ኧርሊንግ ሃላንድ የፕሪሚየር ሊጉን የግብ ክብረ ወሰን ሰበረ

ኤርሊንግ ሃላንድ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የማንቸስተር ሲቲው አጥቂ ኧርሊንግ ሃላንድ በአንድ ውድድር ዘመን 35ኛ የፕሪሚየር ሊግ ግቡን በማስቆጠር ክብረ ወሰን ሰበረ።

ይህም ከዚህ ቀደም በአለን ሺረር እና አንድሪው ኮል ተይዞ ነበረውን የ34 ግብ ክብረ ወሰን ለመስበር አስችሎታል።

“ይህ ድንቅ ምሽት እና ድንቅ አጋጣሚ ነው። ደስተኛ ነኝ፤ ኩራትም ተሰምቶናል” ሲል ሃልነድ ለስካይ ስፖርትስ ተናግሯል።

በተጨማሪም “በጣም አስደናቂ ከመሆን ባለፈ ደስተኛም ነኝ። ሦስት ነጥብ በማሳካታችንም ደስ ብሎኛል። ወሳኙ ነገር ነጥቡ ነው” ሲል ለቢቢሲ ማች ኦፍ ዘ ዴይ ተናግሯል።

የኖርዌይ ዜጋ የሆነው ተጫዋቹ 35ኛ ጎሉን ያስቆጠረው ቡድኑ ዌስት ሃምን 3 ለምንም በማሸነፍ ወደ ደረጃ ሰንጠረዡ መሪነት በተመለሰበት ጨዋታ ነው።

የጨዋታውን መጠናቀቅ የሚያበስረው ፊሽካ ከተሰማ በኋላ አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላን ጨምሮ የቡድኑ አባላት በሙሉ ተሰልፈው ለሃላንድ አድናቆታቸውን ገልጸውለታል።

“ከዚህ ቀደም ታይቶ አይታወቅም። ጎሉን ማስቆጠር ጥሩ ስሜት ይፈጥራል” ብሏል።

የቡድኑ አባላት “አክብሮታቸውን ለመግለጽ ተሰልፈው ጀርባዬን ሲመቱኝ ህመም ነበረው።”

የቡድን አጋሮቹ ብክብር ደስታቸውን ሲገልጹ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አሁን በሃላንድ የተሻሳለውን ይህንን ክብረ ወሰን ኮል በአውሮፓውያኑ 1993/94 የውድድር ዓመት ለኒውካስል 34 ጎሎችን አስቆጠረ። በቀጣዩ ዓመት ብላክበርን ሻምፒዮን እንዲሆን ያገዘው ሺረር ክብሩን ተጋራ።

ሁለቱም ተጫዋቾች ጎሎቹን ሲያስቆጥሩ የሊጉ ቡድኖች ብዛት 22 ነበረ ሲሆን፣ ይህም ከሃላንድ በላይ አራት ጨዋታ እንዲጫወቱ አግዟቸዋል።

ሺረር 42ቱንም ጨዋታዎች በቋሚነት ሲሰለፍ ኮል ሁለት ጨዋታዎች ብቻ አምልጠውታል።

ሃላንድ በመጀመሪያው የሊጉ የውድድር ዓመት ሪከርዱን ለመስበር 31ኛው ሳምንት ድረስ ብቻ ነው የቆየው።

ማንችስተር ሲቲ በሊጉ ቀሪ አምስት ጨዋታዎች አሉት።

“አስደናቂ ነው። 22 ዓመቱ ሲሆን ገና አምስት ጨዋታ ይቀረዋል። ሃትሪክ ከሠራ በኋላ 60ኛው ደቂቃ ላይ ስንቴ ቀይሬዋለሁ? ባልቀይረው ተጨማሪ ጎሎችን ያስቆጥር ነበር። ግን ሊጎዳም ይችል ነበር። እንኳን ደስ አለው” ያሉት አሰልጣን ፔፕ ጓርዲዮላ ናቸው።

“የሺረር እና ኮልን ክብረ ወሰን እንዲሰብር ሳይሆን ጎሎችን እንዲያስቆጥር ነው የምንፈልገው. . . የሊጉን ዋንጫ ማንሳት እንደሚፈልግ እርግጠኛ ነኝ” ብለዋል አሰልጣኙ ጨምረው።

“ክብረ ወሰኑን እንዲሰበር አልፈልግም ነበር። ለመሰበር 28 ዓመት ብቻ ነው የወሰደው። እሱ ድንቅ ተጫዋች ነው” ያለው ደግሞ አለን ሺረር ነው።