ግብፅ የኬንያው ፕሬዝዳንት በሕዳሴ ግድብ ምርቃት ላይ በመገኘታቸው ቅር መሰኘቷን ገለጸች

የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ

የፎቶው ባለመብት, Office of the Prime Minister-Ethiopia

የምስሉ መግለጫ, በሕዳሴ ግድብ ምረቃ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት ፕሬዝዳንት ሩቶ፤ "ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ አገራዊ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን ፓን አፍሪካዊ መግለጫ ነው" ብለው ነበር

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት ላይ በመገኘታቸው ግብፅ ቅር እንደተሰኘች በኬንያ የግብፅ አምባሳደር የሆኑት ሃተም ዮስሪ ሆስኒ ለአገሪቱ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ገለጹ።

አምባሳደሩን ተቀብለው ያነጋገሩት የኬንያ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሰስ ዋታንጉላ በበኩላቸው፤ግብፅ ከናይል ውሃ ጋር የተያያዘ ያላትን "ማንኛውንም ስጋት" በተመለከተ "ኢትዮጵያ ላይ ብቻ" ከማተኮር ይልቅ ከሁሉንም የተፋሰሱ አገራት ጋር እንድትመካከር ጠይቀዋል።

የኬንያ መገናኛ ብዙኃን ዘገባ እንደሚያመለከተው የኬንያ ፓርላማ አፈጉባኤ ዋታንጉላ እና የግብጹ አምባሳደር ሆስኒ ረቡዕ መስከረም 14/2017 ዓ.ም. በተገናኙበት ወቅት በዝርዝር ከተነሱ ጉዳዮች አንዱ በካይሮ እና በአዲስ አበባ መካከል ያለመግባባት ምንጭ የሆነው የናይል ውሃ ጉዳይ ነው።

የግብፁ አምባሳደር ኢትዮጵያ ከሁለት ሳምንት በፊት ባስመረቀችው ግዙፉ የሕዳሴ ግድብ ላይ ያላትን ቅሬታ አስረድተዋል። አምባሳደር ሆስኒ፤ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ "ከዓለም አቀፍ ሕግ የተቃረነ እና የተቋቋሙ የሕግ ማዕቀፍን የማያከብር" እንደሆነ መናገራቸውን የኬንያው 'ዘ ስታር' ጋዜጣ ዘግቧል።

አምባሳደሩ አክለውም፤ የአገራቸው ያላትን መብት የሚያስጠብቅ እና የናይል ውሃ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ አሳሪ ስምምነት እንዲፈረም ከአስር ዓመት በላይ ለሚሆን ጊዜ ስትጥር እንደነበር ገልጸዋል ተብሏል።

የግብፁ ልዑክ፤ "ለምሳሌ በፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያ የሥልጣን ዘመን ከረዥም ድርድር በኋላ በዋሽንግተን ስምምነት ለመፈራረም ዝግጁ ነበርን። በመጨረሻ ጊዜ ግን ኢትዮጵያ ልትገኝ አልቻለችም። በቀላሉ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ ጊዜ እየገዙ ነበር" ሲሉም አትዮጵያን ከስሰዋል።

ግብፅ ሁሉም የናይል ተፋሰስ አገራት የአሌክትሪክ ኃይል በማመንጨት በውሃው ለመጠቀም ያላቸውን መብት እንደምታከብር መናገራቸውም ተዘግቧል። ይሁን እንጂ ኬንያ በህዳሴ ግድብ ምርቃት ላይ በመሳተፏ ግብፅ ቅር መሰኘቷን አምባሳደር ሆስኒ ገልጸዋል።

የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ጷግሜ 4/2017 ዓ.ም. በተካሄደው የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ምርቃት ሥነ ስርዓት ላይ "ዋና እንግዳ" ሆነው ተገኝተው ነበር። ከኬንያው ፕሬዝዳንት በተጨማሪ የሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ደቡብ ሱዳን፣ ባርቤዶስ መሪዎች እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ማህሙድ አሊ የሱፍ ተገኝተዋል።

ፕሬዝዳንት ሩቶ በስነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር "ታላቁ የኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብ አገራዊ ፕሮጀክት ብቻ ሳይሆን ፓን አፍሪካዊ መግለጫ ነው" ሲሉ አሞካሽተውት ነበር። አገራቸው ከግድቡ ከሚመነጨው ኤሌክትሪክ ኃይል "የተወሰነ" ለማግኘት "የኃይል ሽያጭ ስምምነት ለመፈረም ዝግጁ" መሆኗንም አስታውቀው ነበር።

"የትኛውም አገር ይህንን ዓይነቱን ሀብት የመጠቀምን እድል መከልከል የለበትም" ያሉት ሩቶ፤ የናይል ውሃ አጠቃቀም "በፍትሐዊነት፣ ዘላቂነት፣ ትብብር እና የእርስ በእርስ መከባበር ላይ መርሆዎች ላይ" የተመሰረተ ሊሆን እንደሚገም ተናግረዋል።

በትናንናው ዕለት የኬንያ ፓርላማ አፈ ጉባኤን አግኝተው ያነጋገሩት የግብፁ አምባሳደር ሆስኒ፤ የኬንያው ፕሬዝዳንት በሕዳሴው ግድብ ምረቃ ስነ ስርዓት ላይ በመገኘታቸው አገራቸው እንዳልተደሰተች አስረድተዋል።

