የዩኬ ሙዝየሞች የጸረ ቅኝ ግዛት ታጋዮችን ቅሪተ አካል ለዚምባብዌ ለመመለስ ተስማሙ

መሀል ላይ ያለችው ሙቡያ ኔህንዳ በጸረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄ ትታወቃለች

የፎቶው ባለመብት, Alamy

የምስሉ መግለጫ, መሀል ላይ ያለችው ሙቡያ ኔህንዳ በጸረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄ ትታወቃለች

በቅኝ ግዛት ዘመን ከዚምባብዌ የተወሰዱ ቅሪተ አካሎችን ለመመለስ ከዚምባብዌ መንግሥት ጋር እንደሚተባበሩ የለንደን ብሔራዊ የታሪክ ሙዝየም እና ኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ አስታወቁ።

የዚምባብዌ ልዑካን ከሁለቱ ተቋማት ጋር ከተነጋገሩ ነው ይህ የተባለው።

ቅሪተ አካሎቹ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ማገባደጃ ላይ በጸረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄ የሚታወቁ የዚምባብዌ የነጻነት ታጋዮች ናቸው።

ቅሪተ አካሎቹ ዩናይትድ ኪንግደም እንደሚገኙ ይታመናል።

የእንግሊዝን ቅኝ ግዛት ከታገሉ መካከል ንቅናቄውን በመምራት የሚታወቁትት ሰዎች አስክሬን ወደ ዩኬ መወሰዱን የዚምባብዌ ባለሥልጣኖች ያምናሉ።

ነገር ግን እስካሁን የት እንዳሉ በትክክል አልታወቀም።

እአአ በ1890ዎቹ የተነሳው ንቅናቄ ፈርስት ቺሙሬንጋ ይባላል።

የዚህ ንቅናቄ መሪ ከነበሩ መካከል በዋነኛነት የምትጠቀሰው ሙቡያ ኔህንዳ ናት። ከጠፉት ቅሪተ አካሎች አንዱም የሷ ነው።

እንድትገደል የተፈረደባት ዛሬ ሀራሬ በሆነችው የቀድሞ የአገሪቱ ቀጠና ነበር። በዚምባብዌ ብሔራዊ ጀግናም ናት።

የለንደም ብሔራዊ የታሪክ ሙዝየም ባደረገው ምርምር “ከዚምባብዌ የመጡ ሊሆኑ ይችላሉ” የተባሉ 11 ቅሪተ አካሎች አግኝቷል።

ሙቡያ ኔህንዳ እዚህ ግኝት ውስጥ አልተካተተችም።

ከ11ዱ ቅሪተ አካሎች መካከል እአአ በ1893 ከዚምባብዌ የቀድሞ ከተማ ቡልዋዮ የተወሰዱ የሦስት ሰዎች የጭንቅላት ቅሪቶች ይጠቀሳሉ።

በኬምብሪጅ ዩኒቨርስቲ የሚገኘው ደክወርዝ ቤተ ሙከራ እንዳለው “ውስን ከዚምባብዌ የተወሰዱ ቅሪተ አካሎችን” ነው ማግኘት የቻለው።

እነዚህ ቅሪተ አካሎች የጸረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄው ፈርስት ቺሙሬንጋ አባላት መሆናቸው እንዳልተረጋገጠ ለቢቢሲ ገልጿል።

ብሔራዊ የታሪክ ሙዝየም ውስጥ 25,000 ቅሪተ አካሎች ሲገኙ ቤተ ሙከራው ውስጥ ደግሞ 18,000 ቅሪተ አካሎች አሉ።

በዓለም በመዛግብት ብዛት በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ መካከል ናቸው።

በታሪካዊ ስፍራዎች በተካሄዱ ቁፋሮዎች የተገኙት ቅሪተ አካሎች እንዳሉ ሆነው፣ በጊዜ ሂደት ከየት እንደተገኙ ለማወቅ ያልተቻለም ይገኙበታል።

ሀራሬ የሚገኝ የሙቡያ ኔህንዳ ኃውልት

የፎቶው ባለመብት, SHUTTERSTOCK

የምስሉ መግለጫ, ሀራሬ የሚገኝ የሙቡያ ኔህንዳ ኃውልት

በቅኝ ግዛት ዘመን በውጊያ ከሞቱ ሰዎች አስክሬን ላይ የሰውነት ክፍል ይወሰድ ነበር። ከተቀበሩበት አስክሬናቸው ወጥቶም ተወስዷል።

