ሞቷል የተባለውን የልጇን ደፋሪ አፈላልጋ በሕይወት ያገኘችው ሕንዳዊት እናት

የፎቶው ባለመብት, SWASTIK PAL
ባለፈው የፈርንጆች ዓመት ነው። በምዕራብ ሕንድ ቢሃር ግዛት ነዋሪው የሆነች እናት አንድ ዜና ይደርሳታል - “የልጅሽ ደፋሪ ሞቷል” የሚል።
በዚህም ምክንያት በመድፈር ወንጀል የከፈተው ክስ ይዘጋል። ነገር ግን እሷ ጉዳዩን በቀላሉ አልተቀበለችውም።
የልጇ ደፋሪ መሞትን ተጠራጠረች። የተከሳሹን መሞት የሚያረጋግጥ ሰርተፊኬት ለቀረበለት ጉዳዩን ለያዘው ፍርድ ቤት ተጠርጣሪው ስላለመሞቱ ማረጋገጨ ማምጣት ይኖርባታል።
ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ሁለት ሰዎች ሕንዳውያን አስከሬን በሚያቃጥሉበት [በሕንድ አስከሬን በመቅበር ፈንታ ይቃጠላል] አንድ ወንዝ ዳርቻ ደረሱ። ይህ ስፍራ ቅዱስ ወንዝ እንደሆነ ይታመናል።
በቦታው የደረሱት የሟች ሂንዱዎች አስከሬን የማቃጠል ሥነ ሥርዓትን ለመፈጸም ነበር። ነገሮች ግን ሌላ መልክ ያዙ።
ሁለቱም አስከሬን የሚያቃጥሉበት እንጨት ይደረድሩ ጀመር። ግርምት የፈጠረው ግን ግለቦቹ አስክሬን ለማቃጠል እንጨት ይሰብስቡ እንጂ የሚቃጠል አስክሬን አልያዙም ነበር።
በኋላም ከሁለቱ ግለሰቦች በዕድሜ የሚያንሰው ከተሰበሰበው እንጨት ላይ ተንጋሎ አስክሬን መስሎ ተኛ። ሰውነቱ በነጭ ጨርቅ ሲሸፈን እሱም ዓይኑን ጨፈነ። ሌላኛው ግለሰብ የተኛው ሰው ላይ እንጨት ደራርቦ ማስቀመጥ ቀጠለ። የሰውየው ጭንቅላት ብቻ እስኪቀር መላው ሰውነቱ ላይ እንጨቱ ተደረደረ።
ይህ ሁሉ ሲሆን ሁለት ፎቶዎች ተነስተዋል። ማን እነዚህን ፎቶዎች እንዳነሳ ግን አይታወቅም። ሦስተኛ ሰው ስለመኖሩም ምንም የታወቀ ነገር የለም።
የሞተ ሰው መስሎ ፎቶግራፍ የተነሳው ግለሰብ ሞዲ ይባላል። 39 ዓመቱ ሲሆን በመንግሥት ትምህርት ቤት በመምህርነት ያገለግላል። ሌላኛው ግለሰብ ደግሞ አባቱ ራጃራም ሞዲ ናቸው። ዕድሜያቸው በስድሳዎቹ ውስጥ ይገመታል።

የፎቶው ባለመብት, SWASTIK PAL
ይህ ሁሉ የሆነው ፖሊስ ኒራጅ ሞዲ ላይ የመድፈር ክስ ከመሠረተ ከስድስት ቀናት በኋላ ነው። ሞዲ የተከሰሰው የ12 ዓመት ታዳጊ ደፍሯል ተብሎ ነበር።
ተማሪው የነበረችውን ልጅ ደፍሯል የተባለው በፈረንጆቹ 2018 ነበር። ታዳጊዋ ጥቃቱ የደረሰባት በሸንኮራ አገዳ ማሳ ውስጥ ብቻዋን በነበረችበት ወቅት ነው።
ታዳጊዋ የደረሰባትን ለሰው ከተናገረች ድርጊቱን ሲፈጽም በስልኩ መቅረጹን በመንገር በማኅበራዊ ሚዲያዎች እንደሚያሰራጨው አስፈራርቷታል።
እናት በልጇ ላይ የተፈጸመውን ባወቀች ጊዜ ጉዳዩን ይዛ ለሕግ አቤት በማለቷ ሞዲ በቁጥጥር ስር ይውላል። በሕግ ጥላ ስር የቆየው ግን ለሁለት ወራት ብቻ ነው።
ኒራጅ ሞዲ ባለፈው ዓመት “ከሞተ” በኋላ ግን ነገሮች በነበሩበት ቀጠሉ። አባቱም ፍርድ ቤት ቀርበው መሞቱን ተናገሩ። የሞት የምስክር ወረቀት (ሰርትፊኬት) በመውጣቱም “ብቸኛው ተከሳሽ በመሞቱ” ፋይሉ ተዘጋ።
እናት ግን ይህን መቀበል አልቻለችም። መምህሩ የውሸት ሞትኩ ብሎ በመደበቅ ከፍርድ ሊሸሽ ነው በሚል ነው ያልተቀበለችው። ይህች እናት የምትኖረው የሞዲ ቤተሰቦች በሚገኙበት አነስተኛ መንደር ነው።
“ኒራጅ ሞዲ ሞቷል ሲባል ወዲያው ነው ውሸት መሆኑ የገባኝ። በሕይወት እንዳለ አውቄያለሁ” ስትል እናትዬው በቅርቡ ለቢቢሲ ተናግራለች።
ሕንድ ከ700 ሺህ በላይ የገጠር መንደሮች አሏት። በከተሞች ከሚሞቱ ሰዎች ይልቅ በእነዚህ መንደሮች የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው።
አብዛኛዎቹም ሕይወታቸው የሚያልፈው በቤታቸው ውስጥ ነው። ለ54 ዓመታት ሥራ ላይ የቆየው የአገሪቱ ሕግ ሰዎች ሲወለዱም ሆነ ሲሞቱ እንዲመዘገቡ ያስገድዳል። የሞቶች ምክንያት ግን አይጠየቅም።

