የቤት ውስጥ ጥቃትን አሸንፋ ዓለም አቀፍ እውቅናን የተቀዳጀችው ቲና ተርነር

ቲና ተርነር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ቲና ተርነር በሻካራ ድምጿ ብቻ ሳይሆን በመድረክ ላይ እንቅስቃሴዋ አድናቂዎቿ ያውቋታል።

ቲና ከተወለደችበት ገጠራማው ቴኔሲ ዓለም አቀፍ እውቅና እስካገኘችበት ድረስ የሄደችበት ሕይወቷ አልጋ በአልጋ አልነበረም።

ጥቃት ያደርስባት የነበረ ባሏን ትታ ብቻዋን የሙዚቃ ስራዋን መስራት ስትጀምር እድሜዋ 40 ሞልቶ ነበር።

ቲና ተርነርን የእድሜዋ መግፋት አልያም ያሳለፈችው ጥቃት የተሞላበት የፍቅር እና ትዳር ሕይወት አላደበዘዘውም።

የሙዚቃ አልበሞቿን በከፍተኛ ቁጥር ከመሸጥ ጀምሮ፣ መለያዋ የሆኑ የመድረክ ስራዎችን ወደማቅረብ እና ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን በእጇ እስከ ማስገባት የደረሰችው ከዚህ ሁሉ በኋላ ነው።

የደፈረሰ ልጅነት

ቲና ተርነር የተወለደችው እኤአ ሕዳር ወር በ26ኛው ቀን በ1939 ዓ.ም ነው።

ይህች ስሟ እዚህ ግቢ የማትባል የትውልድ መንደሯ፣ ኑትቡሽ፣ በቴናሲ ውስጥ ትገኛለች።

አባቷም አፈር ገፍቶ የሚያድር ገበሬ ነበር፥

የመዝገብ ስሟም አና ሜ ቡለክ ይሰኛል።

የአና ልጅነት ደስታ የራቀው ነበር።

ቤተሰቦቿ የጥይት ፋብሪካ ስራ አግኝተው ሲሄዱ፣ እርሷን አያቶቿ ጋር ትተው እህቷን ብቻ ያዘው በመሄዳቸው ተለያይተው ነው ያደጉት።

በዚህም የተነሳ ኃይማኖታቸውን አጥባቂ በሆኑ አያቶቿ መዳፍ ውስጥ ወደቀች።

ቤተሰቦቿ ከጦርነት በኋላ ዳግም ተመልሰው ሲገናኙ፣ አና ሜ በአካባቢያቸው በሚገኝ የባብቲስት ቤተ እምነት ውስጥ መዘመር ጀምራለች።

አና ሜ 11 ዓመት ሲሞላት እናቷ ከአባቷ ጋር ተለያይታ ቤቱን ጥላ ሄደች።

አባቷ ዳግም ሲያገባ እርሷ እና እህቷ አያቶቻቸው ወደሚኖሩበት ብራውንስቪል፣ ቴኔሲ ሄዱ።

እዚያም በምትማርበት ትምህርት ቤት ቺርሊደር ሆና ማገልገል ቀጠለች።

አና ሜ ቅርጫት ኳስ መጫወት እንዲሁም ግርግር የበዛበት ማሕበራዊ ህይወት ወዳድ ነበረች።

በ1958 ከተመረቀች በኀላ ሚዙሪ በሚገኘው በቅዱስ ሉዊስ ሆስታል ውስጥ ስራ አግኘች።

እርሷ እና እህቷ አንድ ምሽት የሄዱበት የምሽት ክበብ፣ አይኬ ተርነር ከባንዱ ጋር ሲጫወት ተመለከቱት። ይህ የሙዚቃ ሕይወቷ ጅማሮ የተሟሸበት ሆነ

ቲና ተርነር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ወርቃማ እድል

አይኬ ስሙን በሙዚቃው ኢንደስትሪ ውስት የተከለ ባለሙያ ነው። የሙዚቃ ባንዱም ቢሆን አር ኤንድ ቢ አድናቂዎች የሚንሰፈሰፉለት እና በወቅቱ በነበሩ የምሽት ክበቦች ተፈላጊ የሆነ ነው።

