ዶናልድ ትራምፕ "በግሩም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ" የዋይት ሐውስ ዶክተር አስታወቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ "በግሩም የአእምሮ እና የአካል ጤና" ላይ እንደሚገኙ የዋይት ሐውስ ዶክተር አስታወቁ።
ትራምፕ በሁለተኛ የፕሬዝደንትነት ዘመናቸው የመጀመሪያውን የጤና ምርመራ ዋሺንግተን ዲሲ አካባቢ በሚገኝ ሆስፒታል ማድረጋቸው ተሰምቷል።
ፕሬዝደንቱ ባለፈው ሐምሌ የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ ሳለ በተደረገባቸው የግድያ ሙከራ ምክንያት "ቀኝ ጆሯቸው አካባቢ የጥይት ቁስል" እንዳለባቸው ተገልጿል።
"ፕሬዝደንት ትራምፕ በግሩም ጤንነት ላይ ነው የሚገኙት። ልባቸው፤ የነርቭ ሲስተሞቻቸው እና ጠቅላላ አካላዊ ጤናቸው አስደናቂ ነው" ሲሉ ዶክተራቸው ካፕቴን ሾን ባርባቤላ በማስታወሻቸው ፅፈዋል።
ትራምፕ ባለፈው ጥር ወደ ዋይት ሐውስ የመጡት በ78 ዓመታቸው ሲሆን ይህ ሥልጣን ሲይዙ ዕድሜያቸው የገፋ ፕሬዝደንት ያደርጋቸዋል።
የቀድሞው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ከሥልጣን ሲወርዱ ዕድሜያቸው 82 ነበር።
ባለፈው አርብ አምስት ሰዓት በወሰደው ዋልተር ሪድ ሆስፒታል በተከናወነው የጤና ምርመራ ትራምፕ በርካታ የደም ምርመራዎች፣ የልብ ምርመራ፣ እና አልትራሳውንድ እንደተደረገላቸው ዶክተራቸው ጠቁመዋል።
ዶክተሩ የአሜሪካ ባሕር ኃይል አባል የነበሩ፤ በኢራቅ እና በአፍጋኒስታን ያገለገሉ የቀድሞ ወታደር ናቸው።
"ፕሬዝደንት ትራምፕ ድንቅ የአእምሮ እና የአካል ጤንነት ላይ ነው ያሉት። የሀገሪቱ ርዕሰ ብሔር እና ጠቅላይ አዛዥ ሆነው ሥራቸውን በአግባቡ መወጣት የሚችሉ ናቸው" ይላል ዋይት ሐውስ እሑድ ይፋ ያደረገው የዶክተሩ ማስታወሻ።
ፕሬዝደንቱ የአእምሮ ጤናቸውን ለማወቅ በሚል ፈተና እንደተሰጣቸው እንዲሁም ሌሎች የአእምሮ ፍተሻዎች እንደተደረጉላቸው ማስታወሻው ጠቅሶ ድባቴም ሆነ ጭንቀት እንደሌለባቸው አስታውቋል።
ዶ/ር ባርባቤላ እንዳስታወቁት ትራምፕ ሞንትሪያል ኮግኒቲቭ አሰስመንት የተሰኘው ፈተና ተሰጥቷቸው 30 ከ30 ደፍነዋል። ይህ ፈተና የሚሰጠው የአእምሮ ጤናን ለመፈተሽ እና የመርሳት በሽታ አደጋ አለ ወይ የሚለውን ለማወቅ ሲሆን እንስሳትን መሰየም፣ ስዕል እና ቃላትን ደጋግሞ መጥራት የፈተናው አካል ናቸው።
ቅዳሜ ኤር ፎርስ ዋን ወደተሰኘው አውሮፕላናቸው ከመሳፈራቸው በፊት ለጋዜጠኞች ንግግር ያሰሙት ትራምፕ "ሁሉንም ጥያቄ በትክክል መልሻለሁ" ብለዋል።
"በጠቅላላው በጣም መልካም የሚባል አቋም ላይ ነው ያለሁት። ጤናማ ልብ፣ መልካም መንፈስ፣ በጣም መልካም መንፈስ።"
ምንም እንኳ ዶክተሮች የሕይወት ዘይቤያቸውን እንዲቀይሩ "ምክር ቢጤ" ጣል እንዳደረጉላቸው ቢናገሩም ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
በዶክተሩ ማስታወሻ መሠረት ፕሬዝደንቱ የኮሌስትሮል መጠናቸው ለመቆጣጠር መድኃኒት የሚወስዱ ሲሆን ለልብ በሽታ አስፒሪን እንዲሁም ለቆዳቸው ጤንነት ደግሞ ሞሜታሶን የተሰኘ ክሪም ይቀባሉ።
ፕሬዝደንቱ ክብደታቸው 101 ኪሎ ግራም፤ ቁመታቸው ደግሞ 1.89 ሴንቲሜትር ገደማ እንደሆነ ማስታወሻው ያሳያል።












