ቦልሶናሮ ተሸንፈው ኢናሲዮ ሉላ የብራዚል ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ተመረጫ ፕሬዝደናት ሉላ ከድል በኋላ ባለቤታቸውን ሮዛንገላን አቀፈዋል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ተመረጩ ፕሬዝደናት ሉላ ከድል በኋላ ባለቤታቸውን ሮዛንገላን አቀፈዋል

በብራዚል በተከናወነው ፕሬዝዳናታዊ ምርጫ ግራ ዘመሙ የቀድሞ ፕሬዝዳት ሊውዝ ኢናሲዮ ሉላ ዳ ሲልቫ የቀኝ አክራሪውን እና የወቅቱ ፕሬዝዳናት ጄር ቦልሶናሮን አሸንፈዋል።

እጅግ መከፋፈል ከታየበት የሁለቱ ተቀናቃኞች የምርጫ ዘማቻ በኃላ ሉላ 50.9 በመቶ ድምጽ በማግኘት አሸናፊ ሆነዋል።

ይህ ውጤት እንደሚያሸንፉ እምነት ለነበራቸው የቦልሶናሮ ደጋፊዎች አስደንጋጭ ሆኗል።

ሆኖም ይህ ምርጫ በአገሪቱ የፈጠረው መከፋፈል በቀላሉ የመጥፋት ዕድሉ ዝቅተኛ ነው።

የዚህ ምርጫ ውጤት እንደ አውሮፓውያኑ በ2018 በተካሄደው ምርጫ ላይ እስር ቤት በመሆናቸው እና እንዳይወዳደሩ ተግደው የነበሩትን ሉላ ወደ ፖለቲካው የመለሰ ነው።

ፖለቲከኛው በዛ ወቅት የብራዚል መንግሥት የነዳጃ ኩባንያ የሆነው ፔትሮ ብራስ የውል ስምምነት ለማሰር ጉቦ ተቀብለዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸው የነበረ ሲሆን ፍርድ ቤት ጥፋተኛ እንደሆኑ ወስኖባቸው ነበር።

የተላለፈባቸው ብይን ተሰረዞ ወደ ፖለቲካ ህይወታቸው ከመመለሳቸው በፊት 580 ቀናትን በእስር ቤት አሳልፈዋል።

ዳ ሲልቫ አሸናፊ መሆናቸውን ከረጋገጡ በኃላ ባደረጉት ንግግር “ከነ ሕይወቴ ሊቀብሩኝ ሞክረው ነበር። እኔ ግን እዚህ ደርሻለሁ” ብለዋል።

የቅድመ ምርጫ ግምቶች ሉላ እንደሚያሸንፉ አመለክተው የነበረ ቢሆንም በመጀሪያው ዙር የውጤት ልዩነቱ ከተጠበቀው በታች ሆኗል። በዚህም በርካታ ብራዚላውያን የውጤቱን ትክክለኛነት ተጠራጥረው ነበር።

የግራ ዘመሙን ፖለቲከኛ አሸናፊነት አንቀበልም የሚሉት የቦልሶናሮ ደጋፊዎች ዳ ሲልቫን “ሌባ” እያሉ የሚጠሯቸው ሲሆን ክሳቸው መሰረዙ ነጽህናቸውን የሳያል ማለት አይደለም ይላሉ።

ጄር ቦልሶናሮ ቢሸነፉም ለሳቸው ቅርበት ያላቸው ህግ አውጪዎች የምክር ቤቱን አብላጫ መቀመጫ አግኝተዋል። ይህ ማለት ሉላ በፕሬዝዳንትነት ዘመናቸው የሚያወጧቸው ፖሊሲዎች በምክር ቤቱ ከፍተኛ ተቃውሞ ይገጥመዋል ማለት ነው።

ሆኖም እንደ አውሮፓውያኑ ከ2003 እስከ 2010 ለሁለት የምርጫ ዘመን በስልጣን የነበሩት ሉላ ፖለቲካዊ ጥምረት ለመመሰረት አዲስ አይደሉም።

በዘንድሮ ምርጫ መክትላቸው ሆነው የተወዳደሩት እና ከዚህ ቀደም ተቃዋሚያቸው የነበሩትን አልኪም ከጎናቸው ማሰለፍ ችለዋል።

ዳ ሲልቫ አሸናፊ መሆናቸው ከተረጋገጠ በኃላ ባደረጉት ንግግር በተለሳለሰ ሁኔታ የመረጧቸውን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ብራዚላውያንን እንደሚያገለግሉ ተናግረዋል።

“ይህ አገር ሰላም እና አንድነት ይፈልጋል። ይህ ሕዝብ ከዚህ በኃላ ጸብ አይፈልግም” ብለዋል። የ77 ዓመቱ ሉላ ፖለቲካን ከመቀላቀላቸው በፊት የብረታ ብረት ባለሙያ ነበሩ።