በስርቆት ምክንያት የአሜሪካ የተራድኦ ድርጅት በትግራይ የሚያቀርበውን የምግብ እርዳታ አቋረጠ

እርዳታ የሚቀበሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአሜሪካ መንግሥት የተራድኦ ድርጅት የሆነው ዩኤስኤአይዲ በትግራይ ውስጥ ተከስቷል ከተባለው የእርዳታ ምግብ ስርቆት ጋር በተያያዘ በክልሉ ውስጥ የሚያካሂደውን የእርዳታ ሥራ ለጊዜው ማቋረጡን አስታወቀ።

የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ተራድኦ ድርጅት ዩኤስኤአይዲ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው “በትግራይ ውስጥ ረሃብ በሚመስል ሁኔታ እየተሰቃዩ ላሉ ሰዎች የታለመው የምግብ እርዳታ” ከታለመለት አላማ ውጪ ገበያ ላይ ለሽያጭ መቅረቡን በመረዳቱ መሆኑን ገልጿል።

በዚህም ሳቢያ “አስቸጋሪ ያለውን ውሳኔ” ለማሳለፍ መገደዱን በማመልከት፣ ተጨማሪ መግለጫ እስኪሰጥ ድረስ፣ በትግራይ ክልል ውስጥ የሚካሄዱ በድርጅቱ የሚደገፉ የምግብ እርዳታ አቅርቦቶች እንዲቋረጥ መደረጉን አሳውቋል።

በተመሳሳይ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ለተረጂዎች በሚቀርብ የምግብ እርዳታ ላይ ተፈጸመ የተባለውን ስርቆት ለማጣራት ውስጣዊ ምርመራ ለማካሄድበ ትግራይ ክልል ውስጥ የሚያቀርበውን የምግብ እርዳታ ማቋረጡ ከቀናት በፊት ተዘግቧል።

አሶሺየትድ ፕሬስ የዜና ወኪል የእርዳታ ሠራተኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው የዓለም ምግብ ፕሮግራም የእርዳታ ምግብ ተገቢ ላልሆነ አላማ እየዋለ መሆኑን የሚያመለክቱ መረጃዎች መውጣታቸውን ተከትሎ ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ትግራይ የሚያደርገውን የእርዳታ አቅርቦት በጊዜያዊነት አቋርጧል።

ዩኤስኤአይዲ እና የዓለም ምግብ ፕሮግራም በትግራይ ውስጥ የእርዳታ ምግብ ላይ ስርቆት ይፈጸማል በማለት ወደ ክልሉ የሚያቀርቡትን እርዳታ ማቋረጣቸውን ተከትሎ የትግራይ ጊዜያዊ መስተዳደር በድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ ምርመራ መጀመሩን ተገልጿል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳደር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ጉዳዩን አስመልክተው በትዊተር ገጻቸው ላይ እንዳሰፈሩት የእርዳታ ምግብ አቅርቦት ለሌላ አላማ መዋሉን በተመለከተ ከዲፕሎማቶች፣ ከእርዳታ ድርጅት ተወካዮች እና ከክልሉ ነዋሪዎች ጋር ሲነጋገሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል።

ከችግሩ ከፍተኛነት እና ባሉ በርካታ ማስረጃዎች መሠረትነት የድርጊቱን ፈጻሚዎችን ማንነት ሳይለይ ተጠያቂ ለማድረግ በከፍተኛ የክልሉ ኃላፊዎች የሚመራ ምርመራ መጀመሩን አስታውቀዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኢትዮጵያ ውስጥ የሰብአዊ እርዳታ ከሚያቀርቡ ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ውሳኔ የተሰማውም የዓለም ምግብ ፕሮግራም ውሳኔን ተከትሎ ነው።

በእርዳታ ምግብ አቅርቦት ላይ ተፈጽሟል የተባለውን ስርቆት ከታወቀ በኋላ ዩኤስኤአይዲ ከፍተኛ ባለሙያዎቹን በማሰማራት በእርዳታ ፕሮግራሙ ላይ ጠንካራ ምርመራ ማድረግ መጀመሩን እና ይህንንም ተከትሎ የምግብ እርዳታውን ለጊዜው ማቆም የተሻለ አማራጭ መሆኑን ገልጿል።

ተከሰተ የተባለውን ችግር በተመለከተም ከኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት እና ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ባለሥልጣናት ጋር በመነጋገር አጥፊዎችን ለመለየት እና ተጠያቂ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆናቸውን አመልክቷል።

ከተባበሩት መንግሥታት እና ከሌሎች አጋሮቹ የሚገኘውን የምግብ እርዳታ ለተረጂዎች የማቅረብ ኃላፊነት ያለበት የዓለም ምግብ ፕሮግራም፣ ከሳምንታት በፊት በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል በሚያካሂደው የሕይወት አድን የእርዳታ ሥራ ላይ የተፈጸመ የምግብ አቅርቦት ስርቆትን እየመረመረ እንደሚገኝ ተገልጾ ነበር።

ከሳምንታት በፊት አሶሺየትድ ፕሬስ (ኤፒ) የእርዳታ ሠራተኞችን ጠቅሶ እንደዘገበው በእርስ በእርስ ጦርነቱ ከፍተኛ ጉዳት በደረሰባት ሽራሮ ከተማ ውስጥ ከነበረ መጋዘን ውስጥ ለ100 ሺህ ሰዎች ሊበቃ የሚችል የእርዳታ ምግብ መጥፋቱን ተናግረዋል።

ይህንንም ተከትሎ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ዳይሬክተር በአገሪቱ ላሉ አጋር ድርጅቶች በጻፉት ደብዳቤ “በአንዳንድ ገበያዎች የታየው መጠነ ሰፊ የሆነ የእርዳታ ምግብ ሽያጭ የዓለም ምግብ ፕሮግራም ስጋት እንዲገባው አድርጓል” ብለዋል።

ዳይሬክተሩ ለእርዳታ የተባሉ ምግቦች ለገበያ መቅረባቸው በተቋሙ ስም ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ከማሳደሩም በላይ ሰብዓዊ እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው እርዳታ የማሰባሰብ አቅም ላይ ችግር ሊፈጥር ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ለሁለት ዓመት ሲካሄድ ቆይቶ ባለፈው ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በቆመው ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች የምግብ እርዳታ በመዝረፍ እና ለተዋጊዎቻቸው በማቅረብ ሲከሰሱ እንደነበር ይታወሳል።