የፈረንሳይ አየር መንገድ አብራሪዎች በረራ ክፍል ውስጥ ከተደባደቡ በኋላ ከሥራ ታገዱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሁለት የፈረንሳይ አየር መንገድ አውሮፕላን አብራሪዎች በረራ ክፍል ውስጥ ከተደባደቡ በኋላ ከሥራ መታገዳቸው ተገለጸ።
በስም ያልተጠቀሱት ዋና አብራሪ እና ረዳት አብራሪ ከስዊትዘርላንዷ ጄኔቫ ወደ ፓሪስ እየበረሩ ሳለ በቦክስ ድብድብ መግጠማቸውን ሪፖርቶች አመልክተዋል።
ኤርባስ ኤ320 ሲያበሩ የነበሩት አብራሪዎች ድብድብ ሲገጥሙ ድምጽ የሰሙ የበረራ አስተናጋጆች ወደ በረራ ክፍል ገብተው አብራሪዎቹን ገላግለዋል ሲል የስዊትዘርላንዱ ላ ትሪቢዩን ዘግቧል።
ሰኔ ወር ላይ በነበረው በረራ አንዱ አብራሪ በበረራ ክፍሉ ውስጥ እንዲቆይ ከተደረገ በኋላ አውሮፕላኑ በመዳረሻው በሰላም አርፏል ሲሉ የአየር መንገዱ ቃል አቀባይ ለላ ትሪቢዩን ተናግረዋል።
ይህ ክስተት የተሰማው የፈረንሳይ መንግሥት የአየር ደኅንነት መርማሪ አካል (ቢኢኤ) የተወሰኑ የፈረንሳይ አየር መንገድ (ኤየር ፍራንስ) አብራሪዎች የደኅንነት መመሪያዎችን አይጠብቁም የሚል ሪፖርት ካወጣ በኋላ ነው።
ቢኢኤ በሪፖርቱ ዋነኛ ትኩረቱ ያደረገው እአአ 2020 ላይ ከኮንጎ ብራዛቪል ወደ ፓሪስ በነበረ በረራ የተከሰተውን ክስተት ነው።
በዚህ በረራ ላይ አውሮፕላኑ ነዳጅ ያፈሰሰ ሲሆን፤ በደኅንነት መመሪያ መሠረት አብራሪዎቹ ወደ አውሮፕላኑ ሞተር የሚሄደውን ኃይል መቀነስ አልያም በአስቸኳይ ማረፍ ይጠበቅባቸው ነበር ብሏል ቢኢኤ።
ምንም እንኳ አውሮፕላኑ በቻድ እንዲያርፍ ቢደረግም፣ አብራሪዎቹ በመመሪያው መሠረት ፈጣን እርምጃ አለመውሰዳቸው ሞተሩ በእሳት የመያያዝ እድልን ይፈጥር ነበር ብሏል።
ቢኢኤ በሪፖርቱ ከእአአ 2017 እስከ 2022 ድረስ ተመሳሳይ ክስተቶች አጋጥመው አብራሪዎች የደኅንነት መመሪያዎችን ከመከተል ይለቅ ችግርን በማጤን የራሳቸውን የመፍትሄ እርምጃ ሲወስዱ ነበር ብሏል።