የፎቶው ባለመብት, SWASTIK PAL
በቢሃር መንደር የሚገኝ ሰው ሲሞት ቤተሰቦቹ የሟችን መታወቂያ ቁጥር ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል። እንዲሁም ሞቱን የሚያውቁ አምስት ሰዎችን በፊርማቸው ያረጋግጣሉ።
ይህ ማስረጃ ለአካባቢው መስተዳደር ይቀርባል። የቀረበው ማመልከቻ ተረጋግጦ በሳምንት ውስጥ የሞት ሰርተፊኬቱ ይሰጣል።
“በመንደራች ያሉ ሰዎች የሚኖሩት በተጣበበ ቦታ ነው። ሰዉ እርስ በእርስ ይተዋወቃል። የሞተ ሰው ካለ የማይታወቅበት ወይም የማንሰማበት ዕድል የለም” ሲሉ የተጎጂዋ ጠበቃ ጃይ ካራን ጉፕታ ተናግረዋል።
ራጃራም ሞዲ የልጁን የመታወቂያ ቁጥር እና የአምስት ነዋሪዎችን ፊርማ ለመስተዳደሩ አስገብቷል። ሕጉ የሚጠይቀው ሁሉ በመሟላቱ የልጁ የሞት ሰርተፊኬትም ተሰጥቶታል። ማስረጃው ግን የልጁን የሞት ምክንያት አይገልጽም።
እናቲቱ ተከሳሹ በመሞቱ ፋይሉ መዘጋቱን ከሕግ ባለሙያው ከሰማች በኋላ፤ “እንዴት ማንም ስለ መምህሩ መሞት አያውቅም? ከሞተስ በኋላ እንዴት መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓቶች አልተከናወኑም? ስለ መሞቱስ እንዴት አይወራም?” ስትል ጠየቀች።
መንደሩ ውስጥ እየተዘዋወረች ኒራጅ ሞዲ ስለመሞቱ ያውቁ እንደሆነ ሰዎችን ጠያየቀች። ማንም ስለህልፈተ ሕይወቱ አልሰማም። ወደ ፍርድ ቤት አቅንታም ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ አቤት አለች። ፍርድ ቤቱ ደግሞ መምህሩ በሕይወት ስለመኖሩ ማስረጃ እንድታቀርብ ጠየቃት።

