ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታ ምክር ቤት አቤቱታ አቀረበች

የፎቶው ባለመብት, PMO/FB
ኢትዮጵያ ባለፉት 14 ዓመታት ስትገነባው የነበረውን ግድብ ባስመረቀችበት ዕለት የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የኢትዮጵያን የተናጠል እርምጃን በመቃወም ለመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት የአቤቱታ ደብዳቤ አስገቡ።
ባለፉት ዓመታት የግድቡን ውሃ አሞላል እና ቀጣይ ሥራን በተመለከተ በኢትዮጵያ፣ በግብፅ እና በሱዳን መካከል ተደጋጋሚ ንግግሮች ቢካሄዱም ከሚያስማማ ነጥብ ላይ ሳይደረስ የግድቡ ግንባታ ተጠናቅቆ በይፋ ተመርቋል።
የተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎች እና ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት የተካሄደውን የግድቡን ምረቃ ተከትሎ የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ባድር አብደላቲ ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት ፕሬዝዳንት የአገራቸውን ተቃውሞ የሚገልጽ ደብዳቤ ልከዋል።
ግብፅ ታላቁ የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ ባለፉት ዓመታት ለተባበሩት መንግሥታት ተደጋጋሚ ደብዳቤ የጻፈች ሲሆን፣ የግድቡ ምርቃት በተካሄደበት ጳጉሜ 4/2017 ዓ.ም. በላከችው ደብዳቤ ላይ በግድቡ ላይ ያላትን ተቃውሞ አስፍራለች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለየፀጥታው ምክር ቤት በላኩት ደብዳቤ ላይ ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ግንባታዋ "የዓለም አቀፍ ሕግጋትን እና የምሥራቅ አባይ ተፋሰስን የሚመሩትን ደንቦችን የሚጥስ የአንድ ወገን ፕሮጀክት ነው" ብለዋል።
በአፍሪካ ግዙፉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለማጠናቀቅ 14 ዓመታት የወሰደ ሲሆን፣ በእነዚህ ዓመታት ውስጥ ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ለበርካታ ጊዜያት ለድርድር ተቀምጣ እንደነበር ይታወሳል።
ወደ አምስት ቢሊዮን ዶላር የወጣበት ግድብ የውሃ አቅርቦታችንን ይቀንሰዋል የሚል ስጋት ያደረባቸው ሱዳን እና ግብፅ የውሃ ሙሌቱ እና አስተዳደሩን በተመለከተ ኢትዮጵያ አስገዳጅ ስምምነት እንድትፈርም ቢወተውቱም ተቀባይነት ሳያገኙ ቀርተዋል።
ይህንንም ተከትሎ ኢትዮጵያ ግድቡን በተመለከተ የምትወስዳቸውን ሁሉንም የተናጠል እርምጃዎችን እንደማትቀበል እና "በሁለቱ የታችኛው የተፋሰሱ አገራት ሕዝቦችን የኅልውና ጥቅሞች ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል" ያለችውን ግድብ እንደማትቀበል ግብፅ አመልክታለች።
ነገር ግን በታላቁ የሕዳሴ ግድብ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ ግድቡን የገነባቸው የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ለመጉዳት ሳይሆን አለመሆኑን እና በጋራ በመጠቀም ዓላማ "አብረን ተካፍለን ከመብላት" ነው በማለት አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጨምረውም ለወደፊት ለሚሠሩ ትላልቅ ሥራዎች፣ አገራቱ በትብብር እና በጋራ እንዲቆሙ ለግብፅ እና ለሱዳን ጥሪ አቅርበዋል።
ግብፅ በግድቡ የምረቃ ዕለት ለተባበሩት መንግሥታት በጻፈችው ደብዳቤ ከኢትዮጵያ ጋር የሚደረግ ትብብር የታችኛው ተፋሰስ አገራትን ስጋት ከግምት ባስገባ ሁኔታ በዓለም አቀፍ ሕጎች ላይ መሠረት ያደረገ መሆን አለበት ብላለች።
"በተቃራኒው ግን ኢትዮጵያ ግትር አቋም በመያዝ ድርድሮቹ እንዲጓተቱ በማድረግ ግድቡን በማጠናቀቅ አማራጭ የሌለው ሁኔታ እንዲፈጠር አድርጋለች" ያለው የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ደብዳቤ ኢትዮጵያ ግድቡን "ለልማት ፍላጎት ሳይሆን ለፖለቲካ አጀንዳ" እየተጠቀመችበት ነው ሲል ከስሷል።
በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአባይ ውሃ አስተዳደር ላይ በተናጠል የበላይነት ለመያዝ የምታደርገውን ጥረት ግብፅ እንዳላየ እንደማታልፈው አስጠንቅቋል።
"በዓለም አቀፍ ሕግ እና በተባበሩት መንግሥታት ቻርተር እንደተመለከተው የሕዝቧን የኅልውና ጥቅም ለማስጠበቅ ግብፅ ሁሉንም ዓይነት እርምጃ ለመውሰድ ያላትን መብት ትጠቀማለች" ማለቷን መግሥታዊው አል አህራም ጠቅሷል።
ግብፅ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይን በተመለከተ የአሁኑን ጨምሮ ባለፉት ዓመታት ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ምክር ቤት፣ ለአፍሪካ ኅብረት እና ለአረብ ሊግ በማቅረብ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር ሞክራለች። በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ ኢትዮጵያ ግንባታውን አጠናቃ አሁን ለምረቃ አብቅታዋለች።
በዓለማችን በርዝመቱ የሚታወቀው የአባይ ወንዝ ከ85 በመቶ በላይ ውሃውን የሚያገኘው ከኢትዮጵያ ነው።
የወንዙን አብዛኛውን ውሃ የምትጠቀመው ግብፅ ስትሆን በኢትዮጵያ የተገነባው ግድብ በበላይነት ስትጠቀምበት የነበረውን የውሃ መጠን ያሳጣኛል የሚል ስጋት ፈጥሮባታል።
ግብፅ በአውሮፓውያኑ 1959 የተፈረመው እና የአብዛኛውን የውሃውን ድርሻ የሚሰጣትን የቅኝ ግዛት ስምምነት በመጥቀስ የወንዙን ውሃ ሙሉ በሙሉ በበላይነት ለብቻዋ የመጠቀም ፍላጎት እንዳላት የምትለው ኢትዮጵያ ይህ ሁኔታ መለወጥ እንዳላበት ስትከራከር ቆይታለች።
ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ ያላት ድርሻዋን ባረጋገጠ መልኩ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም ላይ ስምምነት እንዲደረስ እና ግንባታው የግብፅን የውሃ ደኅንነት ላይ አደጋ እንደማይጥል በተደጋጋሚ ገልጻለች።