"ኬንያ በዝግጅቱ ላይ በመገኘቷ ተከፍተን ነበር። የትኛውም የተፋሰሱ ሀገር አልተገኘም ነበር፤ ኬንያ ብቻ። ጅቡቲ እና ሶማሊያ የናይል ተፋሰስ አካል አይደሉም" በማለት መናገራቸውን ጋዜጣው ዘግቧል።

የኬንያ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሰስ ዋታንጉላ (ግራ) እና በኬንያ የግብፅ አምባሳደር ሃተም ዮስሪ ሆስኒ

የፎቶው ባለመብት, Speaker Moses Masika Wetang'ula

የምስሉ መግለጫ, የኬንያ ፓርላማ አፈ ጉባኤ ሞሰስ ዋታንጉላ (ግራ) እና በኬንያ የግብፅ አምባሳደር ሃተም ዮስሪ ሆስኒ
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"[ኬንያ] ከኢትዮጵያው ግድብ መጠቀሟ እኛን አይጎዳንም። ከኢትዮጵያ ጋር ያለን ጉዳይ የኤሌክትሪክ ኃይል ከማመንጨታቸው ጋር የተያያዘ አይደለም፤ ከናይል ውሃ ጋር እንጂ። በግብፅ፣ በሱዳን እና በኢትዮጵያ መካከል የሁለትዮሽ ወይም የሦስትዮሽ ስምምነት ላይ መድረስ አለብን፤ ይህም ስምምነት በዓለም አቀፍ ሕግ መሠረት አስገዳጅ [መሆን አለበት]" በማለትም የአገራቸውን አቋም አስረድተዋል።

የኬንያ ፓርላማ አፈ ጉባኤው ሞሰስ ዋታንጉላ ይህንን ንግግር በተመለከተ በፌስቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ፤ "የግብፅ መንግሥት በናይል ወንዝ እና በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ አካታች ውይይትን እንዲቀበል" ማሳሰባቸውን ገልጸዋል።

ፕሬዝዳንት ሩቶ፤ ግብፅ "ግብፅ ኢትዮጵያን ብቻ ከመጥቀስ ይልቅ ከሁሉም የናይል ተፋሰስ አገራት ጋር እንድትመካከር" በሚል ያቀረቡትን ሀሳብ እንደሚቀበሉትም አፈ ጉባኤው በጽሑፋቸው ጠቅሰዋል። "[የፕሬዝዳንት ሩቶን] ሃሳብ በመከተል፣ ውሃ የጋራ ሀብት በመሆኑ አገራትን ከመከፋፈል ይልቅ አንድ ማድረግ እንዳለበት በመግለጽ ጥሪውን በድጋሚ አቅርቤያለሁ" ብለዋል።

ይህንን የሚያጠናክር ዘገባ ያወጣው ዘ ስታር፤ አፈጉባኤው፤ "ከእናንተ ግብጽም ሆነ ከጎረቤታችን ኢትዮጵያ ጋር ችግር የለብንም። እንዲያውም የኤሌክትሪክ ኃይል ከእነሱ ስለምናስገባ ከሕዳሴ ግድብ ተጠቃሚ ነን።

ፕሬዝዳንቱ በቅርቡ እንደተናገሩት ግብፅ በናይል ጉዳይ ላይ ስጋት ካላት በኢትዮጵያ ላይ ብቻ አታተኩሩ። ሁሉንም ወደ ውይይት ጠረጴዛው ጥሩና ችግሮቹን በጋራ ለመፍታት በጋራ እንረዳዳለን" ማለታቸውን አስነብቧል።

በተጨማሪም አፈ ጉባኤው፤ "ከኢትዮጵያ ጋር [የሚነሳ] ግጭት የአፍሪካ ቀንድን የበለጠ አለመረጋጋት ውስጥ ይከትተዋል" በማለትም በፌስቡክ ጽሑፋቸው ስጋታቸውን አንስተዋል።

"ኬንያ በቪክቶሪያ ሐይቅ በኩል ለናይል ውሃ አስተዋጽኦ የምታበረክት እንደመሆኗ መጠን አፍሪካ የራሷን ተግዳሮቶች በመተባበር እና አገር በቀል መፍትሄዎችን በማፈላለግ የመፍታት አቅም እንዳላት ታምናለች" ብለዋል።

አፈ ጉባኤ ሞሰስ ዋታንጉላ፤ ኬንያ ከአዲስ አበባ እና ካይሮ ጋር ያላትን ግንኙነት በመጥቀስ አገራቸው "ስምምነትን ለመገንባት የአሸማጋይነት ሚና ለመጫወት ዝግጁ መሆኗን" እንደተናገሩ ተዘግቧል።

በኒውዮርክ የተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እየተሳተፉ ያሉት ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ወደ ሀገር ሲመለሱ ይህንን በተመለከተ እንደሚያነጋግሯቸው እንዲሁም "ወደ ጋራ [አንድነት] መምጣት እንድንችል ከግብፅ አመራሮች እንዲሁም ከሌሎች የናይል ተፋሰስ አገሮች ጋር እንዲነጋገር እመክረዋለሁ" እንዳሉም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ እና ግብፅ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ለዓመታት ሲያደርጉት የቆዩት ድርድር በሙሉ በሙሉ ስምምነት ላይ ሳይደረስበት ግድቡ ወደ ስራ ገብቷል። አሁንም ቢሆን ግን ኢትዮጵያ ለንግግር እና ለድርድር በሯ ክፍት መሆኑን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ከቢቢሲ አፍሪካ ጋር በነበራቸው ቆይታ መናገራቸው አይዘነጋም።