የፎቶው ባለመብት, SWASTIK PAL
እናቲቱ የመንደሩ ምክር ቤት ሐሰተኛ ማስረጃ ላይ ተመስርቶ የሞት ሰርተፊኬቱን መስጠቱን በመግለጽ አቤቱታ አቀረበች። ጉዳዩ እንዲመረመርም ጠየቀች።
ከዚያ በኋላ ነገሮች በፍጥነት ይቀያየሩ ጀመር።
ኃላፊዎች ጉዳዩ በድጋሚ እንዲታይ ለመንደሩ ምክር ቤት ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፉ። ምክር ቤቱ ግን ኒራጅ ሞዲ መሞቱን የሚያሳዩ ተጨማሪ መረጃዎችን ነው ያገኘው።
ከሞተ በኋላ ያሉ ፎቶዎች፣ አስከሬኑ ሲቃጠል፣ የሚነድ እንጨት፣ የመጨረሻው ሥነ ሥርዓትን የሚያሳዩ ፎቶዎች እና የተጨማሪ የአምስት ሰዎችን ምስክርነት ቀረበ።
የመንደሯ ምክር ቤት አባላት 250 ገደማ ቤቶች ያሏትን መንደር ነዋሪዎች አነጋገሩ። ከነዋሪዎቹ መካከል ግን የኒራጅ ሞዲን ህልፈተ ሕይወት የሰማ አልነበረም።
በሂንዱ የሐዘን መገለጫ ከሆኑ ሥርዓቶች መካከል ቅርብ ቤተሰብ አባላት ፀጉር መላጨት አንዱ ነው። ነገር ግን ከሞዲ ቤተሰብ አባላት ፀጉሩን የተላጨ አልታየም።
“የኒራጅ ሞዲ የቅርብ ቤተሰቦች ጭምር ስለመሞቱ ካለመስማታቸው በላይ የት እንዳለ እንኳን አያውቁም። ሕይወቱ አልፎ ቢሆን ኖሮ የመጨረሻው ሥነ ሥርዓትም በቤታቸው እንደሚከናወን አስታወቁ” ሲሉ መርማሪ ፖሊሱ ሮሂት ኩማር ፓስዋን ገለጹ።
የመንደሯ ምክር ቤት አባላት በድጋሚ ራጃም ሞዲን በጥያቄ ያጣድፉ ጀመር። አሁን ግን ስለልጁ ሕይወት ማለፍ ተጨማሪ ማስረጃዎችን ማቅረብ አልቻለም።
“በድጋሚ ስንጠይቀው የሚያረካ ምላሽ መስጠት አልቻም” የምክር ቤቱ ጸሐፊ ዳርሜንድራ ኩማር ሲሉ ተናግረዋል።
ምርመራው ሲጠናቀቅ ኒራጅ ሞዲ ሳይሞት የውሸት ሞቷል መባሉን አረጋገጠ። አባት እና ልጅ የሞት ሰርተፊኬት ለማግኘት ሐሰተኛ ሰነዶች ማቅረባቸው ተደረሰበት።

የፎቶው ባለመብት, THE NEWS POST
መምህሩ የአምስት ተማሪዎቹን ወላጆች ፊርማ ሳያስፈቅድ ወስዶ የሞት ሰርተፊኬቱን ለማግኘት እንደተጠቀመበት ፖሊስ አረጋገጠ። ለተማሪዎቹ ስኮላርሺፕ ለማመቻቸት በሚል የወላጆቹን ፊርማ መሰብሰቡም ታውቋል።
ግንቦት መገባደጃ ላይ ባለሥልጣናት የኒራጅ ሞዲን የሞት ሰርተፊኬት ሰረዙ። ፖሊሰም አባቱን በቁጥጥር ስር አውሎ ሐሰተኛ ማስረጃ በማዘጋጀት ከሰሳቸው። “እነደዚህ ዓይነት ጉዳይ መርምሬ አላውቅም። ጉዳዩ በእርግጠኝነት ትክክለኛ ቢመስልም የተገላቢጦሽ ሆኖ ነው የተገኘው” ሲሉ ፓስዋን ተናግረዋል።
ሐምሌ ላይ ፍረድ ቤቱ ፋይሉን በድጋሚ ከፈተ። “በማታለል እና በማሳሳት” ተከሳሹ ከቅጣት ለማምለጥ ሞክሯል ብሎ ነው ክሱን በድጋሚ ማየት የጀመረው። መምህሩን ለፍርድ ለማቅረብ ላይ ታች ያለችው እናት ፍርድ ቤት ቀርባ በቁጥጥር ስር ይዋልልኝ ስትል ጠየቀች።
ሞቷል ተብሎ የምስክር ወረቅት ከወጣ ከዘጠኝ ወራት በኋላ ኒራጅ ሞዲ እጁን ሰጠ። በፍርድ ሂደቱ ወቅት ጥፋተኛ አይደለሁም ሲልም አበክሮ ተከራከረ። በዚህ ጊዜ ሁሉ ፍርድ ቤት ሲገባም ሆነ ሲወጣ ተዋርዶ እና በገመድ ታስሮ ነበር።
ባለፈው ወር ፍርድ ቤቱ ሞዲን ጥፋተኛ ብሎታል። ደፍሯል ሲልም የ14 ዓመት እስር አከናንቦታል። ለተጎጂዋም 3628 ዶላር የጉዳት ካሳ እንዲከፈላት ወስኗል።
ራጃራም ሞዲ በበኩሉ በማጭበርበር እና በሐሰተኛ ምስክርነት ሰባት ዓመት በማረሚያ ቤት እንዲያሳልፉ ተፈርዶባቸዋል። አባት እና ልጅ የሞት የምስክር ወረቀቱን የተመለከተው ክሳቸው ደግሞ ገና በመታየት ላይ ይገኛል።












