥ ሕይወቷ አለፈ።
የ20 ዓመቷ ማራህ አቡ ዙህሪ ከእናቷ ጋር ረቡዕ ዕለት ወደ ጣልያኗ ፒሳ ከተማ የበረረችው የኢጣሊያ መንግሥት ባመቻቸላት የሕክምና እድል ነበር።
የፒሳ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል አርብ ዕለት የልብ ድካም አጋጥሟት ወደ ሆስፒታሉ ከመጣች በኋላ መሞቷን አስታውቋል።
ሆስፒታሉ በከፍተኛ ሁኔታ ክብደቷ እና ጡንቻዎቿ ቀንሰው እንደነበር የገለፀ ሲሆን የጣሊያን የዜና ኤጀንሲዎች ደግሞ በከፍተኛ የምግብ እጦት የተጎዳች እንደነበረች ዘግበዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በጋዛ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ የተስፋፋ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት እንዳለ አስጠንቅቋል።
ባለፈው ወር የድርጅቱ ባለሙያዎች ባወጡት ሪፖርት በጋዛ የረሃብ አደጋ እየተከሰተ ነው ሲሉ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
እስራኤል በበኩሏ በጋዛ ረሃብ የለም ስትል የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲዎች እርዳታ ከድንበር አካባቢ አጓጉዘው እያከፋፈሉ አይደለም በማለት ትወነጅላቸዋለች።
እስራኤል በጋዛ ጦርነት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ ከ180 በላይ ሕጻናትና ጎልማሶች ወደ ጣሊያን ለሕክምና ተልከዋል።
በዚህ ሳምንት 31 ታካሚዎች እና አስታማሚዎቻቸው ሮም፣ ሚላን እና ፒሳ መድረሳቸውን የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የብሪታንያ የፓርላማ አባላት መንግሥታቸው የታመሙ እና የተጎዱ የጋዛ ነዋሪዎችን ወደ ዩኬ "በፍጥነት" እንዲያመጣ ጠይቀዋል።
የሕዝብ እንደራሴዎቹ ይህንን የጠየቁት የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር የሕክምና ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የጋዛ ነዋሪዎችን ለመርዳት የሚያስችል ዕቅድ እንደሚያዘጋጁ ከተናገሩ በኋላ ነው።
የአገር ውስጥ ቢሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሕፃናትን ከጋዛ "በፍጥነት" ለማስወጣት እንዳሰበ እንዲሁም ሕፃናቱ እና ተንከባካቢዎቻቸው ወደ ዩኬ እንዲገቡ ከመፈቀዱ በፊት የባዮሜትሪክ ምርመራዎች መደረግ እንዳለበት አሳስቧል።
የእስራኤል ሚኒስቴር በበኩሉ የጋዛ ከተማ ነዋሪዎችን "ደህንነቱ ወደተጠበቀ ቀጠና" ከመዘዋወራቸው በፊት ከእሁድ ጀምሮ ድንኳን እና ሌሎች ቁሳቁሶችን መስጠት እንደሚጀምር አስታውቋል።
ይህ የተሰማው የእስራኤል መንግሥት ወታደሮቹ ጋዛ ከተማን እንደሚቆጣጠሩ ከገለጸ ከቀናት በኋላ ነው።
ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በከተማዋ ትልቅ አካባቢ፣ ዘይቶን ለበርካታ ቀናት የቆየ ከባድ የቦምብ ድብደባ ተፈጽሟል።
የከተማዋ ማዘጋጃ ቤት ቃል አቀባይ በዘይቶን ያለው ሁኔታ "አሰቃቂ" ነው ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል። የእስራኤል ጦር ለተከታታይ ስድስት ቀናት የአየር ድብደባ እና የማፍረስ ዘመቻ ካካሄደ በኋላ አካባቢውን በጅምላ ለቅቀው እንዲወጡ መደረጉንም ገልጸዋል።
በጋዛ ሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር ቅዳሜ ዕለት እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት በትንሹ 36 ሰዎች ተገድለዋል ብሏል።
ተጨማሪ 11 ሰዎች በምግብ እጥረት መሞታቸውን የጤና ሚኒስቴሩ ገልጾ፣ ይህም በረሃብ ምክንያት የሞቱት ሰዎች ቁጥርን ከ250 በላይ አድርሶታል ብሏል።
የእስራኤል ጦር "በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስወገድ ቁርጠኛ ነኝ" በማለት በሐማስ የሚተዳደሩ ሚኒስቴሮች የሚሰጡት የሟቾች ቁጥር ተዓማኒነት እንደሚጎድላቸው ገልጿል።
የእስራኤል መንግሥት በጋዛ የተመጣጠነ ምግብ እጥረት አለ መባሉን ያስተባብላል።
የእስራኤል ጦር አሸባሪዎች እንጂ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት እንደማይፈጽም በመግለጽም ለሰብዓዊ ቀውሱ ተጠያቂው ሐማስ ነው ይላል።
በጋዛ የእስራኤል ጦር ሰፊ ማጥቃት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ ከ60,000 በላይ ሰዎች መሞታቸውን በሐማስ የሚመራው የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።