አንድ ቀን ባንዱ ተጫውቶ እረፍት ሲያደርግ አና ሜ ድምጽ ማጉያው ተሰጥቷት እንድትዘፍን ተደረገ።

አይኬ በሰማው ነገር ከመደመሙ የተነሳ ከባንዱ ጋር እንድትሰራ ጥያቄ አቀረበላት።

በዚያ ወቅት ከባንዱ የሳክስፎን ተጫዋች፣ ሬይመንድ ሂል፣ ጋር የፍቅር ግንኙነት ውስጥ የነበረች ሲሆን ልጅም ወልዳለት ነበር።

በ1958 ተቀባይ በመሆን ከባንዱ ጋር መስራት ጀመረች።

ከሁለት ዓመት በኋላ ግን እድል በሯን አንኳኩታ መጣች።

ፉል ኢን ላቭ (Fool in Love) የተሰኘው እና በተርነተር የተጻፈውን ሙዚቃ እንድትዘፍን ተደረገ።

የሙዚቃ ባንዱ ዋነኛ ድምጻዊ የነበረው አርት ላሲተር፣ በቀረጻ ወቅት መገኘት ባለመቻሉ አና ሜ በኋላ ላይ ዋናው ድምጻዊ ሲመጣ የእርሷን ድምጽ አውጥተው በእርሱ እንተካዋለን ያሉ ባለሙያዎች እነድትዘፍነው አደረጉ።

ነገር ግን የመጀመርያውን ቅጂ የሰማ አንድ ዲጄ በጣም ስለወደደው ወደ የሙዚቃ አሳታሚ ዘንድ አሳልፎ ሰጠው።

ቲና ተርነር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የሙዚቃ ሰንጠረዦች አናት ላይ የተቀመጠችው ቲና

አይኬ አዲሷን ምልምል ከጀርባ ሆኖ ከመቀበል ከፊት ሆኖ ወደ መጫወት አንድትመጣ አግባባት።

ሲያግባበት ግን ስሟን ቲና ብላ እንድትቀይር ጭምር ነበር።

ፉል ኢን ላቭ በቢልቦርድ ስጠረዥ ላይ 27ኛ ደረጃን ያዘ።

በመቀጠል የሰራችው ጎነ ወርክ አውት ፋይን (Gonna Work Out Fine) ደግሞ ምርጥ 20ዎቹ ውስጥ መግባት ቻለ።

ሁለት ግራሚዎችንም በእጇ አስገባች።

በዚህ ወቅት አምስት ሚስቶችን ከፈታው አይኬ ጋር የፍቅር ግንኙነት መስርታ ነብረ።

በ1962 ዓ.ም ተጋቡ።

አይኬ እና ቲና ተርነር ተጣምረው ለሶስት ዓመት ያህል የተለያዩ የሙዚቃ ስራዎችን ቢሰሩም ምንም ኣይነት ደረጃ ሰንጠረዥ ላይ መውጣት የቻለ ሙዚቃ ግን ሊኖራቸው አልቻለም።

ቲና በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣብያዎች ላይ በሚቀርቡ ትርዒቶች ለብቻዋ በመሆንም መቅረብ ጀመረች።

ፕሮዲውሰሩ ፊል ስፔክተር በቲና ድምጽ ተደምሟል።

ተደምሞ ብቻ አልቀረም ሪቨር ዲፕ ማውንቴን ሀይ(River Deep, Mountain High) የተሰኘውን ሙዚቃዋን እንድትቀርጽ አደረጋት።

