የሮክ ኤንድ ሮል ሙዚቃ ንግሥት ቲና ተርነር በ83 ዓመቷ አረፈች

 የሮክ ኤንድ ሮል ሙዚቃ ንግስት አሜሪካዊቷ ቲና ተርነር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

‘ዋትስ ላቭ ጋት ቱ ዱ ዊዝ ኢት’፣ ‘ዘ ቤስት’ በሚሉት ዘመን ተሻጋሪ ሙዚቃዎች የምትታወቀው የሮክ ኤንድ ሮል ሙዚቃ ንግስት አሜሪካዊቷ ቲና ተርነር በ83 ዓመቷ አረፈች።

ሙዚቀኛዋ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በካንሰር፣ ስትሮክና ኩላሊት ህመምን ጨምሮ በበርካታ የጤና እክሎችም ስትሰቃይ ነበር።

ቲና በሙዚቃ መድረኩ መንገስ የጀመረችው በአውሮፓውያኑ 1960 ነበር።

ዘመን፣ ትውልድና፣ ቋንቋ ያልገደባቸው ፕራውድ ሜሪ፣ ሪቨር ዲፕ፣ ማውንቴን ሃይ የሚሉት ሙዚቃዎቿ በሙዚቃ ኢንዱስትሪው ውስጥ የራሳቸውን አሻራ ማሳረፍ ችለዋል።

ወደ ሙዚቃው ስትገባ ከባለቤቷ ኢክ ጋር የነበረ ቢሆንም በርካታ ጥቃቶች ያደረሰባትን ባለቤቷን በአውሮፓውያኑ 1978 ፈታችው።

በ1980ዎቹ ብቻዋን በመውጣት የበለጠ ስኬትን መጎናጸፍ ቻለች።

የሮክ ኤንድ ሮል ሙዚቃ ንግሥት የሚል ስያሜ ያተረፈችው ቲና ተርነር በሚያስገመግም፣ ልብ ሰርስሮ በሚገባ ድምጿና ኃይል በተሞላ የመድረክ አቀራረቧ በሙዚቃ አድማጮች ዘንድ አይረሴ ሆናለች።

የእረፍቷ ዜናም ይፋ የሆነው በአርቲስቷ ኢንሰታግራም ገጽ ላይ ነው።

“በሙዚቃዋ እንዲሁም ወሰን በሌለው የህይወት አፍቃሪነቷ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አድናቂዎችን አትርፋለች። እንዲሁም ለመጪው ትውልድ ፈር ቀዳጅ ሆናለች፤ አነሳስታለች” ይላል ከእረፍቷ ዜና ጋር የተያያዘው ጽሁፍ

“ዛሬ ውድ ጓደኛችንን እንሰናበታለን። የህይወቷ ታላቅ ስራ የሆነውን ሙዚቃዋንም የተወችልን ቲናን ተሰናብተናታል” ይላል።

ቲና ተርነር ለሙዚቃው ባበበረከተችው አስተዋጽኦ ስመ ጥሩውን የግራሚ ሽልማትን ስምንት ጊዜ አሸንፋለች።

ቲና በአሁኑ ወቅት የዓለም የሙዚቃ መድረኩን የሚመሩትን ቢዮንሴ፣ ጃኔት ጃክሰን፣ ጃኔል ሞኔ እና ሪሃና ላይ አስተዋጽኦ እንዳደረገችም ሙዚቀኞቹ ሲናገሩ ይደመጣሉ።

ሙዚቀኛዋ ማረፏን ተከትሎ በርካታ ግለሰቦች አርቲስቷ ያበረከተቻቸውን ሙዚቃዎች፣ ምን ያህል ለጥቁር ሙዚቀኞች በር እንደከፈተች፣ ነጻነት ምን ማለት እንደሆነ እንዳስተማረች እንዲሁም የጥንካሬ ተምሳሌቷን እያነሱም ኃዘናቸውን በመግለጽ ይገኛሉ።

ለ30 ዓመታት ያህል የቲና ስራ አስኪያጅ የነበረው ሮጀር ዴቪስ “ቲና በጥንካሬዋ፣ በሚያስደንቅ ጉልበት እና ታላቅ ችሎታዋ ልዩ እና አስደናቂ የተፈጥሮ ኃይል ነበረች” ብሏል።

“ከተዋወቅንበት 1980 ጀምሮ በርካቶች የሌላቸው እሷ ግን ሙሉ በሙሉ በራሷ ትተማመን ነበር። በጣም እናፍቃታለሁ” ሲልም አክሏል

ታዋቂዋ ሞዴል ናኦሚ ካምቤል፣ የቅርጫት ኳስ ዝነኛው ማጂክ ጆንሰን እና ሙዚቀኞቹ ኬሊ ሮውላንድ፣ ሲያራና ሌሎችም በሙዚቀኛዋ ህልፈት የተሰማቸውን አጋርተዋል።