ይህም እንደ ‘ድል ዋንጫ’ የሚወሰድ አልያም ‘ለምርምር’ በሚል የሚወሰድ ነበር።

በ19ኛው ክፍል ዘመን ፍሬኖሎጂ በተባለው የትምህርት ዘርፍ የሰዎችን የጭንቅላት ቅሪት በማየት ስለ ባህሪያቸው ማወቅ ይቻላል የሚል መላ ምት ላይ ምርምር ይደረግ ነበር።

ይህ መላ ምት ኋላ ላይ ሰዎችን ዘር ላይ ለተመሠረተ ክፍፍል (መድልዎም) እንደሚዳርግ ተደርሶበታል። ከአንድ አካባቢ የመጡ ሰዎችን ከሌሎች አካባቢዎች ተወላጆች ‘በተፈጥሯቸው ያነሱ’ ወደሚል የተዛባ ድምዳሜ የሚያመራም ነበር።

ምርምሩ በሚደረግበት ወቅት ግን ለጥናት ግብአት እንዲሆኑ በርካታ ቅሪተ አካሎች ተሰብስበዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በዩኬ የሚገኙ ቅሪተ አካሎች በዚህ መላ ምት አራማጆች የተሰበሰቡ አልያም በግለሰቦች የተሰበሰቡ ናቸው።

የዚምባብዌ መንግሥት እንደሚለው የጸረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄ አመራሮችና አባላት ቅሪተ አካል በየትኛውም መንገድ ይሁን የዩኬ ሙዝየም ደርሷል።

ቅሪተ አካላቸው ከተወሰዱ መካከል ኋላ ላይ ሙቡያ ኔህንዳ በመባል የምትታወቀው መንፈሳዊ መሪ ቻርዊ ንያካሱካና ትገኝበታለች።

የቀደምቶች መንፈስ በሷ በኩል እንደሚተላለፍ የሚታመን ሲሆን፤ ኔህንዳ የሚለው ስም የተሰጣት ኔህንዳ ከተባለው የቀደምት መንፈስ በመነሳት ነው።

የቅኝ ግዛት ዘመን የእንግሊዝ ባለሥልጣን ገድለሻል ተብላ ታስራ ነበር።

ከዚያም በስቅላት ተገድላ ሰውነቷ እንዲቆራረጥ መረደጉ ይነገራል።

ከዚያ በኋላ ምን እንደተከሰተ ግልጽ ባይሆንም፤ ቅሪተ አካሏ በለንደን ብሔራዊ የታሪክ ሙዝየም እንደሚገኝ የዚምባብዌ ባለሥልጣናት ይናገራሉ። 

በስቅላት ስትገደል “አትጠራጠሩ አጥንቴ ይነሳል” እንዳለች ታሪክ ያስረዳል።

በቅኝ ግዛት ንቅናቄ በርካቶችን እንዳነሳሳችም ይነገርላታል።

ዚምባብዌ እአአ በ1980 ነጻነቷን አግኝታለች።

በሀራሬ በሚገኝ አውራ ጎዳና ኃውልት ቆሞላታል።

አምና ኃውልቱ ሲቆም ፕሬዝዳንት ኤመርሰን ምናንጋግዋ ቅሪተ አካሏን ከለንደኑ ሙዝየም እንደሚያስመልሱ ቃል ገብተዋል።

ከሁለት ዓመት በፊት ወደ ዩኬ የተጓዘውን የልዑካን ቡድን የመሩት ጉድፍሬይ ማህቺ እንዳሉት፤ በዚምባብዌ አንድን ሰው ገድሎ ጭንቅላቱን ከአስክሬኑ ላይ ቆርጦ መውሰድ “ሰውን ከመቃብር በላይም መቅጣት ነው” ተብሎ ይታመናል።

“የሰው ጭንቅላት ከሰውነቱ ከተለያየ እስከወዲያኛው ድረስ ነፍሱ አታርፍም” ብለዋል።

የልዑካን ቡድቡ ወደ ዩኬ ሲያቀና እንዳቀደው የጸረ ቅኝ ግዛት ንቅናቄ ጀግኖችን ቅሪተ አካል ባያገኝም፤ ሙዝየሙ እና ዩኒቨርስቲው ትብብር ለማድረግ ተስማምተዋል።

የዚምባብዌ ልዑካን ከኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ፣ ከፒት ሪቨርስ ሙዝየም እና ከሌሎችም ሙዝየሞች ጋር ተገናኝቷል።

የዚምባብዌ መንግሥት የካቢኔ ስብሰባ ላይ “በዩኬ የዚምባብዌ ልጆች ቅሪተ አካሎች አሉ። አያት ቅድመ አያቶቻችንን ወደ አገራቸው እናስመልሳለን” ተብሏል።