ይህ ግን ለትዳር አጋሯ አይኬ የሚዋጥ አልሆነም።

አይኬ ሁሉን ልቆጣጠር ባይ ነው።

የሙዚቃ ቀረጻዎችንም ለመቆጣጠር ይፈልጋል። ስፔክተር ግን ከቀረጻ ስቱዲዮ እንዲርቅ ከፈለው።

ቲና ተርነር ከባሏ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከጥቃት ያመለጠችው ቲና

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከስፔክተር ጋር የቀረፁት እና ስፔክተር ፊቸሪንግ የገባበት ስራ ምንም እንኳ የቲና ድምጽ ብቻ ያለበት ቢሆንም በአይኬ እና ቲና ተርነር ስም ነው የታተመው።

የሙዚቃ ስራው በአሜሪካ እምብዛም ተቀባይነት ሳያገኝ ቆይቶ በዩኬ ግን ተወደደ።

ይህ ሮሊንግ ስቶኖች በዩኬ የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ሲያቀርቡ አብራቸው እንድትዘፍን ለመጠየቅ ከበቂ በላይ ምክንያት ሆነ።

በተጨማሪም ደግሞ በሌሎች የአውሮጳ አገራት በርካታ የሙዚቃ አፍቃሪዎች ባሉበት ስራዎቿን የማቅረብ እድል ሰጣት።

ሮሊንግ ስቶን በአሜሪካም የሙዚቃ ስራዎቻቸውን ሲያቀርቡ አብራ የማቅረብ እድል አገኘች።

ከሁለት ዓመት በኋላም ጥንዶቹ በአሜሪካ ከፍተኛ ተወዳጅነት ያገኘውን ነጠላ ዜማ ፕራውድ ሜሪን መስራት ቻሉ።

ፕራውድ ሜሪ የክሪዴንስ ክሊርወተር ሬቪቫል (Creedence Clearwater ) ስራ ነው።

በ1973 ቲና ወደ ለንደን ተጉዛ ከፍተኛ ተቀባይነት ማግኝት የቻለ ስራ አቀረበች።፥

በዚያው ዓመት ጥንዶቹ የመጨረሻቸው የሆነውን ኑትቡሽ ሲቲ ሊሚት (Nutbush City Limits) የተሰኘ ምርጥ ስራቸውን በጋራ ሰሩ።

የሁለቱ የፍቅር ግንኙነት ግን እያደር እየጎመዘዘ እየሄደ ነበር።

ቲና ነፍሰጡር እያለች ባሏ ይደበድባት ነበር። ትኩስ ቡና ደፍቶባት ያውቃል።

በ1976 በቦርሳዋ ርጋፊ ሳንቲም ይዛ ከቤቷ በመውጣት ጓደኞቿ ጋር ተደብቃ እየኖረች የፍቺ ትያቄ ፍርድ ቤት አስገባች።

ከዚያ በኋላ ጓደኛዋ የሆነ ፕሮዲውሰር በገንዘብ አግዟት ለብቻዋ የሙዚቃ ስራዎቿን ለአንድናቂዎቿ ማቅረብ ጀመረች።

በእርግጥ መጀመርያ ላይ ትንሸ መንገራገጭ የነበረው ቢሆንም በኋላ ግን ስሟን መትከል ቻለች፣ ዝናዋ መተኮስ ጀመረ።

ለጀርመን ቮግ “በርካታ ሰዎች ቲና ተርነር ያበቃላት መስሏቸው ነበር።

“እነርሱ የሚያውቁት ኤእኬ እና ቲና ተረነርን ብቻ ነበር። ምን እየተካሄደ እንደነበር ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም። ስለዚህ ራሴን መፈተን ነበረብኝ” ብላ ነበር።

ለብቻዋ የሰራቻቸው ሁለት የሙዚቃ አልበሞች ተቀባይነት ካጡ በኋላ ራሷን ዳግም መስራት ቻለች።

ይህም ከሮድ ስቲዋርት እና ከሮሊንግ ስቶኖች ጋር ዳግም የመስራት እድል እንድታገኝ አደረገ።

በ1983 የሰራችው ሌትስ ስቴይ ቱጌዘር (Let's Stay Together) የሙዚቃ ሕይወቷ ዳግም ያንሰራራበት ስራ ነው።

ለንደን የተቀረጸው ‘ፕራይቬት ዳንሰር’ የሙዚቃ አመልበምም ሰባት የሙዚቃ ሰንጠረዦች ላይ ቁንጮ ለመሆን የቻለ ሲሆን ዓለም አቀፍ የሙዚቃ መድረኮችንም እንድታዘጋጅ አድርጓል።

