ወደ ትግራይ የየብስ ትራንስፖርት መጀመር እና የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች ጉብኝት

የፎቶው ባለመብት, Dimtsi Weyane
የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት መቀስቀስን ተከትሎ ተቋርጦ የቆየው ወደ ትግራይ የሚደረግ የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት በይፋ መጀመሩ ሲገለጽ፣ የክልል ርዕሳነ መስተዳደሮች እና የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተሞች ከንቲባዎች ለጉብኝት መቀለ ገቡ።
የትራንስፖርት ሚኒስቴር፣ የትግራይ፣ የአፋር እና የአማራ ክልሎች የትራንስፖርት ቢሮ ባለሥልጣናት ዛሬ ሚያዚያ 19/ 2015 ዓ.ም. በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ በአማራ እና በአፋር ክልሎች በኩል ወደ ትግራይ የሚደረገው የየብስ ትራንስፖርት መጀመሩን ማስታወቃቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ከሚያዝያ 14 ጀምሮ በሙከራ ደረጃ መጀመሩን ከሁለት ቀናት በፊት በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ አስታውቆ ነበር።
ሚኒስቴሩ በአፋር ክልል ወደ መቀለ የየብስ ትራንስፖርት መጀመሩን እና በአማራ ክልል በወልዲያ በኩልም ስምሪት በመስጠት አገልግሎት ማስጀመር መቻሉን ገልጾ፣ አገልግሎቱን በመደበኛነት ለማስጀመር የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች በመጠናቀቅ ላይ መሆናቸውን ገልጾ ነበር።
ከቀናት በፊት ለሰላም ስምምነቱ አስተዋፅኦ ላበረከቱ እውቅና በሰጡበት መርሃ ግብር፣ የአፋር ክልል መንግሥት ወደ ትግራይ የሚወስደውን መንገድ ለአገልግሎት ክፍት ማድረጉን በመግለጽ፣ የአማራ ክልል መንግሥትም ተመሳሳይ እርምጃ እንዲወስድ የትግራይ ጊዜያዊ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ጌታቸው ረዳ መጠየቃቸው አይዘነጋም።
ለሁለት ዓመታት የተካሄደው ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ ወደ ትግራይም ሆነ ከትግራይ ወደ ሌሎች አካባቢዎች የሚደረግ የትራንስፖርት አገልግሎት ተቋርጦ መቆየቱ ይታወሳል።
በፌደራል መንግሥቱ እና በህወሓት መካከል በፕሪቶሪያ ግጭት የማቆም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ ወደ ትግራይ የአየር ትራንስፖርት ቢጀመርም፣ የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎት በይፋ የተጀመረው ከወራት በኋላ ነው።
ይህም የተሰማው በገዢው ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ አደም ፋራህ የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮችን እና የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎችን ይዘው ትግራይ መግባታቸውን ተከትሎ ነው።
የትራንስፖርት ሚኒስቴር እና የክልል ቢሮዎች ዛሬ በሰጡት መግለጫ ወደ ትግራይ የየብስ ትራንስፖርት አገልግሎቱን ለማስጀመር የፈረሱ ድልድዮችን እና መንገዶችን የማደስ ሥራ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል።
ከአዲስ አበባ - ደሴ - ወልዲያ እና አላማጣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ - ሚሌ - ሰመራ - አብዓላ አድርጎ ወደ ትግራይ በሚሄደው መንገድ ላይ የዳሰሳ ጥናት መካሄዱን ገልጸው፣ የሙከራ ጉዞም ተካሂዶበታል ብለዋል።
የፀጥታውን ሁኔታውን ለማስጠበቅም በፍተሻ ኬላዎች ላይ በፌደራል ፖሊስ አማካኝነት ቁጥጥር እንደሚደረግ ተገልጿል።
የየብስ ትራንስፖርቱ መጀመር ተለያይተው የነበሩ ሰዎችን ለማገናኘት፣ ሕክምና ያጡ ሰዎች ሕክምና እንዲያገኙ እና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ እንዲጠናከር አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሏል።
ከጦርነቱ መቆም ከወራት በኋላ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳዳር የተመሠረተ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት ክልሉ ከፌደራል መንግሥቱ እንዲሁም ከሌሎች ክልሎች ጋር ያለው መስተጋብር እያንሰራራ ነው።
በተለያዩ ጊዜያት የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና ሚኒስትሮች ወደ ትግራይ ያቀኑ ሲሆን፣ የትግራይ ክልል ከፍተኛ አመራሮችም ወደ አዲስ አበባ እና ሌሎች ክልሎች ጉዞ አድርገዋል።
ዛሬም የክልል ርዕሳነ መስተዳድሮች እና የከተማ አስተዳደር ከንቲባዎች መቀለ የገቡ ሲሆን፣ ልዑካኑ አሉላ አባ ነጋ አየር ማረፊያ ሲደርሱ በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ እና ሌሎች ከፍተኛ ኃላፊዎችን አቀባበል ተደርጎላቸዋል።
ርዕሳነ መስተዳድሮቹ በትግራይ ክልል ውቅሮ ከተማ በጦርነቱ ወቅት ጉዳት የደረሰባቸውን ፋብሪካዎች መጎብኘታቸው የተገለጸ ሲሆን ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ውይይት ያደርጋሉም ተብሏል።
የልዑኩን ጉዞ በተመለከተ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ረዳኢ ሐለፎም፣ በየጊዜው መሻሻል እያሳየ ያለውን የሰላም ሁኔታ ለማጽናት እና በትግራይ ላይ የደረሰውን ችግር እንዲመለከቱ እና እንዲያውቁ ለማድረግ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
በሰላም ስምምነቱ ሒደት ያልተቋጩ ጉዳዮች መኖራቸውን የገለጹት ኃለፊው፣ ጉብኝቱ በቀጣይ ለሚኖረው የሰላም እንቅስቃሴ አጋዥ ሚና ይኖረዋልም ብለዋል።
የትግራይ እና የአማራ ክልል በሚወዛገቡበት እና ጦርነቱን ተከትሎ በአማራ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ስለሚገኙት አካባቢዎች ዛሬ ከልዑኩ ጋር መቀሌ ከገቡት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጋር ተነጋግረው እንደሁ የተጠየቁት ኃላፊው፣ “አፈጻጸም ላይ የምንነጋገርበት ካልሆነ በስተቀር የእነዚህ አካባቢዎች ጉዳይ በፕሪቶሪያው ስምምነት ላይ የተቀመጠ ነው።በሕገ መንግሥቱ መሠረት ይፈታ የሚል።
ይሁን እንጂ አንዱ ክልል ብቻውንም የሚፈታው አይደለም። ችግሮቹን እያነሱ በየጊዜው ያለውን ሁኔታ እያቃለሉ መሄድ ካልሆነ በስተቀር በዚሁ መቀሌ ላይ ቁጭ ብሎ ችግሩን ፈትቶ ለመሄድ አይደለም።ለመግባባት ያክል የተደረገ የመጀመሪያ ግንኙነት ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።












