በሥራ ላይ ያልነበሩ ሦስት የኔዘርላንድ ኮማንዶዎች አሜሪካ ውስጥ በጥይት ተመቱ

የኔዘርላንድ ኮማንዶ

የፎቶው ባለመብት, DUTCH DEFENCE MINISTRY

በአሜሪካ ለስልጠና የሄዱት ሦስት የኔዘርላንድ ኮማንዶዎች ከስራ ውጪ እያሉ ኢንዲያናፖሊስ ከተማ ከሚገኝ ሆቴል ውጭ በጥይት ተመተው ቆሰሉ።

ክስተቱ ቅዳሜ ሌሊት በከተማው የመዝናኛ ስፍራ መከሰቱ ተገልጿል።

የኢንዲያናፖሊስ ፖሊስ ሦስቱን ኮማንዶዎች በተኩስ ቆስለው መገኘታቸውን እና በአቅራቢያው ወደሚገኙ ሆስፒታሎች መወሰዳቸውን ተናግሯል።

የኔዘርላንድ መከላከያ ሚኒስቴር አንደኛው ተጎጂ በአደገኛ ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እና የተቀሩት ሁለቱ ራሳቸውን እንደሚያውቁ አስታውቋል። 

ሦስቱም የኮማንዶ አባላት ሲሆኑ፣ በኔዘርላንድስ የጦር ኃይሎች ውስጥ ካሉ ልዩ ኦፕሬሽን ክፍሎች የአንዱ አባላት ናቸው።

ጥቃቱ የተፈጸመው ከሥራ ሰዓታቸው ውጭ ካረፉበት ሆቴል ፊት ለፊት በነበሩበት ወቅት ነው ሲል ሚኒስቴሩ አክሎ ገልጿል።

በአካባቢው ፖሊስ በተጎጂዎቹ እና በሌላ ግለሰብ ወይም ቡድን መካከል ቀደም ብሎ ግጭት እንደነበረ ይተታመናል ብሏል።

የኢንዲያናፖሊስ ሜትሮፖሊታን ፖሊስ ዲፓርትመንት አባል ለፎክስ59 “አሁን ልንገልጽ የምንፈልገው መረጃ ጥቃቱ በሆቴሉ ውስጥ የተከሰተ ነገር አለመሆኑን ነው” ብለዋል።

"የምናምነው በሌላ ቦታ ከዚህ በፊት የተደረገ ግጭት እንደነበር ነው።”

የደች መከላከያ ሚኒስቴር የተጎጂዎች ቤተሰቦች መረጃ እንደደረሳቸው እና የአካባቢው ፖሊስ ምርመራ እያከናወነ መሆኑን ገልጿል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ እስካሁን በቁጥጥር ስር የዋለ ሰው የለም።