ከሁለት ዓመት በኋላም ወደ ስክሪን ብቅ ብላ በማድ ማክ ቢዮንድ ተንደርስቶርም (Mad Max Beyond Thunderdome)ላይ አንት ኢንቲቲ (Aunty Entity) ሆና መተወን የቻለች ሲሆን፣ የማጀብያ ሙዚቃዎችንም ሰርታለች።

ከማጀብያ ሙዚቃዎቿ መካከል የፊልሙ መግቢያ ሙዚቃ ዊዶንት ኒድ አናዘር ሂሮ (We Don't Need Another Hero) ይገኝበታል።

ቲና በ1980ዎቹ ተወዳጅ ሙዚቃዎች በአናት በአናቱ ለአድማጮች ስታደርስ፣ ዓለም አቀፍ የሙዚቃ መድረኮችን በተለያዩ አገራት ስታዘጋጅ የነካሽው ሁሉ ይጣፍጥ ተብላ የተመረቀች ትመስል ነበር።

ቲና ተርነር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ለእርጅና ፊት አልሰጥም

ቲና ዝናዋ በ1990ዎቹም ቀጥሎ ነበር።

የመጀመሪያውን የጀምስ ቦንድ ፊልም ማጀብያ ሙዚቃ ጎልደን አይ (GoldenEye) መጫወት ቻለች።

በ61 ዓመቷም በከፊል ራሷን ከሙዚቃ ስራዎች ማሳረፏን ገለፀች።

ቲና ተርነር በጾተኝነት የምትጠራ ሲሆን በ2003 ቢዮንሴ፣ ኦፕራ ዊንፍሬ፣ አል ግሪን እና ጆርጅ ቡሽ በተገኙበት በኬኔዲ ሴንተር የክብር ግብዣ ተደርጎላታል።

በ2008 ዳግም በመምጣት በግራሚ አዋርድ ላይ ስራዎቿን ያቀረበች ሲሆን በሙዚቃ ያሳለፈችውን 50 ዓመታት የሚዘክር የሙዚቃ ዝግጅቶችን አቅርባለች።

በወቅቱ ድምጿ እድሜዋ ያልተጫነው፣ የመድረክ አያያዟ ዛሬም ቢሆን ሳቢ መሆኑን ያስመሰከረችበት ነበር።

በ2013 ደግሞ በ73 ዓመቷ በእድሜ ገፍተው በቮግ መጽሔት ላይ ከቀረቡ ሰዎች መካከል ቀዳሚዋ ሆናለች።

በወቅቱ “ለእርጅና ፊት አልሰጥም” ያለችው ቲና “ደግሞ አላረጀሁም” ስትል ተናግራ ነበር።

ከዚያም በኋላ ለ27 ዓመታት በጓደኝነት ከቆዩት እና ኤክስኪውቲቭ ፕሮዲውሰር ከሆነው ፍቅረኛዋ ኤርዊን ባች ጋር ተጋብተዋል።

በዚህም የአሜሪካ ዜግነቷን ትታ ስዊዘርላንዳዊ ሆናለች።

በ2020 ዳግም የሰራችው 'ዋትስ ላቭ ጎት ቱ ዱ ዊዝ ኢት' በዩኬ ምርጥ አርባዎቹ ውስጥ ተካትቷል።

ይህም ሰባት አስርታትን ወጤታማ የሆነቸ የመጀመርያዋ ሙዚቀኛ በመሆን ቀዳሚ አድርጓታል።

በዓመቱ የስራዎቿን የመብት ድርሻ በ50 ሚሊዮን ዶላር ለቢኤምጂ ራይትስ ማኔጀመንት ሸጠች።